
24 መጋቢት 2025
የፕሬዝደንት ጣይብ ረሲፕ ኤርዶዋን ቀንደኛ ተቀናቃኝ በሙስና ተጠርጥረው መታሰራቸውን ተከትሎ በመላው ቱርክ የተነሳው ከፍተኛ ተቃውሞ ተባብሶ ቀጥሏል።
ኤክሬም ኢማሞግሉ የኢስታንቡል ከንቲባ ሲሆኑ ባለፈው ከሶስት ዓመታት በኋላ ለሚካሄደው ምርጫ የሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ (ሲኤችፒ) ዕጩ ሆነው እሑድ ዕለት ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
ሰውየው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ ቱርክ ላለፉት 10 ዓመታት አይታ በማታወቅ ተቃውሞ የተናጠች ሲሆን ፖሊስ ሰልፈኞች ላይ አስለቃሽ ጪስ እና የጎማ ጥይት ተኩሷል።
ኢማሞግሉ እሳቸው ላይ የተከፈቱ ክሶች ፖለቲካዊ እንደሆኑ በመናገር “በፍፁም አላጎበድድም” ሲሉ በቁጥጥር ሥር ከመዋላቸው በፊት በኤክስ ገፃቸው ፅፈዋል።
ኤርዶዋን ሰልፎቹን ወቅሰው ሲኤችፒ “ሰላማችንን ሊበጠብጥ እና ሕዝባችንን ሊከፋፍል የተነሳ” ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ለአምስተኛ ተከታታይ ምሽት በርካታ ሰዎች በኢስታንቡል ከተማ አዳራሽ አመሻሹን እየተገኙ የቱርክ ባንዲራ እያውለበለቡ ከአድማ በታኝ ፖሊስ ፊት ለፊት ሲዘምሩ እና ሲጮሁ ታይተዋል።
አንዳንድ የፖሊስ መኮንኖች ግፊት ያለው ውሀ እና የሚያቃጥል ኬሚካል ሲረጩ ታይተዋል።
የኢማሞግሉ ባለቤት ዲሌክ ካያ ኢማሞግሉ ለተሰበሰበው ሕዝብ ባደረጉት ንግግር ባላቸው የተጋፈጠው “ኢ-ፍትሐዊነት” ማንም ሊቀበለው የሚገባ እንዳልሆነ ገልፀዋል።
በአውሮፓውያኑ 2013 በቱርክ ከተከሰተው የጌዚ አመፅ በኋላ በሀገሪቱ ታሪክ ትልቁ የሚባል ሰልፍ እየተካሄደ ይገኛል።
ከቱርክ 81 ግዛቶች መካከል 55 በሚሆኑ የተቃውሞ ሰልፍ እየተደረገ መሆኑን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
- አስፈላጊ እየሆነ ስለመጣው ፋይዳ መታወቂያ ሊያውቋቸው የሚገቡ 8 ጉዳዮች24 መጋቢት 2025
- በስኮትላንድ በኤርትራዊው ታዳጊ አሜን ተክላይ ግድያ ሶስተኛ ተጠርጣሪ ተያዘ24 መጋቢት 2025
- አስፈላጊ እየሆነ ስለመጣው ፋይዳ መታወቂያ ሊያውቋቸው የሚገቡ 8 ጉዳዮች24 መጋቢት 2025
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ነጋዴዎችን ጨምሮ ኢማሞግሉ እና ሌሎች 100 ባለፈው ረቡዕ ነው ለጥየቃ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት።
ከንቲባው በይፋ በቁጥጥር ሥር የዋሉት እሑድ ነው።
“ወንጀለኛ ቡድን በማቋቋም እና በማስተዳደር፣ ሙስና በመቀበል፣ አስገድዶ ገንዘብ በመቀበል እና ግላዊ መረጃ በመቅዳት እንዲሁም ጨረታ በማጭበርበር” ክስ ቀርቦባቸዋል።
ፍርድ ቤት እስኪቀርቡ ድረስ እስር ቤት እንደሚቆዩ ተነግሯል። ኤኤፍፒ እና የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ወደ ሲሊቭሪ እስር ቤት ተወስደዋል ሲሉ ዘግበዋል።
ኢማሞግሉ በቀረበባቸው ክስ ምክንያት ከከንቲባነታቸው መነሳታቸውን የቱርክ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ኢማሞግሉ እስራቸውን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው “ዲሞክራሲያችን ላይ የተቀባ ጥላሸት” ሲሉ የፃፉ ሲሆን ትክክለኛው የፍርድ ቤት ሒደት ተግባራዊ አልተደረገም ብለዋል።
በጠበቃቸው አማካይነት በኤክስ ገፃቸው ባጋሩት ፅሑፍ ለተቃዋሚዎች ሰላምታቸውን አስተላልፈው መራጮች ቱርክ “ኤርዶዋን እንደበቃት” አሳይተዋል ብለዋል።
ኢማሞግሉ ሲኤችፒ ፓርቲን ወክለው ለመወዳደር የታጩ ብቸኛው ሰው ነበሩ።
ምንም እንኳ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ዕጩ ከመሆን እና ፕሬዝደንት ሆኖ ከመመረጥ ባያግዳቸውም በቀረቡባቸው ክሶች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ መወዳደር አይችሉም።
እሑድ ዕጩዎችን ለመምረጥ በርካታ ቱርካዊያን ወጥተው ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
ዲሌክ ካያ ኢማሞግሉም ድምፅ ሲሰጡ የሚያሳይ ፎቶ አጋርተዋል።
ኢማሞግሉ የወቅቱን የቱርክ ፕሬዝደንት ኤርደዋንን ሊሞግቱ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
ኤርዶዋን በጠቅላይ ሚኒስትር እና ፕሬዝደንትነት ቱርክን ላለፉት 22 ዓመታት አገልግለዋል።
በቱርክ ሕገ-መንግሥት መሠረት ኤርዶዋን በአውሮፓውያኑ 2028 በሚደረገው ምርጫ መወዳደር አይችሉም።