ብርጋዲየር ጄነራል ምግበይ ሃይለ
የምስሉ መግለጫ,ብርጋዲየር ጄነራል ምግበይ ሃይለ

24 መጋቢት 2025

የትግራይ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ ብርጋዲየር ጄነራል ምግበይ ሃይለን “ለፋኖ ድጋፍ ይሰጣሉ” የሚለውን ጨምሮ ሌሎችም ያቀረባቸውን ክሶች ኃላፊነት የጎደለው ነው ሲል ወቀሰ።

የሰላምና ጸጥታ ቢሮው፤ “እሳቱ ባለበት ለማርገብ ከመጣር ይልቅ ማርገብገብ፣ ላጋጠመህ የራስ ችግር ለተግባራዊ መፍትሔ ከመጣር ይልቅ የማይመለከተው ኣካል በመፍጠርና ጣት በመቀሰር ሰላምና ዕድገትን እንዳይጸና የሚያደርግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው” ሲል ተችቷል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በፌስቡክ ገጹ፤ የትግራይ ኃይሎች አመራር የሆኑትን ብርጋዲየር ጄነራል ምግብ ሃይለን “ግብረ አበሮቹ አደራጅነትና አይዞህ ባይነት ዘመቻ አንድነት በሚል ስያሜ ፋኖ በተለያዩ ክልል የዞን ወረዳዎች ትንኮሳ ለመፈጸም ሞክሯል” በሚል መግለጫ አውጥቷል።

የትግራይ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ በምላሹ፤ “ጀነራል ምግበይና ጓዶቹ በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት በጥብቅ ዲሲፕሊን ተገዝተው ሥራቸውን የሚፈፅሙ እንጂ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ ምንም ዓይነት እንቅቃሴ የሌሉና ያልነበሩ መሆኑን ሊታወቅ ይገባል” ብሏል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መጋቢት 12፣ 2017 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፤ “በተለያዩ ክልል የዞን ወረዳዎች ትንኮሳ ለመፈጸም ሞክሯል” ያለውን ኃይል “ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው ፅንፈኛው ቡድን ተደምስሷል” ብሏል።

የትግራይ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ፣ መጋቢት 13፣ 2017 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፤ “እንዲህ ዓይነቱን እርባና ቢስ ዜና መዘርጋት የትግራይ ሠራዊት ለሰላም እየከፈለ ያለውን ዋጋና ልፋት የውሃ ሽታ የሚያደርግና በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት ዓይነት መግለጫ መውጣቱ ከልብ ኣሳዛኝ ነው” ብሏል።

የትግራይ ኃይሎች አመራር የሆኑትን ብርጋዲየር ጄነራል ምግብ ሃይለ ከኢትዮ ፎረም ጋር ባደረጉት ቆይታ “እኛ እንደዛ አይደለንም። አናደርገውም፤ በፍጹም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

የፕሪቶርያ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን “እንደ ሕዝብም፣ እንደ ጊዜያዊ አስተዳደርም፣ እንደ ሠራዊቱ አባላትም” በሕጉ መሠረት እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ የቀረበባቸውን ክስ በማስተባበል “እኔ እንደዛ አይደለሁም። የትግራይ ሕዝብ ጥያቄም በግለሰቦች አይወሰንም። አግባብ ያለው አደረጃጀት ያለን ነን” ሲሉ ተናግረዋል።

“ከፕሪቶርያ ስምምነት ውጭ ያለአግባብ፣ አንዳንዴ ከኤርትራ፣ አሁን ደግሞ የመጣ ከፋኖ [ጋራ መሥራት] ሌላም ሊመጣ ይችላል” በማለት “ከስምምነት ውጭ የሚደረግ እንቅስቃሴ እንታገላለን፤ እናስተካክላለን፤ ወደ ትክክለኛ መንገድ እንዲገባ ነው [የምንሠራው]” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ያነጋገረው የወሎ ቤተ- አማራ ፋኖ ቃል አቀባይ አበበ ፋንታሁን፣ ብርጋዲየር ጄነራል ምግበይ ሃይለ የፋኖን ኦፕሬሽን “ደግፈዋል” በሚል በመከላከያ ሠራዊነት የቀረበው ክስ “ሐሰት ነው” ብለል።

ብርጋዲየር ጄነራል ምግበይ ሃይለ ከፋኖ ታጣቂ ቡድን ጋር ማንኛውም ግንኙነት እንደሌላቸውም ለሮይተርስ ገልጿል።

የመከላከያ ሠራዊት በፌስቡክ ገጹ ላይ ብርጋዲየር ጄነራል ምግበይ ሃይለ “የፕሪቶሪያን ስምምነት እንዲፈርስና እንዳይሳካ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ያለ ከመሆኑም በላይ የጊዜያዊ መስተዳድሩን ማኅተም ለመንጠቅ እና በኃይል አፍርሶ ሥልጣን ለመያዝ የሞከረ የፀረ ሠላምና ፀረ ልማት አራማጅ ነው” ሲል ከሷል።

የትግራይ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ፣ መግለጫውን “ግልብና ብስለት የጎደለው” ብሎ ከነቀፈ በኋላ “የትግራይን ሕዝብ ግዛታዊ አንድነት ለማስከበር የሚደረግን ተጋድሎ እንዲህ አቃሎና አንኳሶ ማቅረብ ግን የፕሪቶርያውን ስምምነት ወደ መሬት ወርዶ ተግባራዊ እንዲሆን ትልቅ ድርሻ ካለው ተቋም የማይጠበቅና ኃላፊነት የጎደለው ስለሆነ በፍጥነት መስተካከል አለበት ብሏል።

የመከላከያ ሠራዊት “የሰላም ጠንቅ” ሲል የከሰሳቸውን የትግራይ ኃይሎች አመራር የሆኑትን ብርጋዲየር ጄነራል ምግብ ሃይለን “ለዚህ መሰሪ ተግባሩ ጅላጅሉን ፋኖ እንደተባባሪነት በመጠቀም ፅንፈኛው ፋኖ በራሱ ክልል ላይ ያልተገባ ውድመት እንዲፈፅም አዞታል” በማለት ወንጅሏል።

መከላከያ ሠራዊት አክሎም “ዘመቻ አንድነት በሚል ስያሜ ፅንፈኛውን አስተባብሮ በጀመረው ትንኮሳ ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሷበታል። በደቡብ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በሰሜን ጎጃም፣ በምሥራቅ ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃም እንዲሁም በሰሜን ወሎ የምግበይ ላይለ ተላላኪ ፅንፈኞች በለኮሱት እሳት ተለብልበዋል” ብሏል።

317 ተዋጊዎች መገደላቸውን፣ 125 የቆሰሉና ሌሎችም የተማረኩና እጅ የሰጡም እንዳሉ መከላከያ ሠራዊት ጠቅሷል።

ሮይተርስ ያነጋገረው የጎንደር ፋኖ ቃለ አቀባይ ዩሐንስ ንጉሡ በበኩሉ 602 የፌደራል ሠራዊት አባላት መገደላቸውን፣ 430 የቆሰሉና ሌሎችም የተማረኩ ወታደሮች እንዳሉ ገልጿል።

የወሎ ቤተ- አማራ ፋኖ ቃል አቀባይ አበበ ፋንታሁን፣ “30 ተዋጊዎች እንኳን አልተገደሉም” ሲል ለሮይተርስ ተናግሯል።

የትግራይ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ የመከላከያ ሠራዊትን ክስ “ውንጀላና ስም ማጥፋት” ሲል ተችቷል።

የትግራይ ኃይሎች አመራር የሆኑትን ብርጋዲየር ጄነራል ምግብ ሃይለ ከኢትዮ ፎረም ጋር ባደረጉት ቆይታ “አንድም የፋኖ አመራር ከእኔ ጋር ግንኙነት የለውም፤ አላደርገውም፤ አናደርገውም” ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊነት “በአሁኑ ጊዜ የትግራይን ወርቅ እየዘረፈ በኤርትራ በኩል አድርጎ እየሸጠ ይገኛል” በሚል ላቀረበው ክስ ምላሽ የሰጡት የትግራይ ኃይሎች አመራር ብርጋዲየር ጄነራል ምግብ ሃይለ “በፍጹም፣ በፍጹም እንደዛ ዓይነት ውስጥ የምገባ አይደለሁም. . . በትግራይ ውስጥም፣ አሁን ባለሁበት ቦታም፣ ድሮ በመከላከያ በነበርኩበትም፣ በቢዝነስ ውስጥም፣ ሁሉንም በአግባቡ የምሄድ ሕጋዊ ሰው ነኝ” ብለው ምላሽ ሰጥተዋል።

“ከኤርትራ ጋርም ምንም ዓይነት ግንኙነት የለኝም” ሲሉም አክለዋል።

የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ፤ አስመራ በህወሓት እና በትግራይ ክልል “ጊዜያዊ አስተዳደር እየተካሄደ ባለው ግጭት” ውስጥ “ምንም ዓይነት ሚና” እንደሌላት መናገራቸው አይዘነጋም።

በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ቀውስ ተከትሎ ብዙዎች በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።

የመከላከያ ሠራዊነት በፌስቡክ ገጹ ላይ “ምዕራብ ትግራይን አስመልሳለሁ በሚል ዕሳቤ፤ ሁለት ጊዜ የፌዴራል መንግስት ሠራዊትን ለማጥቃት ሞክሮ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ያስበላ ውጊያ እምቢ ሲለው የራሱን ታጣቂዎች ረሽኖና ገድሎ ውጊያው ሳይሳካለት አከርካሪው ተመትቶ ሸሽቷል” በሚል ያቀረበውን ክስ በተመለከት የትግራይ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ በሰጠው ምላሽ “በእርግጥ ዜናውን ከውጭ ለሚያይ ወገን ሊያደናግር ይችል ይሆናል፣ እውነቱንና የሠራዊታችንን ፍላጎትና ዓላማ ለሚያውቅ ግን “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ!!” ከመሆን የዘለለ ፋይዳ አይኖረው” ብሏል።

አክሎም “ይህ መግለጫ የሂደቶቹ ተቀጥላና እሳቱ ባለበት ለማርገብ ከመጣር ይልቅ ማርገብገብ፣ ላጋጠመህ የራስ ችግር ለተግባራዊ መፍትሄ ከመጣር ይልቅ የማይመለከተው ኣካል በመፍጠርና ጣት በመቀሰር ሰላምና እድገትን እንዳይፀና የሚያደርግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል” ብሏል

አያይዞም “ይቅርታ እንዲጠየቅ” ሲል በመግለጫው አክሏል።

ይህ በእንዲህ ሳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሁለት ዓመት የቆይታ ጊዜው የተጠናቀቀው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለሚቀጥለው አንድ ዓመት እንደሚቀጥል ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።

የቆይታ ጊዜው የተጠናቀቀውን ጊዜያዊ አተስዳደር ለማስቀጠል አስፈላጊ የሕግ ማሻሻያዎች እንደሚከናወኑም አስታውቀዋል። በዚህ መልኩ የሚቀጥለው አስተዳደር እስከ ቀጣይ ምርጫ ድረስ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

ይህንን ለማድረግ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ እና ከምክትሎቻቸው ጄነራል ታደሰ ወረደ እና ጄነራል ፃድቃን ገብረትንሳይ ጋር ምክክር መደረጉን ገልጸዋል።

ዐቢይ፤ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ፓርቲዎች ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ መሠረት አስፈላጊው የሕግ ማሻሻያ ተደርጎ ለሚቀጥለው አንድ ዓመት ይቀጥላል ብለዋል።