ኢቫን እና ማርያ

ከ 6 ሰአት በፊት

ማርያ ቀኖቿን የምታሳልፈው የስልክ ጥሪ በመጠበቅ ነው። ባለቤቷ ኢቫን የዩክሬን የጦር አውሮፕላን አብራሪ ነው።

ኢቫን ምን ክፉ ገጥሞት ይሆን ብላ የስልክ ጥሪ ትጠባበቃለች።

የ31 ዓመቱ ኢቫን ከ2022 ጀምሮ ሚግ-29 የጦር አውሮፕላን ያበራል። ከ200 በላይ ተልዕኮ ተወጥቷል።

በጦርነቱ ብዙ ጓዶቹን አጥቷል። ከሞቱት መካከል የልጆቹ የክርስትና አባት ይገኝበታል።

አሜሪካ በዩክሬን እና ሩስያ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እያደረገች ያለችው ጥረት በኢቫን እና ማርያ ሕይወት ትልቅ ለውጥ ያመጣል።

“የተኩስ አቁም ከተደረሰ ሰላም እንሆናለን” ትላለች ማርያ።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አውዳሚ የሆነው የአውሮፓ ጦርነት እንዲቆም ዩክሬናውያን ይፈልጋሉ።

ሩስያ ጥቃት እንደማትፈጽም ማረጋገጫ ማግኘትም ይሻሉ።

የ29 ዓመቷ ማርያ የተኩስ አቁም ለዩክሬን ሽንፈት ይሆናል ብላ ትሰጋለች። በሩስያ የተያዙ ግዛቶች አለመለቃቀቸውን ታስባለች።

“ጀግኖቻቸን ሕይወታቸውን ያጡትና መስዋዕትነት የከፈሉት ለምድን ነው ታዲያ?” ትላለች።

ጥንዶቹ ሲተዋወቁ ሩስያ ወረራ ታደርጋለች ብሎ ያሰበ አልነበረም።

ማርያ እንግሊዘኛ መምህር ነበረች። የኢቫን ጓደኛ ልጅ የምትማርበት ትምህርት ቤት ስለምታስተምር ተዋወቁ።

መጀመሪያ የተገናኙ ቀን ኢቫን ሥራው አደገኛ እንደሆነ ለማርያ ነገራት። እሷ ግን አላስጨነቃትም። ታማኝና ደግ መሆኑ እንድትወደው አድርጓታል።

ብዙም ሳይቆይ ለአንድ ዓመት ተልዕኮ ተሰጠው። ሳይገናኙ ስለቆዩ የሚለያዩ መስሏቸው ነበር።

ግን ከዓመት በኋላ ተጋቡ። ጦርነቱ ሲነሳ ሁሉም ነገር ተለወጠ።

ልጃቸው ያሮስላቫ የተወለደችበት ወቅት ነበር።

ኢቫን በጦርነቱ ምክንያት ልጁ ዳዴ ስትል፣ ጥርስ ስታበቅል አጠገቧ አልነበረም።

“በሺዎች የሚቆጠሩ ፎቶዎች እልክለታለሁ። ከኛ ጋር እንዳለ እንዲሰማው ነው” ትላለች ማርያ።

በቤታቸው ቅርብ ርቀት ተልዕኮ ሲኖረው ለአምስት ደቂቃም ሮጣ ሄዳ ታገኘዋለች። ምግብ ታደርስለታለች።

እያንዳንዱ ደቂቃ ዋጋ አለው።

ኢቫን

ልጃቸው መናገር ሳትጀምር ወደ ሰማይ እየጠቆመች አባቷ አውሮፕላን እንደሚያበር ታሳይ ነበር።

“ልጃችን አባቷ ፓይለት እንደሆነ ታውቃለች። ልደቷ ሲሆን በቪድዮ ደውለንለት አብሮን ኬክ ይበላል። ዩክሬንን ከሩስያ እየተከላከለ እንደሆነ እንነግራታለን” ትላለች ማርያ።

በየስድስት ወሩ የቤተሰብ ፎቶ ይነሳሉ።

“እውነቱን ለመናገር ለመጨረሻ የምንገናኘው መቼ እንደሆነ አለማወቄ ይረብሸኛል። ሁሌም ስንደዋወል የመጨረሻችን ነው ብዬ እፈራለሁ” ስትል ስሜቷን ትገልጻለች።

ራሷን ለከፋ ነገርም ሳይቀር ታዘጋጅ ነበር።

በጦርነቱ የመጀመሪያው ዓመት የወታደሮች ባለቤቶች መረጃ ይለዋወጡ ነበር።

ዩክሬናውያን አሜሪካ እና አውሮፓ ሩስያ ጥቃት መልሳ እንደማትጀምር ማረጋገጫ እንዲሰጧቸው ይፈልጋሉ።

በኢቫን እና ልጁ

ማርያ የተኩስ አቁም “ግጭቱን ይገታዋል” ትላለች።

አሜሪካ እና ፈረንሳይ ኤፍ-16 የጦር ጀት ለዩክሬን ለግሰዋል። ዩክሬን በሶቭየት ዘመን አውሮፕላኖች ነበር ስትዋጋ የነበረው።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያን ለዩክሬን የጦር ድጋፍና ወታደራዊ መረጃ መስጠት እንዲያቆሙ ይፈልጋሉ።

ተንታኞች ይሄ የፑቲን ጥያቄ ጦርነቱን ለመቀጠል ከመፈለግ የመጣ ነው ብለው ይሰጋሉ።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከመጋረጃ በስተጀርባ ከፑቲን ጋር ስምምነት ላይ ደርሰዋል ተብሎም ይገመታል።

የዩክሬን ጦር ኃይል ለመጪው ዓመታት በተጠንቀቅ መጠበቁ አይቀርም። ማርያም ይሄንን ታውቃለች።

በዩክሬን ሰላም ቢኖርም ባለቤቷ ሰላም እንደማያገኝ ትናገራለች።

በጦርነቱ ልቡ መሰበሩን ትገልጻለች። የጓዶቹ ሞት ትርጉም አልባ ሆኖ እንዲሰማው አትሻም።

በሩስያ የተያዙት የዩክሬን ግዛቶች አንድ ቀን እንደሚመለሱ ተስፋ ታደርጋለች።

በአገራቸው ሕይወታቸውን ዳግም እንደሚገነቡ ታምናለች።

“ሁሌም እንደምንጠብቀው ባለቤቴ እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ” ትላለች።