አዮን ፖላርድ

24 መጋቢት 2025

አዮን ፖላርድ ሆስፒታል አልጋ ሲይዝ 286 ኪሎግራም ነበር የሚመዝነው። ኩላሊቱ መሥራት እያቆመ ነበር።

ለአንድ ቀንም በሕይወት ስለመቆየቱ እርግጠኛ አልነበረም። በወቅቱ 27 ዓመቱ ነበር።

ኩላሊቱ በቀዶ ሕክምና መቀየር ነበረበት። ነገር ግን ከልክ ባለፈ ውፍረቱ ምክንያት ቀዶ ሕክምናው ሊካሄድ አልቻለም።

“ሰውነቴ እስከሚችለው ድረስ ራሴን እየገፋሁ ነበር። ሐኪሞቹ ቀጣዩቹ ስምንት ሰዓታት በሕይወቴ ቁልፍ ሰዓታት መሆናቸውን ነገሩኝ። ጠዋት በሕይወት ላልኖር እንደምችልም ገለጹልኝ” ሲል ወቅቱን ያስታውሳል።

191 ኪሎግራም ከቀነሰ በኋላ አዲስ ኩላሊት በቀዶ ሕክምና እንደሚሰጠው ተነግሮታል

ዌልስ ውስጥ በሚገኘው ካረናፎን የሚኖረው አዮን በወቀቱ ኩላሊቱ ከጥቅም ውጭ ሆኖ ነበር።

“መጥፎ ሁኔታ ውስጥ መሆኔን ነገሩኝ። አዲስ ኩላሊት እንዳይሰጠኝ ሰውነቴ በጣም ትልቅ ነበር። ስለዚህ የኩላሊት እጥበት መጀመር አለበት ተባልኩ” ይላል።

‘ምግብ ተቆጣጥሮኝ ነበር’

በተለይ እናቱ በሁኔታው በጣም ተጨንቃ ነበር። የተቀሩት ቤተሰቦቹን ጓደኞቹም የጤናው ነገር አሳሰባቸው።

“ጤናው አስጨነቀን። በምግብ ምክንያት ራሱን ወደ መቃብሩ እየወሰደ ነበር” ትላለች እናቱ ኤልሪ።

በሰውነቱ ልክ የሚሆን ልብስ ለማሰፋት አስቸጋሪ ነበር። ወገቡ 72 ኢንች ደርሶ ነበር።

“ራሴን ማዘዝ አልችልም ነበር። የሚቆጣጠረኝ ምግብ ነበር። ምግብ የማደርገውን ሁሉና ሕይወቴን ተቆጣጥሮት ነበር። የምግብ ሱስ እንዳለብኝ ማመን አልፈለግኩም። እጅግ በጣም እመገብ ነበር” ይላል።

ለነበረበት ሁኔታ ምክንያቶችን እየደረደረ ራሱን ቢደልልም እውነታው ግን “ስግብግብና ሰነፍ መሆኔ ነበር” ሲል ወደኋላ መለስ ብሎ ያስታውሳል።

አሁን ላይ ሆኖ ሕይወቱን ወደኋላ መለስ ብሎ ሲመለከት “ያሳፍረኛል” ይላል።

“ሕይወቴን በዛ መንገድ በመኖሬ አፍራለሁ። ሰውነቴን ምን እንዳደረግኩት የታወቀኝ አሁን ነው።”

ሰውነቱን ለማስተካከል ሰባት ዓመታት ወስዶበታል። ሆዱን ለመቀነስና ቆዳውን ለማጥበብ ቀዶ ሕክምና አድርጓል።

አዮን ፖላርድ

191 ኪሎግራም ከቀነሰ በኋላ የኩላሊት ቀዶ ሕክምና ሊደረግለት እንደሚችል ተነገረው።

ኩላሊቱን የምትለግሰው እናቱ ነች።

“ሕይወቱን መኖር ይገባዋል” ስትል ለልጇ በደስታ ኩላሊት እንደምትለግስ ትናገራለች።

አዮን ፖላርድ

አዩን አሁን ሕይወቱ ተለውጧል።

“ብዙ ነገር ነው ያሳለፍኩት። አሁን ያለ ችግር መኖር ነው የምፈልገው” ይላል።

እናቱ ኩላሊት ልትሰጠው መሆኑን በመጥቀስ “የእናቴ ጤና በእርግጥ ያሳስበኛል” ይላል።

“ራሷን ለአደጋ አጋልጣ የእኔን ሕይወት ለማስተካከል እየሞከረች ነው” ሲልም ስሜቱን ገልጿል።