የዩኤንኤድስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዊኒ ቢያኒማ

ከ 6 ሰአት በፊት

የአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ መቋረጡ በየቀኑ ተጨማሪ 2,000 አዳዲስ በኤችአይቪ የሚያዙ ሰዎች እንዲኖሩ እና በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንዲሞቱ ያደርጋል ሲሉ የዩኤንኤድስ ኃላፊ አስጠነቀቁ።

እአአ በ2004 በኤች አይቪ ኤድስ ይሞቱ የነበሩ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቁጥር በ2023 ወደ 600,000 መቀነስ ተችሎ የነበረ ቢሆንም፣ የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ ግን ኤችአይቪን በመከላከል ረገድ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት ይቀለብሳል ተብሏል።

የዩኤንኤድስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዊኒ ቢያኒማ የአሜሪካ መንግሥት ለኤችአይቪ ፕሮግራሞች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ፣ የውጭ እርዳታን ለማቆም መወሰኑ ከወዲሁ አስከፊ መዘዝ እያስከተለ ነው ብለዋል።

በተለይ ሴቶች እና ልጃገረዶች ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን በማስጠንቀቅ አሜሪካ ድጋፍ የማቋረጥ ውሳኔዋን በአስቸኳይ እንድትቀይር ጠይቀዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጥር ወር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት የመንግሥትን ወጪ ለመከለስ በሚል ለ90 ቀን ያህል አገራቸው የምትሰጠውን እርዳታ ማቋረጣቸውን አስታውቀዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አብዛኛው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) ፕሮግራሞች ተቋርጠዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው የኤችአይቪ ሕክምና እና መከላከል መርሃ ግብሮች በመቋረጣቸው የተነሳ፣ በአፍሪካ ውስጥ የእናቶች እና የሕፃናት ክሊኒኮች እንዲዘጉ ተደርጓል፤ ሕይወት አድን የሆኑት የፀረ-ኤችአይቪ መድሃኒቶች (ARV) ላይም እጥረት ተፈጥሯል።

ቢያኒማ የፀረ ኤችአይቪ መድሃኒቶች በድሃ አገራት እምብዛም ወደ ማይገኙበት፣ኢንፌክሽኖች እና ሞት እየጨመሩ ወደ ነበረበት 1990ዎቹ እንዳይመለስ መስጋታቸውን ተናግረዋል።

አሜሪካ ለዓመታት የኤችአይቪ ሕክምና እና መከላከል ላይ ብቸኛዋ የገንዘብ ድጋፍ ሰጪ አገር የነበረች ሲሆን፣ ቢያኒማ ዋሽንግተንን ላሳየችው ልግስና እና ሰብዓዊነት አመስግነዋል።

አክለውም አሜሪካ “በጊዜ ሂደት የምታደርገውን ድጋፍ ለመቀነስ መፈለጓ ምክንያታዊ ነው” ነገር ግን “የሕይወት አድን ድጋፍ በድንገት ማቋረጥ ከባድ ተጽዕኖ ያሳድራል” ብለዋል።

እስካሁን ድረስ ዋሽንግተን ውሳኔዋን እንድትቀይር የሚቀርቡላትን ተማጽኖዎች እየሰማች እንደሆነ የሚያሳይ ምንም ምልክት የለም።

በአውሮፓ የሚገኙ ለጋሽ አገራትም የገንዘብ ድጋፍን ለመቀነስ ያቀዱ ሲሆን፣ ኤችአይቪን መከላከል ላይ የሚሰራው የተባበሩት መንግሥታት የጋራ ኤጀንሲ (ዩኤንኤድስ) ሌሎች አገሮች በአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ምንም ዓይነት ፍንጭ አለማሳየታቸውን ገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ቢያኒማ ሰኞ ዕለት በጄኔቫ ንግግር ሲያደርጉ በኬንያ ኤችአይቪ በደሟ የሚገኘውን የጁሊያናን ታሪክ ጠቅሰው ከአሜሪካ መንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ እናቶች ልጆቻቸው በበሽታ እንዳይያዙ ለመከላከል የምትሰራውን ሥራ አቅርበዋል።

አሜሪካ የምታደርገው ድጋፍ ከተቋረጠ ጁሊያና ሥራዋን ማጣት ብቻ ሳይሆን፣ ጡት የሚጠባው ልጇ ሕክምናውን በማጣት ምክንያት ለአደጋ ሊጋለጥ ይችላል ስትል እንደምትሰጋ ቢያኒማ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ናይጄሪያ፣ኬንያ፣ሌሴቶ፣ደቡብ ሱዳን፣ቡርኪናፋሶ፣ማሊ፣ሄይቲ እና ዩክሬን የአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ ካቆመ በቅርቡ የኤችአይቪ መድሃኒት ሊጨርሱ እንደሚችሉ ተናግሯል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም የኤችአይቪ ፕሮግራሞች መስተጓጎል “የ20 ዓመታት እድገትን ሊቀለበስ ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በየካቲት ወር፣ በደቡብ አፍሪካ ኤች አይቪ መከላከል ላይ በግንባር ቀደምትነት የሚሰራው ቡድን፣ ትሪትመንት አክሽን ካምፔይን (TAC)፣ የኤች አይ ቪ ታማሚዎች ለሕክምናቸው አስፈላጊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ሲታገሉ አገሪቱ ወደነበረችበት ልትመለስ እንደምትችል አስጠንቅቋል።

የቲኤሲ ሊቀ መንበር ሲቦንጊሌ ቻባላላ “መሞት አንችልም፣ በአገልግሎት ተደራሽነት ስንሰቃይ ወደ ነበረንባቸው ዓመታት መመለስ አንችልም፤በይበልጥ ደግሞ ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ግለሰቦች” ብለዋል ።

ቢያኒማ ለትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ ያመረተቻቸውን የጸረ ኤች አይቪ መድሃኒቶች ለመሸጥ የሚያስችል ምክረ ሃሰብ አቅርበዋል።

በጊልያድ የአሜሪካ ኩባንያ የተሰራው ሌናካፓቪ (Lenacapavi) በየስድስት ወሩ በመርፌ የሚሰጥ ሲሆን ዩኤንኤድስ 10 ሚሊዮን ሰዎች ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ያምናሉ።

ከእንደዚህ አይነት ስምምነት የሚገኘው ትርፍ እና ሥራ ለአሜሪካ በጣም ጠቃሚ ይሆናል ሲሉ ቢያኒማ አክለው ገልጸዋል።

ዩኤንኤድስ የገንዘብ ቅነሳ ከሚደርስባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች አንዱ ነው።

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ 6,000 ያህል ሥራ ሊያጣ እንደሚችል ሲገልጽ፣ ዩኒሴፍ በበኩሉ የሕጻናትን ሞት መቀነስ ላይ የታየው መሻሻል ስጋት ላይ መውደቁን ገልጿል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በረሃብ ስጋት ውስጥ ባሉ ክልሎች የሚሰጠውን ድጋፍ (ራሽን ) መቀነሱን አስታውቋል።