
ከ 6 ሰአት በፊት
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን በአገሪቱ እየተካሄደ የሚገኘውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለስድስተኛ ምሽት መቀጠሉን ተከትሎ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን “የአመፅ እንቅስቃሴ” በመቀስቀስ ተጠያቂ አደረጉ።
በኢስታንቡል አመጽ የተቀሰቀሰው የኤርዶዋን ዋነኛ ተቀናቃኝ የሆኑት የተቃዋሚ ፓርቲ አባል እና የከተማዋ ከንቲባ ኤክሬም ኢማሞግሉ ባለፈው ረቡዕ በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ነው።
የሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ (CHP) አባል የሆኑት ኤክሬም ኢማሞግሉ ከቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ጠንካራ የፖለቲካ ተቀናቃኞች መካከል አንዱ ተደርገው ይቆጠራሉ።
የተቃዋሚ ፖለቲከኛውን እስር የተቃወሙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሰኞ ዕለት ዳግም አደባባይ ለተቃውሞ ተሰብስበዋል።
እሁድ ምሽት የነበረው አመጽ ተባብሶ አስለቃሽ ጭስ እና ጥይት ተተኩሶ ነበር።
ኢማሞግሉ ከከንቲባነታቸው የታገዱ ሲሆን፣የቀረበባቸው ውንጀላ ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው ቢሉም፣ ኤርዶዋን በበኩላቸው ይህንን አስተባብለዋል።
ሰኞ ማምሻውን በኢስታንቡል ከተማ ማዘጋጃ ቤት አካባቢ የቱርክን ባንዲራ በመያዝ መፈክር እያሰሙ የነበሩ በርካታ የተቃውሞ ሠልፈኞችን የሚጠብቁ የአድማ በታኝ ፖሊሶች ተገኝተው ነበር።
ምንም እንኳ ሰኞ ዕለት የነበረው የተቃውሞ ሠልፍ በአንጻሩ ሰላማዊ የነበረ ቢሆንም፣ እሁድ ዕለት የታየው ከባድ ግጭት እንዳይደገም የሰጋው የከተማዋ ፖሊስ አድማ መበተኛ ውሃ የጫኑ መኪኖችን አሰማርቶ ታይቷል።
ከሰኞ ምሽት ስብሰባዎች በፊት በወጡ አሃዞች የቱርክ መንግሥት ተቃውሞው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 1,133 ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉ ተገልጿል።
ኤርዶዋን ቀደም ሲል በቴሌቭዥን በተላለፈው መግለጫቸው ሰልፎቹን “ክፉ” በማለት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን “የዜጎቻችንን ሰላም ቅስቀሳ በማድረግ አደፍርሰዋል” ሲሉ ወቅሰዋል።
ከቱርክ ዋና ከተማ አንካራ መግለጫቸውን የሰጡት ፕሬዝዳንቱ የተቃውሞ ሰልፎች እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበው፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “ለቀረበባቸው ውንጀላ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ. . . በፖለቲካ ታሪካችን ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ . . . [ባለፉት] አምስት ቀናት ውስጥ እጅግ በጣም ጸያፍ እና ሕገወጥ መግለጫዎችን ሰጥተዋል” ብለዋል።
- የቱርኩ ፕሬዝዳንት ዋነኛ ተቀናቃኝ ፕሬዚደንታዊ እጩ ከመሆናቸው ከቀናት በፊት ታሰሩ19 መጋቢት 2025
- የቱርኩ ፕሬዝደንት ተቀናቃኛቸውን ማሰራቸውን ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ ተፋፋመ24 መጋቢት 2025
- ለ43 ዓመታት አድማጮቹን ያገለገለው እና በድንገት በትራምፕ ውሳኔ የተዘጋው ቪኦኤ አማርኛከ 8 ሰአት በፊት
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
የሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ (CHP) ሊቀመንበር ኦዝጉር ኦዚል ሰኞ ምሽት ሺህዎች በተሰበሰቡበት ባደረጉት ንግግር የተቃውሞ ሠልፉ “ፋሲሽዝም ላይ የሚደረግ ተቃውሞ ነው” ብለዋል።
ኦዜል ማክሰኞ በሲሊቪሪ እስር ቤት የሚገኙትን ኢማሞግሉን እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።
አክለውም የፍርድ ሂደቱ እንዲቋረጥ እና እንዲለቀቁ እንደሚጠይቁ እንዲሁም የፍርድ ሂደቱ በቀጥታ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን በሆነው ቲአርቲ ( TRT) እንዲተላለፍ አቤት እንደሚሉ ተናግረዋል።
በእስር ላይ የሚገኙት ኢማሞግሉ ሰኞ እለት በ2028 ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካን ሕዝቦች ፓርቲ (CHP) እጩ ሆነው ተመርጠዋል።
እጩ ሆነው እንዲቀርቡ የተሰጣቸው ድምጽ ፓርቲያቸውን ወክለው የሚሳተፉት ብቸኛው ሰው መሆናቸውን ያረጋገጠ ሲሆን ተምሳሌታዊም ተብሏል።
እሁድ ዕለትን በእስር ቤት ያሳለፉት የተቃዋሚ ፖለቲከኛው እና ፕሬዝዳንታዊ እጩው በዕለቱ “ወንጀለኛ ድርጅት በማቋቋምና በማስተዳደር፣ጉቦ በመቀበል፣ በመዝረፍ፣ የግል መረጃዎችን በሕገወጥ መንገድ በማዘጋጀት እና እና ጨረታ በማጭበርበር” የሚል ክስ በይፋ ቀርቦባቸዋል።
ኢማሞግሉ በሳምንቱ መጨረሻ በኤክስ ገጻቸው ላይ በለጠፉት ጽሑፍ “በፍፁም አልሸነፍም” በማለት መታሰራቸውን “በዲሞክራሲያችን ላይ ጥቁር ነጥብ” ሲሉ ገልጸውታል።
ለተቃውሞ ሰልፈኞቹም ያላቸውን ስሜት ያጋሩት ፖለቲከኛው መራጮች ቱርካውያን ኤርዶዋን “እንደበቋት” አሳይተዋል ብለዋል ።
ለተከታታይ ቀናት እየተካሄደ ያለው የተቃውሞ ሰልፍ በ2013 የሕዝብ መናፈሻን መፍረስ ተከትሎ ከተደረገው የጌዚ ተቃውሞ በኋላ በቱርክ ከታዩ ሰልፎችሁሉ ትልቁ ነው ተብሏል።
የኢማሞግሉ የትዳር አጋር ዲሌክ ካያ፣ ከኢስታንቡል ከተማ ማዘጋጃ ቤት ውጭ በመገኘት ባለቤታቸው ያጋጠመውን “ግፍ” ለሰላማዊ ሰልፈኞች ዘርዝረው አስረድተዋል።
ኢማሞግሉ ባለፈው ሳምንት መንግሥት ከሙስና ጋር በተያያዘ ምርመራ አድርጎ ካሰራቸው ከ100 በላይ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።
ከታሰሩት ውስጥ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና ነጋዴዎች ይገኙበታል።
የፖለቲከኛው መታሰር በፕሬዚዳንትነት ከመወዳደር ወይም ከመመረጥ አያግዳቸውም።
ነገር ግን በተከሰሱበት በማንኛውም ወንጀል ከተፈረደባቸው መወዳደር አይችሉም።
በእስር ላይ የሚገኙት ፖለቲከኛው በቱርክ ውስጥ ለ22 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር እና በፕሬዝዳንትነት ስልጣን ከያዙት የኤርዶዋን እጅግ ተቀናቃኞች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ናቸው ተብሎ ይታሰባል።
ሆኖም ኤርዶዋን ሕገመንግሥት እስካልተሻሻለ ድረስ ዳግመኛ በ2028 ምርጫ ላይ መወዳደር አይችሉም።
የቱርክ የፍትህ ሚኒስቴር ኤርዶዋንን ከእስር ጋር የሚያገናኙትን በመተቸት በአገሪቱ የፍትህ ነጻነት መኖሩን አጽንኦት በመስጠት ተናግሯል።