Andargachew Tsege
ቀን የካቲት 2017
በአንዳርጋቸው ጽጌ
የአማራን የህልውና አደጋ ከመከላከል ትግል ጋር የተያያዙ የተመጠኑ የግል ምልከታዎች!
ክፍል ፡ 12 የአማራ የህልወና ትግል በጤነኛ እና በታመሙ ብሄረተኞች እንቃስቃሴ ላይ ያሳደረው ተጽእኖና አንደምታው።
• በቅድሚያ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለብሄርተኛነት ስናወራ ሁለት አይነት ብሄረተኛነት መኖሩን መገንዘብ ያስፈልጋል። አንደኛው ብሄረተኛነት ጤነኛ የምለው ብሄረተኛነት ሲሆን ሌላው የታመመ ብሄረተኛነት የምለው ነው።
• ጤነኛ ብሄረተኛነት፣ ማህበርሰቦች ስለራሳቸው ባህል፣ ቋንቋ፣ ማንነት ላይ የተመሰረተ በራስ መተማመን ላይ የቆመ የማንነት/የራስ ግንዛቤ ነው። ይህ ብሄረተኛነት የሌሎች በተመሳሳይ መንገድ የተቀርጸ ብሄረተኛነት አያስደነግጠውም። የራሱን ብሄረተኛነት ለሌሎች ብሄረተኛነቶች አደጋ ነው ብሎ አያስብም። የራሱም ይሁን የሌሎች ብሄረተኛነት የሚገለጽባቸው ባህሎች ቋንቋዎች የሁላችንም ውበቶች ናቸው ብሎ የሚያምን ነው።
• ጤነኛ ብሄረተኛነት፣ መኖሪያ ቤቱን ካደረገው ሃገረ ኢትዮጵያ ጋር ጠብ የለውም። ማንነቱ ከነልዩ የሆኑ ባህርይው የሚከበረው ኢትዮጵያ በሚባል ሃገር ውስጥ ነው ብሎ ያምናል። ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ብትወድቅ አደጋ ላይ እወድቃለሁ ብሎ ያስባል። ለጋራ ጥቅምና ህልውና መከበር ሲባል ከልዩነት ይልቅ አንድነት የሚያስጨንቀው ነው። የዚህ አይነት የማንነት ግንዛቤ ያላቸው የጤነኛ ብሄረተኛነት ባላቤት የሆኑ ህዝቦች እና ልሂቃን በኢትይጵያ ውስጥ ትልቁን ቦታና ቁጥር የያዙ ናቸው። በዚህ ጤነኛ ብሄረተኛነት ውስጥ ከሁሉም ጎልቶ የሚታየው የአማራን ብሄረተኛነት ነው። ከየትኛው የአማራ ብሄረተኛነት/የማንነት ግንዛቤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታዩ ሌሎች የማንነት ግንዛቤዎች/ብሄረተኛነቶች ጋር ራሱን ሳያነጻጽር፣ ሌሎችን በጠላትነት ሳይፈርጅ በራሱ መልካም እሴቶች ላይ ብቻ የቆመ ብሄረተኛነት ነው። ይህ የአማራን ህዝብና ልሂቁን በአንድ ላይ ያስተሳሰረ የማንነት ግንዛቤ የጤነኛ ብሄረተኛ ሁነኛ መገለጫ ነው።
• በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ ሌሎች ብሄረተኛነቶች/የማንነት ግንዛቤዎች በህዝብ ደረጃ ጤነኛ ቢሆኑም፣ ህዝብን እና የብሄሩን ልሂቅ በአንድ ላይ በጤነኛ ብሄረተኛነት በማስተሳሰሩ ጉዳይ ላይ ችግር የሚታይባቸው ናቸው። በህዝብ በኩል ስለባህሉ፣ ቋንቋው፣ ሰለተወፊቱ፣ ስለማህበራዊ እሴቶቹ፣ ስለአኗኗር ዘይቤው ያለው የማንነት ግንዛቤ/ ብሄረተኛነት ልክ አንደአማራው ብሄረተኛነት/የማንነት ግንዛቤ በራሱ የቆመ ነው። ከሌሎች የማንነት ግንዛቤዎች ጋር ጠብ ወይም። ጥላቻ ያለው አይደለም። የትግራይ ገበሬና ለፍቶ አደር ከአማራ ገበሬና ለፍቶ አደር ጋር ጠብ የለወም። የኦሮሞ ገበሬና ለፍቶ አደር ከአማራ ገበሬና ለፍቶ አደር ጋር ጠብ የለወም። በህዝብ ደረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ማናቸውም የማንነት ግንዛቤዎች እሰላም በአንድነት ለመኖር ችግር የለባቸውም። ሆኖም ግን ከአማራ ውጭ፣ በልሂቁ የሚቀነቀኑ ብሄረተኛነቶች ግን እንደተራው ህዝብ ሁሉም ጤነኞች ናቸው ማለት አይቻልም።
• በበርካታ ማህበረሰቦች ውስጥ በልሂቁ የሚቀነቀነው ብሄረተኛነት/የማንነት ግንዛቤ በራሱ የቆመ ሳይሆን አንድ ህዝብ፣ አማራን በጠላትነት ፈርጆ የቆመ ነው። የታመመ የሚያደርገውም ይህ ነው። እንዲህ አይነቱ ብሄረተኛነት ትኩረቱ በልዩነት ላይ ነው። ኢትዮጵያ የሚባል ሃገር ቢኖር ባይኖር ጉዳዩ አይደለም። “የኢትዮጵያ እንደሃገር መቀጠል የሚያስደስተው አማራ የሚባል ህዝብ” አለ በሚል ስሌት ለአማራ ጥላቻ ሲል ሃገር የማፍረስ ጥረቱን እንደ ትልቅ ስኬት የሚቆጥር ነው። በጥላቻ ላይ የተገነባ ብሄረተኛነት በመሆኑ የአማራ ቋንቋ፣ የአማርኛ/የግእዝ ፊደሎች፣ የአማራ ባህል፣ እሴቶች በሙሉ የሚጠላ ነው።
• የታመመ ብሄረተኛ ባላቤት፣ ቻይናዎችና ጃፓኖች ለመዘመን፣ በቴክኖሎጂ ለመገስገስ ፊደላቸውን ወደላቲን ፊደል መቀየር እንዳልተገደዱ ያውቃል። የአማርኛ ቋንቋ የሚጻፍበት ፊደል፣ ብቸኛው የጥቁር ህዝቦች ፊደል፣ የግእዝ ፊደል እንደሆነ ያውቃል። ይህን እያወቀም አማራ ለሚባል ነገር ካለው ጥላቻ “የአማራ ፊደል ነው” ብሎ የፈጠራ ወሬ ያሰራጫል። ከዚህም ተነስቶ የኔ ነው የሚለው አብዛኛው ህዝብ ለማንበብና ለመጻፍ የሚጠቀምበትንና ሌሎች ኦሮምኛ የማያውቁ በኢትዮጵያ የሚገኙ ማህበረሰቦች፣ ኦሮምኛ በቀላሉ ሊማሩ የሚችሉበትን የግእዝ ፊደል አስወግዶ ጉዞውን ቀጥሏል። በቅኝ ሳይገዛ፣ ቅኝ ገዥዎችን አሳፍሮ እንዳልመለሰ፣ የቅኝ ገዥዎችን የነጮቹን የላቲን ፊደል በስራ ላይ እንዲውል ያደረገ ብሄረተኛነት ነው፤ ይህ የታመመ ብሄረተኛነት። በአማርኛ ቋንቋ አትናገሩ፣ ከአማራ ጋር የመሰረታችሁን ትዳር አፍርሱ፣ ከአማራ ነጋዴዎች ሸቀጥ አትግዙ ወዘተ የሚሉ በአንድ ህዝብ ላያ ያነጣጠረ ጥላቻ ላይ የተመሰረቱ ብሄረተኛነቶች የታመሙ ናቸው።
• እንዲህ አይነቱ የታመመ ብሄረተኛ ልሂቅ በጋራ ችግሮች ላይ ተወያይቶ ለሁሉም የሚበጅ ሰላማዊ መፍትሄ መፈለግ አይታየውም። ሰላማዊ መንገድ የማይታየው ሁሉንም ነገር በሜንጫ በጡጫ አሳካዋለሁ ብሎ የሚያምን ስለሆነ ነው። ሰውን የሚያክል ፍጡር በማንነቱ ስለሚጠላ ብቻ እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ መግደል፣ ንጽሃን ለመጨፍጨፍ ምንም አይነት የሞራል ልጓም የማይዘው ፍጡር ነው። ህዝብ በህዝብ ላይ ተነስቶ ደም እንደጎርፍ በፈስ ግድ የሌለው ፍጥረት ነው።
• የአማራ የህልውና ትግል ጤነኛ የሆነ ብሄረተኛነት ለተላባሱ ህዝቦችና ይህን ጤነኛ ብሄረተኛነት ለሚጋሩ የሌሎች ማህበረሰብ ልሂቃን ስጋት አይደለም። እንዳውም እነዚህ ልሂቃን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የታመመ ብሄረተኛነት ለሚያስተናግዱ አካላት የአማራ ብሄረተኛነት ማርከሻ አድረገው እያዩት ነው። ዛሬ በርካታ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ብሄርና ብሄረሰቦች የአማራ ፋኖ ትግል እንዲሳካ የሚፈልጉት፣ የማንነታቸው፣ የባህልና የቋንቋቸው መጠበቅ በነጻነት በሰላም ሰርተው የመኖር እድላቸው በታመሙ ብሄረተኞች ከመጨፍለቅ የሚያድን ዋስትና አድረገው የሚያዩት ስለሆነ ነው። የአማራ ህዝብ ትግል በእነዚህ ብሄረተኞች አይን አንደምታው በጎ ነው።
• በታመመ ብሄረተኛነት ለተለከፉ አካላት ግን የአማራው የህልወና ትግል ስጋት ሆኖባቸዋል። የፖለቲካዊና የወታደራዊ ጥንካሬው አስፈርቷቸዋል። በኦሮሞ ብልጽግና ውስጥ ላሉ አክራሪና ተረኛ ብሄረተኞችና ከዛም ውጭ የታመመ ብሄረተኛነታቸውን መታክም ላልቻሉ አንዳንድ ልሂቃን “አማራው የሚያደርገው ትግል ለጨፍላቂነት ነው” የሚል ክስ ማዥጎድጎድ የጀመሩት ለዚህ ነው።
• ይህ ክሳቸው አድማጭ እንዲያገኝ ራሳቸው ከሚናገሩት አልፈው የውስጥ አዋቂዎች ናቸው በሚል፣ ይህን ክስ የሚያቀርቡ ባንዳ የአማራ ምሁራን ቀጥረዋል። በቅርቡ ዳኛቸው አሰፋ በአንድ ሚድያ ላይ ቀርቦ የአማራን ትግል የጨፍላቂዎች፣ ሌላውን ህዝብ በንቀት የሚያዩ ስብስቦች ትግል ነው ብሎ ማቅረቡን ልብ ይሏል። እነዚህ የታመሙ ብሄረተኞች ያለ የሌለ ሃይላቸውን ተጠቅመው አማራን ወደከፋ የህልውና አደጋ ውስጥ ለመክተት የሚያደርጉት ጥረት ከዚህ ስጋት የመነጨ ነው።
• የአማራ የህልውና ትግል የፈጠረው ወታደራዊና ፖለቲካዊ ጥንካሬ ከዚህ በፊት “ይህ ጥንካሬ ያለን እኛ ብቻ ነን” በሚል የታበዬ ብሄረተኛነት ተላብሰው ይኖሩ የነበሩትን አክራሪ ብሄረተኞችን አስበውት የማያውቁት ጉዳይ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል። ቢመቱት መልሶ መምታት ብቻ ሳይሆን መደምሰስም የሚያስችል እመቅ ጉልበት ያለው የአማራ ብሄረተኛነት እየመጣ እንደሆነ ልብ ማለት ጀምረዋል። አንዳንዶቹን ሌላው ቢቀር ይህን አዲስ ክስተት ግምት ውስጥ ያስገባ የአቋም መስተካክል/ሽግሽግ እንዲያደርጉ እያስገደዳቸው እንደሆነ በተጨባጭ እያየነው ያለ ሃቅ ነው። ይህ ነውር አይደለም። ፖለቲካ ማለትም ይህ ነው። ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የመቀራረብና የጋራ ችግሮችን በጋር ውይይትና ድርድር የመፍታት ፍላጎት የሌላቸው አክራሪ ብሄረተኞች ከአማራ ጋር ያለን ልዩነት በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት እንፈታለን ወደሚል አቋም ያመጣቸው የህልወና ትግሉ ያደገበት ወታደራዊና ፖለቲካዊ ፍጥነት ነው።
• ይህ የአቋም መሸጋሸግ እንዳለም ሆኖ ጤነኛ ብሄረተኛነትን እና የታመመ ብሄረተኛነት በሚያስተናግዱ አካላት መሃከል በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ልዩነት በሰላማዊ መንገድ፣ በድርድር፣ ሰጥቶ በመቀበል ሊፈታ የሚችልበት እድል አሁንም ጠባብ ነው። ስር በስደደ የአማራ ህዝብ ጥላቻ ላይ ተኮትኩቶ ያደገ ብሄረተኛነት፣ አሁንም ቅጥ ያጡ፣ ለሰጥቶ መቀበል መንገድ የማይከፍቱ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም አንድነት ልማት ማምጣት የማያስችሉ ጥያቄዎች በማቅረብ ችግሮችን በድርድር የመፍታት ሂደቱን ሊያጨንግፈው ይችላል። በእንዲህ አይነቱ ሁኔታ በጤነኛ በታመመ ብሄረተኞች መሃከል ያለው ልዩነት የሚፈታው ብዙ ውድመትና እልቂት በሚያስተናግድ ግፍጫ ሊሆን ይችላል። ይህን ትንበያ “የሰይጣን ጆሮ አይስማው” ብሎ ደፋፍኖ ማለፉ ለማንም አይበጅም። ይህ ግፍጫ አንዱን አሸናፊ ሌላውን ተሸናፊ በማድረግ ላይጠቃለል ይችላል። መጨረሻው የሁሉንም የጋራ ውድመት አስከትሎ የሁሉንም ህዝብ ህይወት ወገሃነብነት ሊቀረው ይችላል።
• ይህ እንዳለ ሆኖ በዛሬይቱ ኢትይጵያ በጤነኛ እና በታመመ ብሄረተኛነት መሃከል ግፍጫ ቢነሳ አንድ ነጥብ ግልጽ ሆኖ ወጥቷል። ይህ ነጥብ የኢትዮጵያ ሁኔታ ከዚህ በኋላ በሽተኛ ብሄረተኛነት የበላይነቱ አስጠብቆ መቀጠል የሚችልበት እድሉ የጠበበ መሆኑ ነው። የቢሆንስ ትንተና የሚሰራ ንቁ የሁኔታዎች ታዛቢ የሚደርስበት መደምደሚያ ጤነኛውና የታመመው ብሄረተኛነቶች በሚያደርጉት የሞትና የሸረት ትንንቅ የታመመ ብሄረተኛነት በአሸናፊነት መውጣት እንደማይችል ነው።
• የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል ጤነኛ ብሄረተኛነት ለሚያራምዱ ሆኖም ግን አቅማቸው ደካማ ለነበሩ በርካታ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ማህበረስቦች የብርታት ምንጭ ሆኗቸዋል። የአማራ የህልውና ማስከበር ትግል በሁለቱ አይነት ብሄረተኞች መሃል የነበረውን የሃይል ሚዛን አዛብቶታል። የመሸናነፍ ነገር የሚወራ ከሆነ የሃይል ሚዛኑ አሰላለፍ የሚያሳየው ኢትዮጵያን ለሁላችንም የምትመች ሃገር እናድርጋት፣ በዘረኛነትና በተረኛነት ነዳጅ የሚነጉደው በሽተኛ ብሄረተኛነት ከኢትዮጵያ ሊርቅ ይገባዋል የሚለው ሃይል አሸናፊ እንደሚሆን ነው።
• ይህን በፍጥነት በመቀየር ላያ ያለን ሃገራዊ እወነታ አለመረዳት፣ ቀድሞውኑ በድንቁርና እና በጥላቻ የተመሰረተ ብሄረተኛነት ትክክለኛ አለመሆኑን አለመገንዘብ፣ ይህ የጥላቻ ብሄረተኛነት እስከ አሁንም በህዝብና በሃገር ላይ ያደርሰው አስከፊ ድቀት በጥሞና አለማጤን ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ይሆናል።
• ወቅቱ የሚጠይቀው አዲስ ግንዛቤ የአማራ የህልወና ትግል መጠንከር የፈጠረው ወታደራዊና ፖለቲካዊ ጥንካሬ ማደጉን በጥሞና ማጤን ብቻ አይደለም። መጀመሪያውኑ በአማራ ህዝብ ላይ ስሁት ትርክት ደርሶ፣ በዚህ ትርክት አማካይነት በተፈጠረ አሉታዊ አመለካከት የአንድ ህዝብ ብሄረተኛነት ለመቅረጽ ልሂቁ የሰራው ስራና የሄደበት እርቀት ትክክል ነበር ወይ የሚል ስር ነቀል የአመለካከት ለውጥ የሚጠይቅ ግንዛቤ ነው። በተለይ ደግሞ የአማራን እና የትግራይን ህዝብ ዝንተአለም ተቆራኝቶ የቀጠለ የጋራ ህልውና ታሪክ የሚያውቁ የትግራይ ልሂቃን ከምር እራሳቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል።ይህ ምልከታ ለትግራይ ልሂቃን በተለየ የሚሰራ ቢሆንም እኢትዮጵያ ውስጥ የዘመናት የህዝቦችን መስተጋብር በደንብ ለማይረዱ የኦሮሞም ልሂቃን የሚሰራ ነው።
ለሌሎችም አጋሩ!
