ዳኛቸው ሻምበል ፊዚክስ እያስተማረ

ከ 8 ሰአት በፊት

ዛሬ በኦንላየን ፊዚክስ በማስተማር ዝነኛ የሆነው ዳኛቸው ወይንም ተማሪዎቹ በሚጠሩት ስሙ ‘መምህር ዳኒ’፣ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ “ትምህርት መቀበል አይችሉም” ከሚባሉ ልጆች መካከል አንዱ እንደነበር ይናገራል።

ሁሌም በትምህርታቸው የተሻሉ ተማሪዎችን ሲያገኝ እንዴት እንደሚያጠኑ ይጠይቅ እንደነበር ያስታውሳል።

በአንድ ወቅት ከክፍል አንደኛ የሚወጣውን ጓደኛውን እንዴት ጎበዝ መሆን እንደሚቻል ሲጠይቀው “የአሳ ዘይት ጠጥቶ” እንደሆነ ይነግረዋል።

ሞከረው፤ለውጥ የለም።

ሌላኛው ጓደኛው ደግሞ ‘ጠዋት ጠዋት ሜዲቴት ስለማደርግ ነው’ ትምህርት የሚገባኝ አለው። እርሱንም ሞከረ፤ አልተሳካም።

“አንድ በጣም የምወደው ጓደኛ ነበረኝ እርሱ ደግሞ ‘ቴክዋንዶ ስለምሰራ ነው’ አለኝ። እርሱን ሥሰራ ግራ እጄ ተሰብሮ ወጣሁ”

ጎበዝ ለመሆን ብዙ ሞክሬ ነበር ግን አልተሳካልኝም ይላል፤ የመጀመርያ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲያስታውስ።

ዳኛቸው ከባልንጀሮቹ እኩል ቀለም እንዲዘልቀው እንደተመኘ ስምንተኛ ክፍል ደረሰ።

አባቱ በጥበቃ ሠራተኝነት በሚሰሩበት የግል ትምህርት ቤት ውስጥ በነጻ የሚማረው ዳኛቸው፣ ስምንተኛ ክፍልን ከጓደኞቹ ኮርጆ 96 ፐርሰንታይል ማምጣቱን ያስታውሳል።

አባቱ በልጃቸው ውጤት ፈነጠዙ።በጓደኞቹ መካከል፣ ሰው በተሰበሰበበት አቅፈው እያሽከረከሩ በእርሱ መኩራታቸውን፣ በውጤቱ መደሰታቸውን ነገሩት።

ዳኛቸው ውጤቱን እንዴት እንዳመጣው ስለሚያውቅ ደነገጠ።

አባቱ ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱን ሰምተው፣ አቅፈው ሲያሽከረክሩት “እስከዚያ ድረስ አባቴን የሚያስደስተው የኔ መማር ነው ብዬ አስቤ አላውቅም” ይላል።

አባቱ የጥበቃ ስራቸውን ሲሰሩ በትምህርት ቤት ውስጥ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ያግዛቸው እንደነበር የሚናገረው ዳኛቸው “ፈገግ ይላል እንጂ እንደዚያ ደስ ሲለው አይቼ አላውቅም” ይላል።

አባቱ ተማሪዎች መካከል ዓይናች በእንባ ተሞልቶ፣ አቅፈው ሲያሽከረክሩት፣ አባቱን ስለማስደሰት ብቸኛው የፍጥነት መንገድ ትምህርት መሆኑ ገባው።

የዓመቱ ትምህርት ተከፍቶ ዘጠነኛ ክፍል እስኪገባ ድረስ በድሬዳዋ ከተማ በሚገኝ ቤተ መጻሕፍት ጠዋት እየሄደ ማንበብ እና ማጥናት ጀመረ።

“ሒሳብ ነው መጀመርያ ማጥናት የጀመርኩት” የሚለው ዳኛቸው የተለያዩ የሒሳብ ስሌቶችን እንደ አዲስ መቀመር ያዘ።

በወዳጆቹ እጅ ሲሽሞነሙኑ ያያቸው ቁጥሮች ታዘዙት።ዓይኑ ላይ ብዥታ እና ግርታ ይፈጥሩ የነበሩ ስሌቶች ያለ ችግር ይቀምራቸው ገባ።

የክረምቱ ወራት አልቆ ዘጠነኛ ክፍል ሲገባ ሒሳብ ቀሎኝ ስለነበር ጥሩ ውጤት ማምጣት ስጀምር “ትምህርት ይገባኛል እንዴ እኔ?” እስክል ድረስ ጥሩ ውጤት ማምጣት ጀመርኩኝ ይላል።

ዳኛቸው ለመጀመርያ ጊዜ ዘጠነኛ ክፍል የመጀመርያው መንፈቅ ዓመትን ሦስተኛ በመውጣት አጠናቀቀ።

“ዘጠነኛ ክፍል ስገባ ነቃሁ” የሚለው ዳኛቸው ከዚያ በኋላ ትምህርቱ ላይ ጠንክሮ መቀጠል አንዱ የሕይወቱ አካል ሆነ።

ከሦስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተባረረው ዳኛቸው

ዳኛቸው ሻምበል ውልደት እና እድገቱ በድሬዳዋ ሲሆን እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርቱን ያጠናቀቀው ብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት ነው።

በ2007 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቅያ ፈተና 515 በማምጣት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ተቀላቀለ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ምህንድስና የትምህርት ክፍል 1 ዓመት ከ6 ወር ቢማርም በሱስ ተጠምዶ ትምህርቱን ማጠናቀቅ ሳይችል ቀረ።

ወደ ቻይና የመሄድ እድል ያገኘው ዳኛቸው፣ ሳን ዙ ከተማ ውስጥ የፔትሮሎየም ኢንጂነሪንግ ትምህርቱን ሲከታተል አሁንም ያለበት ሱስ ሳንካ ሆነው።

ለሁለተኛ ጊዜ ቻይና ሐንዡ የምትባል ከተማ የኮምፒውተር ሳይንስ ለመማር የሄደው ዳኛቸው አሁንም ሱሱ ትምህርቱን በአግባቡ መቀጠል አላስቻለውም።

ከሦስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሱስ ምክንያት የተባረረው ዳኛቸው አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የተወሰኑ ወራት ቆየ።

ድሬዳዋ እያለሁ “ከትምህርት ቤት፤ ከቤት ትምህርት ቤት የምል ልጅ ነበርኩኝ” የሚለው ዳኛቸው ከቤተሰብ ተለይቶ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ግን “ሁሉንም ነገር መሞከር ያምረኝ ነበር” ይላል።

ከዚያ ሲጋራ፣ ጫት እየቆየ ደግሞ የተለያዩ አደንዛዥ ዕፆችን እና መጠጥን መጠቀም ጀመረ።

ቻይና የትምህርት እድል አግኝቶ በሄደበት ወቅት ከሱስ ወጥቶ ትምህርቱ ላይ ለማተኮር ለራሱ ቃል ቢገባም “ከራሴ ጋር ስለተጣበቀ አልቻልኩም” ይላል።

ቻይና ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ሳለ በዙርያው ያለ ገደብ እና ከልካይ ሲጃራ የሚያጨሱ ሰዎች ሲመለከት፣ ከሦስት ቀን በላይ ከሱሱ ተነጥሎ መቆየት አልሆነለትም።

በቻይና ቆይታው በነበረበት ሱስ ምክንያት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ “ለአስር ቀን ከታሰርኩ በኋላ ነው ወደ ኢትዮጵያ የተመለስኩት” ይላል።

ዳኛቸው ቤተሰቦቹ ከቻይና መመለሱን እንዲያውቁ አልፈለገም። ስለዚህ ሰፊዋ አዲስ አበባ አንድ ጎዳና ጥግ ተሸሽጎ መቅረትን መረጠ።

በሱስ እና ተስፋ መቁረጥ ወደ ጎዳና ሕይወት መግባቱን የሚናገረው መምህር ዳኛቸው፤ ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች በቀጥታ ያመራው ወደ ቢሾፍቱ ነበር።

ወደ ቢሾፍቱ ለምን እንደሄደ ሲጠየቅ “ቢሾፍቱን የማውቃት ድሮ ነው። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እያለሁ የሜካኒካል ምህንድስና ትምህርት ክፍል ስማር አንድ ትልቅ ፕሮጀክት ለመስራት ወደዚያ ሄጄ ነበር” ይላል።

ቢሾፍቱ በሱስ ዓለም ሲንቧቸር፣ ሕይወቱ የበለጠ እየከበደው መጣ።

በልቶ ማደር ችግር ሆነ። ከሱስ አልፎ ሆዱን ማስታገስ፣ ጥሙን ማርካት አልቻለም። ስለዚህ ጥሏት የመጣው አዲስ አበባ ናፈቀችው።

“ማንም ሰው የማያውቀኝ ቢሾፍቱ ከምሞት ትንሽ ሰው የሚያውቀኝ አዲስ አበባ ሄጄ ብሞት አስከሬኔን ለቤተሰቤ ለመላክ እንኳ ይቀላል ብዬ ነው” ይላል ምክንያቱን ሲያስረዳ።

መናኸሪያ የነበሩ የጎዳና ጓደኞቹ 35 ብር ሰብሰብው ሰጡት። እና በእርሱ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀመረ።

ዳኛቸው ሻምበል

የሕይወት አቅጣጫ ለውጥ ጅማሮ

ከቢሾፍቱ አዲስ አበባ እየመጣ ሳለ መኪናው ቆሞ ለፍተሻ ሲወርዱ ዳኛቸው ሱሱን ማስታገሻ ለመፈለግ ዞር ዞር አለ።

የሲጋራ ቁራጭ አግኝቶ አጭሶ ሲመለስ መኪናው ውስጥ ያሉ ተሳፋሪዎች ገብተው የእርሱ ቦታ ላይ ተቀምጠው ጠበቁት።

ክፍት ወንበር የነበረው ከአንዲት ሴት ጎን ነበር።አጠገብ ለአጠገብ ተቀምጠው ሲያወሩ፣ታሪኩን ሲያካፍላት አዘነችለት።

“እንደምትረዳኝ ቃል ገባችልኝ” ይላል ሁኔታውን ሲያስታውስ።

በወቅቱ መስተንግዶ እየሰራች በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርስቲ ነርሲንግ ትማር የነበረችው ይህች ሴት፣ ለዳኛቸው ሕይወት መለወጥ ምክንያት ሆነች።

እርሷ በቢሾፍቱ ትንሽ ቤት ተከራይታ የምትኖር ቢሆንም ለዳኛቸው ያላትን ለማካፈል፣ የሚተኛበት አነስተኛ ፍራሽ ለመዘርጋት አላመነታችም።

ይህች ሴት የአሁን ባለቤቱ እንደሆነች የሚናገረው ዳኛቸው፣ በእርሷ ድጋፍና እርዳታ የጎዳና ሕይወቱ አበቃ።

እርሷ ጋር ተጠግቶ ሲኖር ቀስ በቀስ ከሱስ እየራቀ መጣ።

“መጽሐፍትን ማንበብ ጀመርኩኝ። ወደ እግዚአብሔር ተጠጋሁ። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመርኩኝ” ከዚያ በኋላ ሱስ እርግፍ አድርጎ መተዉን ያስረዳል።

ሕይወቱ መልክ እየያዘ የመጣው ዳኛቸው ተማሪዎች የከበዳቸውን የሒሳብ፣ የፊዚክስ ትምህርት ሰብሰብ አድርጎ ማስተማር ጀመረ።

“በኮሮና ወቅት በቤተክርስትያን ውስጥ አንድ ክፍል ተሰጥቶኝ አስተምራቸው የነበሩ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ነበሩ” የሚለው ዳኛቸው፣ ከኮሮና በኋላ በአንድ ወር ውስጥ ተዘጋጅተው ለስምንተኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና እንዲቀመጡ ሲነገራቸው ትምህርት ቤቱ ፊዚክስ መምህሩ ለቅቆበት ስለነበር አንድ ተማሪ የእርሱን ስም አንስቶ ለርዕሰ መምህሩ ነገራቸው።

“መምህር እስክንቀጥር ድረስ ክፍሉን ያዝልኝ ብለው አስገቡኝ” ይላል አጋጣሚውን ሲያስታውስ።

እንዲያስተምራቸው ሳይሆን እንዳይረብሹ፣ እንዲቆጣጠር ክፍል ውስጥ የተመደበው ዳኛቸው ግን ከተማሪዎቹ ጋር በሒሳብ እና ፊዚክስ ጨዋታ ጀመረ።

ተማሪዎቹ ወደዱት፤የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አስተያየት ሲሰበስቡ ጥሩ ነገር ስለሰሙ ቀጠሩት።

በዚያች አጋጣሚ የተጀመረች የማስተማር ሕይወት ለሦስት ዓመት ያህል በትምህርት ቤቱ ውስጥ በፊዚክስ መምህርነት እንዲቀጥል አስቻለው።

ዳኛቸው ሻምበል በቢሾፍቱ አደራጅቶት የነበረው ቤተ መጻሕፍት

የማጠናከርያ ትምህርት መስጫ እስከመክፈት

ዳኛቸው አስጠግታው ከምትኖረው ሴት ጋር ትዳር መስርቶ መኖር ጀምሯል።

ሁለቱ ጥንዶች ኑሯቸውን ለማሸነፍ እቁብ እየጣሉ የቤት እቃዎቻቸውን ለማሟላት ይጥራሉ።

ዳኛቸው እና ባለቤቱ ይጥሉት የነበረው 9000 ብር እቁብ ሲደርሳቸው ቁምሳጥን ለመግዛት ቢያስቡም፣ የማጠናከርያ ትምህርት ቤት ለመክፈት ወስነው ቤት ተከራዩ።

ለሦስት ዓመታት በመምህርነት ተቀጥሮ ከሚሰራበት ትምህርት ቤት ለቅቆ በቢሾፍቱ ከተማ “School of My Seed” የሚባል የማጠናከሪያ ትምህርት መስጫ ተቋም ከፈተ።

የማጠናከሪያ ትምህርት ተቋሙን በ16 ተማሪዎች ነበር የጀመረው።

ከ16ቱ ውስጥ ደግሞ የሚከፍሉት ስድስቱ ብቻ ሲሆኑ፣ 10 ተማሪ ደግሞ በነጻ ማስተማር ጀመረ።

“ዋናው የኛ ዓላማ ማገልገል ነበር” የሚለው ዳኛቸው በሦስት ወር ውስጥ የተማሪዎቹ ቁጥር ወደ 80 ማደጉን ይናገራል።

ዳኛቸው በአንድ ክፍል የጀመረው የማጠናከርያ ትምህርት፣ የተማሪዎቹ ቁጥር እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ወደ ሦስት ክፍል አሳደገው።

በልጅነቱ ከቤተሰቦቼ ጋር ይኖር የነበረው በአንድ ክፍል መሆኑን የሚናገረው ዳኛቸው፣ ለማጥናት ሲፈልግ እነርሱ ላይ ለሊቱን ሙሉ እያበሩ ማጥናት ስለሚጨንቀው ሌላ ሠፈር ያሉ ጓደኞቹ ጋር በመሄድ እያደረ ያጠና እንደነበር አልረሳም።

በቂ የማንበብያ ስፍራ የሌላቸው፣ እንደ እርሱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በሚገኝ ቤተሰብ ውስጥ የሚያድጉ ተማሪዎች እነዲገለገሉበት በሚል የማጠናከርያ ትምህርት በሚሰጥበት ሕንጻ ላይ አንድ 24 ሰዓት ግልጋሎት የሚሰጥ ቤተ መጻሕፍት አደራጀ።

ቢሾፍቱ ላይ በነበረው የማጠናከርያ ትምህርት መስጫ ወደ 14 ሰዎችን ቀጥሮ ያሰራ እንደነበር ያስታውሳል።

ተማሪዎቹም ከፊዚከስ ውጪ ሌሎች የሳይንስ ትምህርቶችን ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ሒሳብ እና እንግሊዘኛ ይማሩ ነበር።

ቢሾፍቱ ማጠናከርያ እየሰራ እያለ ማስተማር አትችልም ተብሎ ተዘጋበት።

በዚህ ወቅት በመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ ከመደበኛው ትምህርት ሰዓት ውጪ መማርያ ክፍል ጠይቆ በበጎ ፈቃደኝነት ልጆችን ማስጠናት ጀመረ።

ፊዚክስ እያስተማረ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለቀቁት ቪዲዮች የተቀረፁት በዚህ ወቅት መሆኑንም ይናገራል።

ቢሾፍቱ ላይ ከ2000 በላይ ተማሪዎችን አስጠንቻለሁ የሚለው ዳኛቸው፣ በ2016 ዓ.ም ወደ 45 የሚጠጉ ተማሪዎችን ለአራት ተከታታይ ወራት ከፈተና በፊት በማስጠናት ወደ ዩኒቨርስቲ መግባታቸውን ይናገራል።

ከእነዚህም መካከል 20 ያህሉ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያወጣውን ፈተና ወስደው በማለፍ መግባታቸውን ጨምሮ ተናግሯል።

ዳኛቸው ሻምበል እና ያስተማራቸው ተማሪዎች

‘ማስተማር ጥሪ ነው’

ዳኛቸው ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ፊዚክስን አጥብቆ ይወድ ነበር።

ከልጅነቱ ጀምሮ ሌሎችን ማስጠናት ደግሞ ባሕሪው መሆኑን ይናገራል።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለም ሆነ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ተማሪዎች የከበዳቸውን ነገር ቀለል አድርጎ ማስረዳት ተሰጥኦው እንደነበር ያስታውሳል።

“የማስተማር ጉጉቱ ከድሮም ውስጤ ነበር፤ ግን አስተማሪ እሆናለሁ የሚል እምነት በፍፁም አልነበረኝም፤ እቅዱም አልነበረኝም።”

አባቱ ግን ያለውን ሰዎችን የማስረዳት ትጋት እና ተሰጥኦ ተመልክተው “መምህር ብትሆን ብዙዎች ከስርህ ይማሩ ነበር” ይሉት ነበር።

ዳኛቸው የሚያስተምራቸውን ልጆች ውጤት ሲመለከት፣ ያገኘውን ተቀባይነት ሲመዝን እስከ መጨረሻ የሕይወት ፍጻሜው ድረስ እያስተማረ መቀጠል እንደሚፈልግ ይናገራል።

አሁን ጸሎቴ ሁሉ “ሞቴንም አስተምሬ ስወጣ ቢያደርገው” የሚል ነው የሚለው ዳኛቸው፣ የማስተምረው “ለገቢ ምንጭ፣ ለኑሮ፣ ለመተዳደርያ አይደለም።የማስተማር ‘ፓሽን’ ስላለኝ እና አንድ ለአባቴ የገባሁለት ቃል ስላለ ነው የማስተምረው” ይላል።

በአሁኑ ወቅት ከቢሾፍቱ ጓዙን ጠቅልሎ አዲስ አበባ የከተመው ዳኛቸው፣ በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በበጎ ፈቃድ ተማሪዎችን ለመደገፍ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይናገራል።

ዳኛቸው ለበርካቶች ከባድ የሆነውን ፊዚክስ እንዴት እንዲህ አቅልለህ ማስተማር ቻልክ ተብሎ ሲጠየቅ፣ “እኔ የማስተምረውን የፊዚክስ ትምህርት ለመረዳት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ መሆን አይጠበቅም” ይላል።

“የአንደኛ ክፍል ተማሪ እንኳ ብትሆን እንዲገባህ አድርጌ ነው ለማስተማር ጥረት የማደርገው ሲል ይናገራል። ያም ይመስለኛል ተማሪዎቹን የበለጠ እንዲረዱት እና እንዲመሰጡ ያደረጋቸው።

“ፊዚክስን ሳጠና ለራሴ ብቻ አይደለም የማነብበው። ለማስተምራቸው ተማሪዎች ጭምር ነው፣ አሁን የስድስት ወር ልጅ አለኝ እና የሰድስት ወር ልጄ ራሱ በምን መንገድ ባስረዳው ሊገባው ይችላል የሚለውን ነው ደግሜ ደግሜ የማስበው።”

ከየትኛውም የትምህርት ተቋም በመምህርነት ሙያ ያልሰለጠነው ዳኛቸው፣ መምህርነትን ተምሮ በመመረቅ ዲግሪ በመያዝ ባለሙያ መሆን ቢቻልም “እኔ ግን መምህርነት ጥሪ ነው ብዬ አስባለሁ” ይላል።

“ለተማሪ በቀላሉ የሚያስረዱ፣ በተማሪ የሚወደዱ መምህራን ጥሪያቸው በመሆኑ ነው ብዬ አምናለሁ።”

ዳኛቸው ቢሾፍቱ ቤተልሔም ትምህርት ቤት ከስምንተኛ እስከ 11ኛ ክፍል ድረስ በሚያስተምርበት ወቅት የፔዳጎጂ (የማስተማር ስነ ዘዴ) ስልጠና እንዲያገኝ መደረጉን ገልጿል።

በአሁኑ ወቅትም በኦንላየን አጫጭር ኮርሶችን ለመውሰድ ጥረት እያደረገ መሆኑን ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ባደረገበት ወቅት ተናግሯል።