ኤርትራዊው ታዳጊ አሜን ተክላይ ግድያ

24 መጋቢት 2025, 08:00 EAT

በስኮትላንድ፣ ግላስጎው ነዋሪ የነበረው ታዳጊ አሜን ተክላይ ግድያ ጋር በተያያዘ ሶስተኛ ተጠርጣሪ ተያዘ።

የ15 ዓመቱ አሜን ከሶስት ሳምንታት በፊት በከተማዋ ሜሪሂል አካባቢ ክላሬንደር ጎዳና ላይ በተፈጸመበት ጥቃት በጸና ቆስሎ መገኘቱ ይታወሳል።

ምንም እንኳ የድንገተኛ ሕክምና ባለሙያዎች በስፍራው ቢደርሱም ሕይወቱ እዚያው ማለፉ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት የ16 ዓመት ታዳጊ የሆነው ሶስተኛው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር እንደዋለ እና እንዲሁም ክስ እንደተመሰረተበት የስኮትላንድ ፖሊስ አስታውቋል።

ታዳጊው ዛሬ፣ ሰኞ ግላስጎው በሚገኝ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብም ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም የ14 ዓመት ልጅ ታዳጊ በአሜን ግድያ እና በጥቃት ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቧል። ሌላኛው ሁለተኛው ተከሳሽ የ15 ዓመት ታዳጊ በጥቃት ወንጀል እንዲሁ ክስ ተመስርቶበታል።

አሜን ከአባቱ ጋር በግላስጎው ከተማ ይኖር የነበረ ሲሆን በቅርቡም ነው በዩኬ ‘ የመቆየት መብት’ የተሰጠው።

አሜን፣ ጆርዳንሂል በተሰኘ ስፍራ በሚገኘው የቅዱስ ቶማስ አኩዋናስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበር።

አሜን ተግባቢ፣ በጣም ተወዳጅ እንዲሁም በሙዚቃ እና መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ፍላጎት የነበረው ታዳጊ እንደነበር የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ገልጸዋል።

ለአሜን ኃዘናቸውን ለመግለጽ አበባ ያስቀመጡ ሰዎች

ርዕሰ መምህር ክሌር ማኪንሊ የታዳጊው ሞት “ለትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ አስደንጋጭ” ነበር ብለዋል።

የ17 ዓመት እህቱ ደሊና በበኩሏ አሜን “የዩናይትድ ኪንግደም ዜግነት አግኝቶ ዶክተር፣ መሐንዲስ ወይም የቅርጫት ኳስ ተጫዋች የመሆን” ተስፋን ሰንቆ እንደነበር ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ስኮትላንድ ተናግራለች።

ታዳጊው በግላስጎው ለስምንት ዓመታት ያህል ኖሯል።

አሜን “ወንድሜ ብቻ ሳይሆን የቅርብ ጓደኛዬም ነበር” ስትል ለቢቢሲ ስኮትላንድ ኒውስ ተናግራለች።

አክላም “በጣም ተወዳጅ ልጅ፣ በጣም ደግ እና ብሩህ ነበር” ብላለች።

የስኮትላንድ ፖሊስ በአሜን ግድያ ላይ ሰፊ ምርመራ ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል።

ሱፐር ኢንቴንደንት ቼሪል ኬሊ እንዳሉት “መልሱ ያለው የአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ነው” ካሉ በኋላ፤ ባልደረቦቻቸው የመንገድ ላይ ካሜራዎችን እየተመለከቱ እንዲሁም ቤት ለቤት በመሄድ ጥያቄዎችን እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም “በዚህ አስጨናቂ ጊዜ ሀሳባችን ሁሉ ከአሜን ቤተሰቦች እና ወዳጆች ጋር ነው። ለእነሱ ልዩ ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

ፖሊስ ግድያውን በሚመለከት መረጃ ያለው ማንኛውም ሰው ለዚህ ምርመራ ተብሎ በተከፈተው የመረጃ መቀበያ በኩል ጥቆማውን እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።