
24 መጋቢት 2025
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ትናንት ይፋ ባደረገው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ጭማሪ የአንድ ሌትር ቤንዚን ዋጋ 112 ብር ከ67 ሳንቲም ደረሰ።
የነጭ ናፍጣ ዋጋ ደግሞ የዘጠኝ ብር ገደማ ጭማሪ ተደርጎበታል።
ከእሁድ መጋቢት 14/2017 ዓ.ም. ምሽት ጀምሮ ተግባራዊ መሆን የጀመረው የነዳጅ ምርቶች ዋጋ ማሻሻያ በዚህ ዓመት ለሶስተኛ ጊዜ የተደረገ የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ ነው። መንግስት በነዳጅ ምርቶች ላይ ያደርግ የነበረውን ድጎማ በቀስ በቀስ ማንሳት የጀመረው በ2014 ዓ.ም. ነበር።
መንግሥት፤ ከሶስት ዓመት በፊት በጀመረው ሂደት የግል እና የተቋማት ተሽከርካሪዎች በአንድ ዓመት ውስጥ ከድጎማ ስርዓቱ የወጡ ሲሆን የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የሚያገኙት ድጎማ ደግሞ በአምስት ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ የማድረግ እቅድ ይዟል።
ይሁንና ባለፈው ዓመት መጨረሻ ሐምሌ ላይ መንግሥት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እገዛ መተግበር የጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከትሏል።
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ወደ ገበያ መር ስርዓት የተለወጠው የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት፤ በውጭ ምንዛሬ እየተገዛ በሚገባው የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከትሏል።
- የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለአዲስ ማደያዎች ነዳጅ ላለማቅረብ መወሰኑን አስታወቀ13 ታህሳስ 2024
- አስፈላጊ እየሆነ ስለመጣው ፋይዳ መታወቂያ ሊያውቋቸው የሚገቡ 8 ጉዳዮች24 መጋቢት 2025
- በስኮትላንድ በኤርትራዊው ታዳጊ አሜን ተክላይ ግድያ ሶስተኛ ተጠርጣሪ ተያዘ24 መጋቢት 2025

በውጭ ምንዛሬ ዋጋ ለውጥ ምክንያት የመጣው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በቀጥታ ተግባራዊ እንደማይሆን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መስከረም ላይ አስታውቆ ነበር። እንደ ሚኒስቴሩ ገለጻ በውጭ ምንዛሬ ለውጡ ምክንያት የመጣው ለውጥ ተግባራዊ የሚደረገው ለአንድ ዓመት ያህል በየሶስት ወሩ በሚደረግ የዋጋ ጭማሪ ነው።
በዚህ መሰረት መስከረም ወር ላይ የተደረገው የመጀመሪያው ማሻሻያ፤ በቤንዚን ላይ የ8 ብር ከ54 ሳንቲም ጭማሪ ያስከተለ ሲሆን የነጭ ናፍጣ ዋጋ ደግሞ በ6 ብር ከ54 ሳንቲም እንዲጨምር አድርጓል።
በዚህ ዓመት ሁለተኛው የዋጋ ጭማሪ የተደረገው ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ ነበር። ከሶስት ወር በፊት በተደረገው ማሻሻያ የአስር ብር ጭማሪ የተደረገበት ቤንዚን፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋጋው ከ100 ብር ተሻግሯል።
በወቅቱ የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋም ከነበረበት 77.76 ብር ወደ 109.56 አድጓል። ነጭ ናፍጣ እና ኬሮሲን ላይ የተደረገው የስምንት ብር ጭማሪ ነበር።
ትናትን ይፋ የተደረገው የዋጋ ማሻሻያ በዚህ ዓመት ከተደረጉት ከፍ ባለ ሁኔታ ቤንዚን ላይ 11 ብር ከ20 ሳንቲም ጭማሪ አስከትሏል። በዚህ የቤንዚን ዋጋ 112 ብር ከ67 ሳንቲም ደርሷል።
በነጭ ናፍጣ እና ኬሮሲን ላይ ደግሞ የስምንት ብር ከ95 ሳንቲም ጭማሪ ተደርጓል። በአዲሱ ዋጋ መሰረት የሁለቱ የነዳጅ ምርቶች መሸጫ በሊትር ወደ 107 ብር ከ93 ሳንቲም ከፍ ብሏል።
የሶስት ብር ከ64 ሳንቲም ጭማሪ ተደረገበት የአውሮፕላን ነዳጅ 113 ብር ከ20 ሳንቲም ገብቷል። የቀላል ጥቁር ናፍጣ ዋጋ 109 ብር ከ22 ሳንቲም የደረሰ ሲሆን ከባድ ጥቁር ናፍጣ ዋጋው ወደ 106 ብር ከ75 ሳንቲም አድጓል።
ከተያዘው 2017 ዓ.ም. መጀመር አንስቶ ለሶስት ጊዜ የተደረጉት ማሻሻያዎች፤ በቤንዚን መሸጫ ዋጋ ላይ የ30 ብር ጭማሪ አስከትለዋል። በሶስቱ ማሻሻያዎች ነጭ ናፍጣ ላይ የመጣው ጭማሪ 24 ብር ከ19 ሳንቲም ነው።
የአውሮፕላን ነዳጅ መሸጫ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር የ42.37 ብር ጭማሪ አስተናግዷል።