የአሜሪካ ባንዲራ፣ ዶናልድ ትራምፕ እና የቪኦኤ አማርኛ አርማ
የምስሉ መግለጫ,ለአርባ ሦስት ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ ሕይወት፣ ጥበብ በቅርበት የዘገበው፣ በአሜሪካውያን ግብር ከፋዮች ገንዘብ የተቋቋመው ቪኦኤ በዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ ከተቋረጠ አንድ ሳምንት አልፎታል።

ከ 7 ሰአት በፊት

አርብ፣ መጋቢት 6/ 2017 ዓ.ም ለቪኦኤ አማርኛ መደበኛ የስርጭት ቀን ነበር።

ጋዜጠኞቹ የተለመደውን የ30 ደቂቃ ዝግጅቶቻቸውን አቅርበው ሲሰነባበቱ፣ ቅዳሜ ምን እንደሚተላለፍ ተነጋግረው እና የሥራ ድርሻ ተከፋፍለው ነው።

ቅዳሜ ዕለት ግን ቪኦኤ አማርኛን ጨምሮ 1300 የቪኦኤ ሠራተኞች የግዳጅ እረፍት እንዲወጡ የሚገልጽ የኢሜል መልዕክት ደረሳቸው።

የሬዲዮ ጣብያው ከተመሰረተበት እአአ 1982 ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ፀጥ ረጭ አለ።

የሬዲዮ ጣብያው የኮንትራት ሠራተኞች ቅጥራቸው ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ።

ቋሚ ሠራተኞቹ ዕጣ ፈንታቸው እስኪወሰን ድረስ የግዳጅ እረፍት ላይ እንዲቆዩ ተወሰነ።

በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ወሳኝ ምዕራፎች ላይ እማኝ በመሆን ለ43 ዓመታት በስርጭት ላይ የቆየው ቪኦኤ አማርኛ ልሳኑ ተዘጋ።

ለአርባ ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ ሕይወት፣ ጥበብ በቅርበት የዘገበው፣ በአሜሪካውያን ግብር ከፋዮች ገንዘብ የተቋቋመው ቪኦኤ በዶናልድ ትራምፕ ቀጭን ትዕዛዝ ተቋረጠ።

ይህ እንደ መረጃ ምንጭ ለሚያዩት አድማጮቹ፣ ለበርካታ ሠራተኞቹ፣ የኢትዮጵያን መገናኛ ብዙኃን ለሚከታተሉ ሁሉ አስደንጋጭ ዜና ነበር።

ቪኦኤ አማርኛን ለመሠረቱት እና ለ40 ዓመት ላገለገሉት አንጋፋው ጋዜጠኛ ንጉሤ መንገሻ ደግሞ “ልብ ሰባሪ ዜና” ነው።

ቪኦኤ በአጭር ይቀጫል ብለው አስበው እንደማያውቁ የሚናገሩት አቶ ንጉሤ “ቮይስ ኦፍ አሜሪካ ተዘግቷል የሚለው ዜና ለእኔ ዱብ እዳ ነው የሆነብኝ። በጣም ነው የደነገጥኩት” ብለዋል።

አቶ ንጉሤ የበጀት ቅነሳ ለውጥ እንደሚመጣ ገምተው የነበረ ቢሆንም “ተዘግቷል ሲባል ግን በጣም፣ በጣም መጥፎ ስሜት ነው የሚሰማው። በጣም ነው ያዘንኩት፤ በጣም ነው ውስጤ ያረረው” ሲሉ ተናግረዋል።

“የጨለማ ጊዜ ነው የመጣው” የሚሉት አቶ ንጉሤ መንገሻ፣ በአጠቃላይ የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ (ቪኦኤ) 380 ሚሊዮን አድማጭ ነው ያለው። ከዚህ ውስጥ 180 ሚሊዮኑ አፍሪካ ውስጥ ነው ይላሉ።

“ዛሬ የሚደሰቱ ሠዎች ቢኖሩ አምባገነኖች ናቸው” ሲሉ ያክላሉ።

ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገው እና በመገናኛ ብዙኃን ላይ የተለያዩ የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን የሚሰራው እንዳልካቸው ኃይለ ሚካኤል (ዶ/ር) በበኩሉ፣ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የቪኦኤን እና ሌሎች የፌደራል ተቋማትን የመዝጋት ውሳኔ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለራሷ ለአሜሪካም “ትልቅ ጉዳት ያለው እና ‘ሪስፔክት’ [አክብሮት] የሚያሳጣት ጭምር ነው” ይላል።

ቪኦኤ አማርኛን የመሠረቱት እና ለ40 ዓመት ያገለገሉት አንጋፋው ጋዜጠኛ ንጉሤ መንገሻ በቢሯቸው ውስጥ
የምስሉ መግለጫ,በብዕር ስማቸው ጌታሁን ታምራት በመባል የሚታወቁት አንጋፋው ጋዜጠኛ ንጉሤ መንገሻ፣ ከአቶ ታምሩ ሀምፖ፣ ይኼይስ ውሂብ፣ አዳነች ፍስሀዬ፣ ዮሐንስ ኃይለ ኢየሱስ ጋር በመሆን እአአ በ1982 ቪኦኤ አማርኛን መስርተዋል።

በሳምንት ’12 ሚሊዮን የሚሆን ኢትዮጵያዊ የሚያዳምጠው’ ቪኦኤ

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ቪኦኤ አማርኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ስርጭት ሲጀምር መረጃ ከመንግሥት ቋት ብቻ ነበር የሚፈስሰው።

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሥልጣን ላይ በነበሩበት ሰዓት፣ ኢትዮጵያ በአንድ ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ በምትተዳደርበት በዚያ ወቅት፣ አሜሪካውያንን ከኢትዮጵያ ውስጥ ጠራርገው ባስወጡበት ጊዜ ነው ቪኦኤ አማርኛ ስርጭት የጀመረው።

ያኔ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጂሚ ካርተር ለፕሮፓጋንዳ በሚል ገንዘብ በመመደባቸው፣ ቪኦኤ በአማርኛ ቋንቋ ስርጭት ጀመረ።

በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ተመራማሪ የሆኑት አቶ እንዳልካቸው ኃይለ ሚካኤል ቪኦኤ አማርኛ እኤአ 1982 ሲቋቋም በወቅቱ አገር ውስጥ ነጻ የሆነ የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ያልነበረበት እንደነበር አስታውሰው “በጣም ብዙ ሰው ያዳምጠው የነበረው ሚዲያ ነው” ይላሉ።

በዚህ ሀሳብ የሚስማሙት አንጋፋው የቪኦኤ አማርኛ የቀድሞ ዋና አዘጋጅ ንጉሤ መንገሻ “የደርግ መንግሥት የአገሪቱን ፖለቲካ ሕዋ በሙሉ የተቆጣጠረበት ጊዜ ነበር። አንድ ዓይነት አስተሳሰብ፣ አንድ ዓይነት ቅኝት፣ አንድ ዓይነት የፖለቲካ ፍልስፍና. . . አገሪቱን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጣርበት ጊዜ ነበር። ከቀበሌ ጀምሮ እስከ አርሶ አደር ማኅበር የአገሪቱን ሕይወት የሚቆጣጠርበት ጊዜ ነበር።በዚያ ወቅት ነው አማርኛ አገልግሎቱ የተከፈተው” ይላሉ።

ቪኦኤ አማርኛ ስርጭት በጀመረበት ወቅት በኢትዮጵያ በተለያዩ ነፍጥ ባነገቡ ኃይሎች መካከል ውግያው ተጧጡፎ ነበር።

በዚህ ወቅት ሚዛናዊ መረጃ ማግኘት ብርቅ ነበር። መንግሥት በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን ከሚባለው ውጪ አማራጭ የመረጃ ምንጭ ውሱን ነበር።

ከእነዚህ መካከል አንዱ በመሆን የአየር ሞገዱን የተቀላቀለው ቪኦኤ አማርኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነት ማግኘቱን አቶ ንጉሤ ያስታውሳሉ።

“አገሪቱ ወስጥ ስላሉ አንገብጋቢ ሁኑኔታዎች፣ ስለ ረሃብ፣ ጦርነት፣ ስለ ደርግ መንግሥት ቁጥጥር እና አምባገነናዊነት፣ ስለ ስደተኞች እንዘግብ ነበር። ስንጀምር 30 ደቂቃ ብቻ ነበር የተሰጠን። ስድስት ወር አልፈጀም ወደ አንድ ሰዓት እንዲያድግ ተደረገ። ምክንያቱ ደግሞ በጣም አድማጭ በጉጉት ይጠብቀው ስለነበር ነው”

እንዳልካቸውም (ዶ/ር) ይህንኑ በመጥቀስ “የማይተካ ታሪካዊ አስተዋጽኦ ያደረገ ነው” ይላል።

“ላለፉት 40 ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የዘገበ፣ የሰነደ፣ በአሜሪካ ታክስ [ግብር] ከፋዮች የተቋቋመ ትልቅ ድርጅት ነው” ሲል ያክላል።

የቪኦኤ አማርኛ መስራች ከሆኑ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ንጉሤ “ለደርግ መውደቅ ቪኦኤ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ብዬ የማምን ሰው ነኝ። ምክንያቱም ደርግ የሚደብቀውን ነገር ያወጣ ነበር።” ይላሉ።

አቶ ንጉሤም ሆኑ እንዳልካቸው (ዶ/ር) ስለ ቪኦኤ ሲናገሩ የሚጠቀሙት ተመሳሳይ አገላለጽ “ሚዛናዊ እና ተዓማኒነት ያለው ዘገባ” ይሰራ እንደነበር ነው።

እንዳልካቸው (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ውስጥ የተዓማኒነት ችግር በስፋት እንደሚታይ ገልጾ፣ “አንድ ዜና ሲዘገብ ማን ነው የዘገበው የሚለው ጥያቄ ሁሌም አብሮ ይነሳል” ብሏል።

“. . . ቪኦኤ ላይ የተዘገበ ነገር እውነተኛነቱ ብዙ ጥያቄ ውስጥ አይገባም። ምናልባት ትንታኔው እና አተረጓጎሙ ላይ ልዩነት ቢኖርም ዘገባ ላይ ግን ቪኦኤ ላይ ከተዘገበ የተዓማኒነት ጥያቄ ብዙ የለም።”

አክሎም የቪኦኤ መዘጋት የመረጃ ስርጭት ችግር ይፈጥራል ብሎ እንደሚያምን በመግለጽ፣ አድማጮች የሰሙትን መረጃ ለማረጋገጥ የሚመጡ ነበሩ ይላል።

“በተለይ ደግሞ ከፖለቲካ ጋር የተነካኩ ነገሮችን የማመን ችግር ስላለበት ‘ቬሪፋይ’ ለማድረግ [ለማረጋገጥ] ቪኦኤን ይሰሙታል። አንደኛ በመጀመርያ ደረጃ የመረጃ ስርጭት ችግር ይገጥመናል ብዬ አስባለሁ። አንዱ ይህ ነው። ኢትዮጵያውያን አሁንም ድረስ የሚከታተሉት የሚዲያ ተቋም ነው። ትልቅ ጉዳት አለው።”

አቶ ንጉሤ ደጋግመው የቪኦኤ አማርኛ መዘጋት የሚያደርሰውን ጉዳት ሲናገሩ የአድማጮች ቁጥርን በመጥቀስ ነው።

“በነገራችን ላይ ቪኦኤ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ሰፊ የሆነ አድማጭ ያለው ነው። በአሁኑ ጊዜ እንኳ በመላው ዓለም 380 ሚሊዮን ሕዝብ ነው የሚያደምጠው።እኔ ከመልቀቄ በፊት 1/3ኛው አድማጭ ያለው አፍሪካ ውስጥ ነበር።

“እኔ በጡረታ በተገለልኩበት ወቅት፣ የዛሬ ሦስት ዓመት 12 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ በየሳምንቱ ያዳምጠው ነበር። በአማርኛ በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ ማለት ነው በድምሩ”

ባለፉት 15 ዓመታት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ሁሉም በራሱ አቅጣጫ ብቻ የሚተምበት መሆኑን እንዳልካቸው (ዶ/ር) ያነሳል።

እንደዚህ ቪኦኤ ያሉ የሚዲያ ተቋማት ግን ሁሉንም የፖለቲካ ማኅበረሰቦች፣ በብሔርም በሃይማኖትም የተደራጁትን ለማቀራረብ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው ሲልም ያክላል።

“በአማርኛ የሚዘገበው ፕሮግራም ወደ ኦሮምኛ ሲተረጎም አያለሁ። ወደ ትግርኛ ሲተረጎም አያለሁ። በተመሳሳይ በትግርኛ እና በአማርኛ የተሰሩ ፕሮግራሞች ወደ ኦሮምኛ ሲተረጎሙ አያለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ዘጋቢዎቻቸው ራሱ በኦሮምኛም በአማርኛም ሲሰሩ አስተውላለሁ። እና ይኼ በጣም የተከፋፈለውን የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለማቀራረብ የተሻለ የጋራ እውነት እንዲኖራቸው፣ አሁን የጋራ እውነት የምንለው ነገር እየጠፋ ስለመጣ፣ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ የነበረ ትልቅ ተቋም ነበር።”

አቶ ንጉሤ በቪኦኤ መዘጋት በሚሊዮን የሚቆጠረው አድማጭ ተጎድቷል ብለው እንደሚያስቡ ሲናገሩ፣ አቶ እንዳልካቸው በበኩሉ “የኢትዮጵያ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ቪኦኤ በመዘጋቱ ትልቅ ጉዳት ይደርስበታል” ይላል።

የትራምፕ እና የቪኦኤ ጠብ

ዶናልድ ትራምፕ ቪኦኤ ላይ ቂም የቋጠሩት አሁን አይደለም።

የመጀመርያው የሥልጣን ዘመናቸው ላይም ቪኦኤ በእርሳቸው እና በዙርያቸው ባሉ ሰዎች ጥርስ ውስጥ ገብቶ ነበር።

ያኔ የቪኦኤን ዘገባ በተደጋጋሚ የተቹት ፕሬዝዳንቱ በአንድ ወቅት “አስጸያፊ” ብለውት ነበር።

ከዚያም የቪኦኤ እናት ኩባንያ የሆነውን የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ኤጀንሲን (USAGM) እንዲመሩ ማይክል ኤል ፓክን ሾሙ።

ማይክል ፓክ ትራምፕን ይተቻሉ ያሏቸው ጋዜጠኞችን ማጥቃት በኢዲቶሪያል ጉዳዮች ጣልቃ መግባት ጀመሩ።

ጆ ባይደን የአሜሪካ ሕዝብን ድምጽ አግኝተው ወደ ኋይት ሐውስ ሲገቡ የመጀመርያ ያደረጉት ነገር እኚህን ግለሰብ በማንሳት የቀድሞዋን ኃላፊ፣ አማንዳ ቤኔትን በድጋሚ ሾሙ።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የናዚ ፕሮፖጋንዳን ለመገዳደር የተቋቋመው ቪኦኤ፣ በ50 የተለየዩ የዓለማችን ቋንቋዎች መረጃዎችን የሚያሰራጨው ቪኦኤ፣ በሳምንት ከ360 ሚሊዮን በላይ ሳምንታዊ አድማጮች ያሉት ቪኦኤ በትራምፕ አልተወደደም።

የፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ የቪኦኤ እናት ኩባንያ በሆነው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ኤጀንሲ ላይ ያነጣጠረ ነው።

ዩኤስ ኤጀንሲ ፎር ግሎባል ሚዲያ (US Agency for Global Media) ለትርፍ ያልተቋቋሙ እና ኮሚኒዝምን ለመከላከል የተመሰረቱ የሬዲዮ ጣቢያዎችንም በገንዘብ ይደግፋል።

ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸው ሲመረጡ በቪኦኤ ላይ ያላቸው አቋም አገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው ምስጢር ሆነ።

ይህንን የዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ በመደገፍ ኤለን መስክ በኤክስ ገጹ ላይ “ቪኦኤን ከዚህ በኋላ ማንም የሚያዳምጠው የለም” ሲል ለጠፈ።

ኋይት ሐውስ የትራምፕን ውሳኔ በተለመከተ “ግብር ከፋዮች ከዚህ በኋላ ለፕሮፖጋንዳ ገንዘብ አይከፍሉም” የሚል አስተያየት መግለጫ ሰጠ።

ትራምፕ ያስተላለፉት ውሳኔ በኮንግረሱ ድጋፍ ያገኘ ሲሆን ዩኤስ ኤጀንሲ ፎር ግሎባል ሚድያ የተባለውን ድርጅት ዒላማ ያደረገ ነው።

ይህ ኤጀንሲ ቪኦኤ፣ ራድዮ ፍሪ እስያ እና ራድዮ ፍሪ አውሮፓ የተባሉትን ጣቢያዎች ያስተዳድራል።

እነዚህ ጣቢያዎች የፕሬስ ነፃነት የላቸውም በሚባሉ ሥፍራዎች በሚሠሯቸው ዘገባዎች ይታወቃሉ።

ቻይና፣ ካምቦዲያ፣ ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ከእኒዚህ ሥፍራዎች መካከል ይመደባሉ።

የ ዩኤስኤጂኤም (USAGM) ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ካሪ ሌክ፣ ዶናልድ ትራምፕ ቪኦኤ እንዲዘጋ ያስተላልፉትን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ እንደሚደግፉ በገለፁበት ንግግራቸው በኤጀንሲው ውስጥ ብክነት፣ ማጭበርበር እንዲሁም ስልጣንን አላግባብ መጠቀም በሠፊው እንደሚታይ ገልጸዋል።

በዚሁ ንግግራቸው ላይ የኤጀንሲው ጥፋቶች ሲሉ ከዘረዘሯቸው መካከል ከፍተኛ የብሔራዊ ደህንነት ጥሰቶች፣ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው አላስፈላጊ ስምምነቶች እና ኮንትራቶችን መፈጸም ተጠቅሰዋል።

ኤጀንሲው ለሐሰተኛ ዜና ኩባንያዎች 100 ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በማውጣትም ተኮንኗል።

ካሪ ሌክ ይህንን ከዘረዘሩ በኋላ ኤጀንሲው ” ከላይ እስከ ታች በስብሷል፤ ለአሜሪካ ግብር ከፋይም ሸክም ነው። ኤጀንሲውን ማዳን አይቻልም ” ሲሉ ደምድመዋል።

ቪኦኤ እና በእናት ኩባንያው የሚደገፉ ጣቢያዎች 400 ሚሊዮን አድማጮችን እንደሚያገለግሉ መረጃዎች ያሳያሉ።

ቪኦኤ
የምስሉ መግለጫ,ቪኦኤ እና በእናት ኩባንያው የሚደገፉ ጣቢያዎች 400 ሚሊዮን አድማጮችን እንደሚያገለግሉ መረጃዎች ያሳያሉ።

29 ዓመት የሆናቸው የቪኦኤ ኦሮምኛ እና ትግርኛ አገልግሎቶች

ደርግ ከመንበሩ ወርዶ፣ ኢህአዴግ ስልጣን ሲረከብ ቪኦኤ የተሻለ ግንኙነት ይፈጠራል የሚል እምነት እንደነበረው አቶ ንጉሤ ይናገራሉ።

“የተሻለ የሚዲያ ሕዋ ይፈጠራል፣ እንደ ልባችን በነጻነት እንሰራለን የሚል ግምት ነበረን።”

ይህ የቪኦኤ አማርኛ ተስፋ ግን የሚሰምር አልሆነም። እንደ አቶ ንጉሤ ትውስታ ኢህአዴግ የሚያደርገው ቁጥጥር ጠበቀ።

የሬዲዮ ስርጭቶቹ ወደ አድማጭ እንዳይደርሱ ይታፈኑ “ጃም” ይደረጉ ጀመር።

ይኹን እንጂ ቪኦኤ አማርኛ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘጋቢ የኖረው በኢህአዴግ ስልጣን ዘመን ነው።

“በዚያ ወቅት አዲስ አበባ፣ መለስካቸው አምሃ እና እስክንድር ፍሬው ነበሩ ዘጋቢዎቻችን። መቀሌ አንድ ነበረን።”

የኢህአዴግ መንግሥት ቪኦኤ አማርኛን ለማዘጋት የተለያዩ ጥረቶች ማድረጉን አቶ ንጉሤ ያስታውሳሉ።

“ደጋፊዎቹ እዚህ ከተማ ውስጥ ‘ካምፔይን’ [ዘመቻ] ያደርጉ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስም ለሚያገኟቸው የአሜሪካ ባለስልጣናት እንዲዘጋ ይወተውቱ ነበር። አንድ ጊዜ ሁለት ሪፐብሊካን እና ዲሞክራቶች የኮንግረስ አባላት አማርኛው ይዘጋ ብለው ውሳኔ አሳልፈው ነበር”

የመንግሥት ውትወታ እና ዘመቻ ሲበረታ የቪኦኤ ኃላፊዎች ለምንድን ነው አማርኛው የሚዘጋው ብለው ጠየቁ።

ከመንግሥት በኩል ያገኙት መልስ ደግሞ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀይሟል” የሚል ሆነ።

ለምን ተቀየመ ሲባል ስርጭቱ በአማርኛ ቋንቋ ብቻ በመሆኑ የሚል ምላሽ ተገኘ።

መንግሥት ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚል ሃሳብ በማቅረቡ፣ የቪኦኤ ኃላፊዎች “እንደዚያማ ከሆነ ለምን ትግርኛ እና አፋን ኦሮሞ አይሆኑም” የሚል ሀሳብ አቀረቡ።

“እኔም ሆንኩ ሌሎች ሰርቪሱ [አገልግሎቱ] ላይ ያለን ሰዎች የእነዚህ ቋንቋዎች መጀመርማ እንደውም የአድማጭ ቁጥር ይጨምርልናል ብለን ነው የከፈትናቸው” ይላሉ አቶ ንጉሤ።

በዚህም የተነሳ ሐምሌ ወር 1996 ኦሮምኛ እና ትግርኛ ቋንቋዎች ስርጭታቸውን ጀመሩ።

እነዚህ ቋንቋዎች ስርጭት ሲጀምሩ ከአማርኛ ቋንቋ ላይ ሠላሳ ደቂቃ ተቀንሶ እንደነበር አቶ ንጉሤ ያስታውሳሉ።

የኢህአዴግ የስልጣን ዘመን የቪኦኤ አማርኛ ባልደረቦች የተከሰሱበት ዘመንም ነበር።

በ1997 ምርጫን ተከትሎ በተፈጠረው ግርግር መንግሥት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን፣ አባላትን እና ጋዜጠኞችን ሲያስር እና ክስ ሲመሰረት አቶ ንጉሤን ጨምሮ ሌሎችም የጣብያው ሰራተኞች ክስ ተመስርቶባቸዋል።

“ከተከሰሱት ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ፤ ሌሎችም ተከስሰው ነበር። አሜሪካዊ ዜግነት ስለነበረን የስቴት ዲፓርትመንት ጣልቃ ገብቶ ነው ክሳችን ውድቅ የተደረገው።”

ቪኦኤ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን መምጣት

በ2018 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ቪኦኤ አማርኛ በአገር ውስጥ የሚገኙ ዘጋቢዎቹን ቁጥር ወደ 15 ማሳደግ ቻለ።

በባሕር ዳር፣ ሐዋሳ፣ መቀለ፣ አምቦ ዘጋቢዎች ኖሩት። ከአሃዱ ሬዲዮ ጋር የአጋርነት ስምምነት በመፈጸም ስርጭቶቹ በጣብያው እንዲተላለፍ ማድረግ ቻለ።

ይህ ጊዜ ግን ለቪኦኤ አማርኛ ብቻ ሳይሆን ለአቶ ንጉሤ መንገሻም የተለየ ነበር።

ከ43 ዓመታት በኋላ ወደ አገራቸው ለመጀመርያ ጊዜ መግባት የቻሉት በዚያ ወቅት ነው።

እኔም ሆንኩ ባልደረቦቼ በደርግ ወቅት ወደ አገር ቤት መግባት አንችልም ነበር የሚሉት አቶ ንጉሤ፣

“ከ40 ዓመት በላይ ኢትዮጵያን መርገጥ አልቻልኩም። አገሬን በጣም ነው የምወደው። በደርግ ጊዜ በጣም ከባድ ነበር። አገሬ ለመግባት ቤተሰቦቼንም ይዜ ለመሄድ በጣም እጓጓ ነበር። ግን ከ40 ዓመት በላይ ወደ 42 43 ዓመት አልቻልኩም ነበር” ብለዋል።

“እናቴ ታምማ ላያት አልቻልኩም። አባቴ ሲታመምም ላስታምመው አልቻልኩም። ሲያርፉም ሁለቱንም ልቀብራቸው አልቻልኩም። ስለዚህ የሞቱ ወዳጆቼን፣ ወላጆቼን መቃብራቸው ሄጄ እርሜን ያወጣሁት ያኔ ነው።”

የአሜሪካ ድምጽ (ቪኦኤ) ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የትግራይ ክልል የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የሚፈጽማቸውን ወንጀሎች እንዳላየ በማለፍ እና ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ተከስሷል።

በወቅቱ ቪኦኤ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በትክክለኛ እና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለመዘገብ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ የቀረበበትን ውንጀላ አስተባብሏል።

ጡረተኛው አቶ ንጉሤ ቪኦኤ ተለውጦ ዳግም ስርጭቱን እንደሚጀመር ተስፋ አላቸው።

“ተስፋ አደርጋለሁ በመሃል ምህረት ወርዶ ሪፐብሊካኖች እና ዲሞክራቶች ጣልቃ ገብተው የፕሬዝዳንት ትራምፕን አስተዳደር አሳምነው ፕሮግራሞች በሙሉ እንደማይዘጉ ተስፋ አደርጋለሁ። ተስፋዬ ይኸው ነው።”

እንዳልካቸው ኃይለ ሚካኤል (ዶ/ር) ደግሞ አሜሪካ በዚህ “የትርክት ውግያ” በበዛበት “ተጽዕኖና ጫና” ለማሳደር ኃያላን በሚራኮቱበት ዓለም ቪኦኤን ዘግታ እጇን አጣጥፋ ቁጭ ካለች “በራሷ ላይ ግብ የማስቆጠር ከባድ አካሄድ ነው የሚሆነው” ይላል።