
24 መጋቢት 2025
የትራምፕን አስተዳደር አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ውዝግብ ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ከአሜሪካ እንዲባረሩ የተደረጉት የደቡብ አፍሪካው አምባሳደር በአገራቸው ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።
አምባሳደር ኢብራሂም ራሱል እሁድ ዕለት፣ መጋቢት 14/ 2017 ዓ.ም በኬፕታውን በሚገኘው ዓለም አቀፉ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
አምባሳደሩን በአየር ማረፊያው ሲጠባበቁ የነበሩ የአፍሪካ ናሺናል ኮንግረስ ፓርቲ፣ የደቡብ አፍሪካ ኮሚዩኒስት ፓርቲ እና የሰራተኛ ማህበራት እና ሌሎች ደጋፊዎቻቸው ሲዘፍኑ እና ሲደንሱ ታይተዋል።
አንዳንዶች “ኢብራሂም ራሱል አገራችንን በክብር አገልግለዋል” የሚሉ መፈክሮችንም ይዘው ነበር።
ትራምፕ ስልጣን መረከባቸውን ተከትሎ በአሜሪካ እና በደቡብ አፍሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት የተሞላበት ሆኗል።
አምባሳደሩ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር እሳጣ ገባ ያስገባቸው ከዚያ ቀደም ብሎ አንድ የደቡብ አፍሪካ ቲንክ ታንክ ያዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ላይ የሰጡት አስተያየት ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ “አሜሪካን የሚጠላ ዘር ላይ የሚያተኩር ፖለቲከኛ” ብለው ከፈረጇቸው በኋላ፤ በአገሪቱ ተቀባይነት የላቸውም ሲሉ ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
የ62 ዓመቱ ዲፕሎማት የዶናልድ ትራምፕን ፖሊሲ እንዲሁም በአህጉሪቷ ላይ ስለሚኖረው አንድምታ ትንታኔያቸውን ሰጥተዋል።
አምባሳደሩ የሰጡት አስተያየት ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ ያጸደቀችው የመሬት ፖሊሲ በተወሰኑ “ማኅበሰረሰቦች” ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል ለአገሪቱ የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጣቸውን ተከትሎ በአገራቱ መካከል ውዝግብ መነሳቱን ተከትሎ ነው።
- አሜሪካ በቅርቡ ያባረረቻቸው የደቡብ አፍሪካው አምባሳደር ማን ናቸው?20 መጋቢት 2025
- የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነታቸውን በማወጅ የመጀመሪያ የሆኑት ኢማም በደቡብ አፍሪካ ተገደሉ17 የካቲት 2025
- አሜሪካ በቅርቡ ያባረረቻቸው የደቡብ አፍሪካው አምባሳደር ማን ናቸው?20 መጋቢት 2025

Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ደቡብ አፍሪካ ከጨቋኙ የአፓርታድ ስርዓት ከ30 ዓመታት በፊት ብትላቀቅም አሁንም አብዛኛው የአገሪቱ የእርሻ መሬቶች አነስተኛ በሆኑት ነጮች እንደተያዘ ነው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የመሬት ባለቤትነት በአገሪቱ አከራካሪ እና አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ የቆየ ሲሆን በቅርብ ጊዜ የጸደቀው የመሬት ፖሊሲ ይህንን ኢፍትሃዊነት ለማስተካከል ያለመ ነው ተብሏል።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአንዳንድ ሁኔታዎች ያለ ካሳ መሬት መውረስ የሚያስችል ረቂቅ ሕግ እንዲሆን ፈርመዋል። የአሜሪካ መንግሥት በደቡብ አፍሪካ አናሳ ነጮች ኢ-ፍትሃዊነት እየተፈጸመባቸው ነው ሲል ከሷል።
አምባሳደር ራሱል በበኩላቸው ትራምፕ “የበላይነትን ለማስፈን እየሞከሩ ነው” ብለዋቸዋል።
አክለውም በአሜሪካ ነጮች አናሳ የመሆናቸው አዝማማሚያ መታየቱን ተከትሎ “ነጮችን ተጠቂ አድርጎ በመሳል ለማስጮህ እየሞከሩ ነው” ብለዋቸዋል።
አምባሳደሩ ኬፕታውን ከደረሱ በኋላ ምንም የሚጸጽታቸው ነገር እንደሌለ ተናግረው የሰጡትንም አስተያየት ትክክል ነው ብለዋል።
አምባሳደሩ የደቡብ አፍሪካ ምሁራን እና ፖለቲካ አመራሮችን ለማንቃት ያስተላለፉት መልዕክት ነው ብለዋል።
“በአሜሪካ ውስጥ የምንታይበት ሁኔታ እንዲቀየር እፈልጋለሁ። ከአሜሪካ ጋር ከዚህ ቀደም ስናደርገው የነበረው አሰራር መልካም አልነበረም” ሲሉም ነው የተናገሩት።
የአምባሳደር ራሱል መባረረ በአሜሪካ ያልተለመደ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ ነው።
ከዚህ ቀደም ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው ዲፕሎማቶች ቢባረሩም በአምባሳደር ደረጃ ግን ብዙም የሚታይ አይደለም።
ራሱል በገዢው ፓርቲ የአፍሪካ ናሺናል ኮንግረስ በተለያዩ የስልጣን ቦታዎች አገልግለዋል።
ከዚያም ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስልጣን ላይ ከመጡ በኋላ ከአውሮፓውያኑ 2010-2015 ድረስ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ።
አምባሳደሩ ከዚህ ቀደም ባላቸው ልምድ እንዲሁም ከዋሽንግተን ጋር ባላቸው ሰፋ ያለ ግንኙነት ድጋሚ በአውሮፓውያኑ 2024 አምባሳደር እንዲሆኑ ተሾመዋል።
አፓርታይድን በመታገል ወደ ፖለቲካ ህይወት የተቀላቀሉት አምባሳደሩ የፍልስጤም አገር ምስራታን የሚደግፉ ናቸው።
ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው በሚል በዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት የከሰሰቻት ሲሆን ይህም ጉዳይ በጦር መሳሪያ ጭምር እየደገፈቻት ያለችውን አሜሪካን አስቀይሟል።