በኻን ዩኒስ ሆስፒታል ላይ እስራኤል የፈፀመችው ጥቃት

24 መጋቢት 2025

እስራኤል እሑድ አመሻሹን ጋዛ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ ባደረሰችው ጥቃት ነባር የሐማስ አመራር እና ረዳታቸው መገደላቸውን ሐማስ ለቢቢሲ አሳወቀ።

በኻን ዩኒስ ግዛት ናስር ሆስፒታል ላይ በደረሰው ጥቃት የሐማስ የፋይናንስ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ኢስማኢል ባርሁም መገደላቸው ተሰምቷል።

ግለሰቡ ከአራት ቀናት በፊት በእስራኤል ጥቃት በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት በሆስፒታሉ ሕክምና እያገኙ እንደነበር የሐማስ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የእስራኤል ጦር ኃይል ባወጣው መግለጫ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ይንቀሳቀስ የነበረ ቁልፍ የሐማስ ላይ ጥቃት ማድረሱን አስታውቋል።

ጦር ኃይሉ “ከባድ የመረጃ ስብሰባ ከተሠራ በኋላ” በፈፀመው ጥቃት “ነጥሎ የሚመታ መሣሪያ” መጠቀሙን ገልጿል።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንዳለው በጥቃቱ የሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ “ሌሎች በርካታ” ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ሚኒስቴሩ አክሎ እንደገለፀው በጥቃቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት የሆስፒታሉ ክፍል ሠራተኞች ከአካባቢው ለቀው ወጥተዋል።

ቢቢሲ ማጣራት የቻለው ተንቃሳቃሽ ምስል እንደሚያሳየው ከሆነ ከጥቃቱ በኋላ በሥፍራው የነበሩ ሰዎች እሣቱን ለማጥፋት ሙከራ ሲያደርጉ ነበር።

እስራኤል በተደጋጋሚ ሐማስ ሆስፒታሎችን በመሸሸጊያነት ይጠቀማል እንዲሁም ለጦር መሣሪያ ክምችት እና ለዕዝ ማዕከልነት ይጠቀምባቸዋል ስትል ትወቅሳለች።

ነገር ግን ሐማስ ይህን ወቀሳ ፈፅሞ አይቀበለውም።

እስራኤል በኻን ዩኒስ እሑድ በፈፀመችው ጥቃት ሌላኛው የሐማስ አመራር ሳላህ አል-ባርዳዊል መገደላቸውን የሐማስ ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስቴሩ እንዳለው በኻኒ ዩኒስ እና ራፋህ እሑድ ጥዋት በተፈፀሙ ጥቃቶች 30 ሰዎች ተገድለዋል፤ አመሻሹን ደግሞ ሆስፒታሉ ጥቃት ተፈፅሞበታል።

እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ ባለፈው ማክሰኞ ድጋሚ ጀምራለች። ይህም ለሁለት ወራት ያክል የቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲቋረጥ ምክንያት ሆኗል።

ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በተፈፀሙ ጥቃቶች በጋዛ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

እስራኤል በዩናይትድ ስቴትስ የቀረበውን አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት አልቀበልም ብሏል ስትል ሐማስን ትወቅሳለች። ሐማስ ደግሞ እስራኤል ዋናውን የተኩስ አቁም ስምምነት አፍርሳለች ሲል ይወቅሳል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ48 ሺህ189 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሦስተኛው የጋዛ ሕንጻዎች መውደማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።