
ከ 8 ሰአት በፊት
የሱዳን ጦር ተቀናቃኙን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን በማሸነፍ በመዲናዋ ካርቱም ቁልፍ ቦታዎችን እንደገና መቆጣጠር ችሏል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና የተሰጠውን የሱዳን ጦር ከፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥቱ ማስወጣት ችሎ ነበር።
ጦሩ ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ በካርቱም ማዕከል የሚገኘውን ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት መልሶ ተቆጣጥረዋል።
ባለፈው ዓርብ በደስታ የተሞሉ የጦሩ ወታደሮች በውጊያው ጥይት በበሳሳው የፕሬዚዳንታዊ መንግሥት ደጃፍ ላይ ፎቶዎች ሲነሱ ታይተዋል።
የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የተከሰተው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በአገሪቱ በሚገኘው የጦሩ፣ ጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃትን እንዲሁም የመዲናዋን አየር ማረፊያን ጨምሮ፣ በርካታ ግዛቶች በአውሮፖውያኑ ሚያዝያ/ 2023 መቆጣጣሩን ተከትሎ ነው።
ደም አፋሳሹ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ህይወትን ከመቅጠፍ በተጨማሪ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ተገደዋል።
በአገሪቱ በረሃብ እና በቸነፈር በርካቶች መገረፋቸውን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለማችን የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንደሆነ ፈርጆታል።
ቢቢሲ በግጭቱ ወቀት በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የተጋሩ ቪዲዮዎችን እና ምስሎችን በማጥናት ጦሩ ካርቱምን መልሶ ለመቆጣጠር ያደረገውን ጉዞ ለመቃኘት ሞክሯል።
የካርቱም ከተማ አባይ ብለን በምንጠራው ወይም በሁለቱ ብሉ እና ዋይት ናይል የተከበበች ናት። ከተማዋ በዚህ መልክዓ ምድር መገኘቷም የጦሩን ጉዞ ፈታኝ አድርጎታል።
ጦሩ ከተማዋን እንደገና መልሶ ለመቆጣጠር በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በካርቱም ይዞታዎቹ ላይ መስከረም፣ 2017 ላይ ጥቃት ጀመረ።
ከዚያም ጥር ወር ላይ ከሌሎች ሚሊሻዎች ድጋፍ ያገኘው ጦሩ ሌሎች ስትራቴጂካዊ ድሎችን ማሳካት ችሏል።
ጥር 17- ከከበባ መውጣት
በማዕከላዊ ካርቱም የሚገኘው የጦሩ ዋና መቀመጫ ለ21 ወራት ያህል በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከበባ ውስጥ ገብቶ ነበር።
በስፍራው የነበሩ የጦሩ ወታደሮች ከሌሎች የጦሩ ክፍሎች ጋር እንዳይገናኙ እና ከተማዋም በከበባ ውስጥ ገብታ ነበር።
ከዚያም ጦሩ በሰሜን በኩል ያደረገውን ግስጋሴ ተከትሎ ጥር አጋማሽ ላይ ተጨማሪ ኃይል ለመላክ እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ከበባ መስበር ችሏል።
ጥር 17 ላይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የወጣ ቢቢሲ ማረጋገጥ የቻለው ቪዲዮ የጦሩ ወታደሮች በጦሩ ዋና መስሪያ ቤት ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

- መከላከያ ሠራዊት ጄነራል ምግበይ ኃይለ ላይ ያቀረበውን ክስ የትግራይ የሰላምና የጸጥታ ቢሮ “ኃላፊነት የጎደለው ነው” አለ24 መጋቢት 2025
- አስፈላጊ እየሆነ ስለመጣው ፋይዳ መታወቂያ ሊያውቋቸው የሚገቡ 8 ጉዳዮች24 መጋቢት 2025
- በአንድ ወቅት በሩሲያ ሥር የነበረው የአሜሪካ ደሴት24 መጋቢት 2025
በማግሥቱ የጦሩ አዛዥ ጄነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን የሰራዊታቸውን ዋና መስሪያ ቤት ጎብኝተው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን “ድምጥማጡን ለማጥፋት” እስከ አገሪቱ ጥግ እንደሚያሳድዷቸው ተናግረዋል።
ጥር 28- 29- የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን መውጫ መዝጋት
ፍልሚያው መጠናከሩን እና በያዟቸው ግዛት ላይ የውጊያው ጫና የጠነከረባቸው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከዋይት ናይል ወጥተው ወደ ምዕራባዊ ግዛት ለመሄድ ሞክረዋል።
ሆኖም በወንዙ መሸጋገሪያ ዋነኛ ድልድይ ላይ ጦሩ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ማምለጫ መስመራቸው ተዘጋ።
ጥር 29 ላይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የወጣ ቪዲዮ ከካርቱም 40 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ጀበል አውሊያ የተሰኘው መሸጋገሪያ በከፋ በተጎዱ መኪኖች ተዘግተው አሳይቷል። በስፍራው ጥቁር ጭስ ሲወጣም ይሄው ቪዲዮ ያሳያል።

ከዚያ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ጦሩ ጥቃት መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን በዚያን ወቅት የወጣ የሳተላይት ምስል ጥቁር ጭስ አሳይቷል።
የካቲት 24 -ቁልፍ ድልድይ መቆጣጠር
ወደ ካርቱም የተቃረቡ የጦሩ ወታደሮች በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የሚገኘውንና የመጨረሻውን ዋነኛ መሻገሪያ የሆነውን የማንሺያ ድልድይ ለመቆጣጠር ሞከሩ።
የካቲት 24 ድልድዪን ለመቆጣጠር የተደረውን ውጊያ የሚያሳይ የድሮን ቪዲዮ ጦሩ ለቀቀ።
በዚህ ቪዲዮ ላይ ጦሩ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ተሽካርካሪዎችን ሲያጠቁ እና የኃይሉ ወታደሮች ለመሸሽ ሲሞክሩ ማየት ይቻላል።
በድልድዪ ላይ ጥቃት ሲደርስ አንዳንድ ሰዎችን የጫነ ጭነት መኪና እንዲሁም ከጎኑ አብረውት የሚሮጡ ሰዎች በእሳት ወደላይ ሲነሱ ይታያል።

በቀጣዮቹ ቀናት ጦሩ በድልድዩ ላይ ያሉ ስፍራዎችን በመቆጣጠር በአካባቢው መውጫ ያጡ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎችን ለመክበብ ችሏል።
መጋቢት 7- የጦሩ ግስገሳ ወደ ማዕከላዊ ካርቱም
የጦሩ ወታደሮች ወደ ማዕከላዊ ካርቱም በሚያደርጉት ግስገሳ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በደፈጣ ውጊያ ሲያጠቋቸው የሚያሳይ ቪዲዮ መጋቢት 7 ወጥቷል።
በፍጥነት እየነዳ ያለ ሞተር ሳይክል በተኩስ እሩምታ ተመትቶ ሲገለበጥ እና አሽካርካሪውን አየር ላይ ሲወረውረው ያሳያል።
የተኩስ እሩምታውን የከፈቱት የጦር ሰራዊቱ አባላት ባደረሱት ጥቃት እንኳን ደስ አላችሁ ሲባባሉ በቪዲዮው ላይ ይሰማሉ።

በቪዲዮዎቹ ላይ የምንመለከታቸው ህንጻዎች እና ዛፎችን ከሳተላይት ምስሎች ጋር በማዛመድ ይህ ስፍራ ከፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት 2 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ መሆኑን ቢቢሲ አረጋግጧል።
መጋቢት 11-የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት መልሶ መቆጣጠር
የጦር ሰራዊቱ በፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ የሚገኘውን አል ቃስር ጎዳና ላይ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ሲያደርስ የሚያሳይ ቪዲዮ መጋቢት 11 ወጥቷል።
ቪዲዮው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ የሚያሳይ ሲሆን በተመሳሳይም በርካታ ፍንዳታዎች ከእሳቱ ተሰምቷል።
አረብኛ ቋንቋ በሚሰማበት በዚህ ቪዲዮ ላይ ጥቃቱ መሳሪያ በጫኑ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መኪኖች ላይ የተፈጸመ እንደሆነ ይገልጻል።
ቢቢሲ በቪዲዮው ላይ የሚታዩ ሁለት ህንጻዎችን በጉግል ካርታዎች (ጉግል ማፕስ) ጋር በማመሳሰል ስፍራው ከፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት 1 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሆኑን አመላክቷል።

ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በደስታ የተሞሉ የሱዳን ጦር ወታደሮች እጆቻቸውን በድል አድራጊነት ከፍ አድርገው በቤተ መንግሥቱ ፊት ለፊት ፎቶ እየተነሱ ነበር።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አሁንም ጉልህ የሆኑ የከተማዋን ስፍራዎች እና የምዕራባዊ ሱዳን ሰፊ ቦታዎችን ተቆጣጥሯል። ነገር ግን ጦሩ ቤተ መንግሥቱን መቆጣጠሩ በጦርነቱ ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነ ተቆጥሯል።