የዩቲዩብ መንደር

ከ 8 ሰአት በፊት

ቱልሲ በሕንድ የምትገኝ መንደር ናት። ነዋሪዎቿ በአብዛኛው ዩቲዩበር ሆነዋል።

የ32 ዓመቱ ጃቪ ቨርማ ከነዋሪዎቹ አንዱ ነው።

በሕንድ ባህላዊ ልብስ ሳሪ የተዋቡ ሴቶችን ቪድዮ ይቀርጻል። አንድ አዛውንት በወጣቶቹ መካከል ተቀምጠዋል።

ከወጣቶቹ አንዷ የአዛውንቷን እግር ትነካለች። ሌላዋ ውሃ ታቀርብላቸዋለች።

ጃቪ ሥራውን ይወደዋል። የሚቀርጻቸው ሴቶችም ደስተኛ ናቸው። ዩቲዮብ ላይ ቪድዮዎቹ ተወዳጅነት እያገኙ ነው።

ከጃቪ በቅርብ ርቀት የ26 ዓመቱ ራጄሽ ዲዋርም ሂፕ ሆፕ ሙዚቃ ከፍቶ ቪድዮ ይቀርጻል።

አብዛኞቹ የመንደሩ ቤቶች ተመሳሳይ ናቸው። ነዋሪዎች ረዣዥም ዛፎች ዙርያ ይሰባሰባሉ።

‘የዩቲዩብ መንደር’ የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷቸዋል።

የዩቲዩብ መንደር

በመንደሩ ወደ 4,000 ሰዎች ይኖራሉ። 1,000 ያህሉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከዩቲዩብ ጋር የተያያዘ ሥራ አላቸው።

በመንደሩ ውስጥ ቪድዮ ያልተቀረጸ ሰው ማግኘት ከባድ ነው።

ከዩቲዮብ በሚገኘው ገቢ የመንደሯ ምጣኔ ሃብት አድጓል። በመንደሩ እኩልነት እንዲሰፍንና ማኅበራዊ ለውጥ እንዲመጣም አግዟል።

ጥሩ ገንዘብ እያገኙ ካሉት መካከል ከዚህ ቀደም ሥራ ማግኘት ያልቻሉ ሴቶች ይጠቀሳሉ።

20 ዓመት ያስቆጠረው ዩቲዩብ በየወሩ 2.5 ቢሊዮን ሰዎች ይጠቀሙታል።

ሕንድ ከፍተኛ ተጠቃሚ አላት። ዩቲዮብ በበይነ መረብ ይዘት የሚፈጠርበትን መንገድ የለወጠ ነው። ለዚህ ማሳያ ደግሞ የቱልሲ መንደር ነው።

የ49 ዓመቱ አርሶ አደር ነትራም ያድቭ “ወጣቶችን ከአልባሌ ልማድና ወንጀል እንዲቆጠቡ ያደረገው ዩቲዩብ ነው። በሚሠሩት ነገር መላው መንደሩ ይኮራባቸዋል” ይላል።

የመንደሩ የማኅበራዊ ሚዲያ አብዮት የተነሳው እአአ በ2018 ነበር።

ቨርማ እና ጋይንድራ የተባሉ ጓደኞች የዩቲዩብ ገጽ ከፈቱ።

“የፈጠራ ችሎታችንን ማሳደግ ነበር ግባችን” ይላሉ።

ቀኝ ዘመም የሒንዱ ቡድን የፍቅረኞች ቀን ጥንዶች ላይ ጥቃት ሲያደርሱ የሚያሳይ ቪድዮ ሲለቁ ዝነኛ ሆኑ።

ማኅበራዊ ትችትና ስላቅ አዘልም ቪድዮ ነበር።

“ቪድዮው እያዝናና መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው” ትላለች ቨርማ።

በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች አፈሩ። ከ125,000 በላይ ሰብስክራይበር በወራት አገኙ።

ቪድዮዎቻቸው ባጠቃላይ ከ260 ሚሊዮን በላይ ተመልካች አግኝተዋል።

በወር 30ሺህ ሩፒ (346 ዶላር) ማግኘት ሲጀምሩ ዩቲዩብን ዋነኛ ሥራቸው አደረጉ።

ቨርማ በቪድዮቹ አማካይነት ከፊልም ሠሪዎች ጋር ተዋውቃ እስካሁን በሰባት ፊልሞች ተውናለች።

የቱልሲ መንደር ነዋሪ አዲትያ ባግል በቨርማና ሹክላ ቪድዮዎች ተነሳስቶ ነው ዩቲዮብ የጀመረው።

በዓመት ከ20,000 በላይ ተከታዮች አገኘ።

የዩቲዩብ መንደር

ከዚያም ቨርማ በአዘጋጅነትና ጸሐፊነት ቀጠረችው። አብረው መሥራትም ቀጠሉ።

ሌላው ዩቲዩበር የ38 ዓመቱ ማኖጅ ያድቭ ነው። በልጅነቱ ነበር ወደ ትወና የገባው።

ዩቲዩብ ላይ ትወናውን ካሳየ በኋላ በአካባቢው ታዋቂ በሆነ ሲኒማ ሥራ አግኝቷል።

“ይሄንን ሁሉ ያገኘሁት በዩቲዩብ አማካይነት ነው። ስሜቴን ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል” ይላል።

በዩቲዩብ አማካይነት የቱልሲ መንደር ሴቶች በፈጠራው ዘርፍ በብዛት ተሰማርተዋል።

የዩቲዩብ መንደር

የቀድሞው የመንደሩ አስተዳዳሪ ድራውፕዲ ቪንሹ ለመንደሩ መለወጥ ዩቲዩብ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ትናገራለች።

በሕንድ ማኅበረሰባዊ አመለካከት ለመለወጥ ዩቲዩብ ሚናው ቀላል አይደለም።

መድልዎች ለማስወገድ፣ የቤት ውስጥ ጥቃትን ለመከላከል እንዲሁም ፆተኛ ዕሳቤዎችን ለማጥፋት ዩቲዩብን መጠቀም እየተለመደ መጥቷል።

“ሴቶች በፆተኛ ዕሳቤ ምክንያት የሚገጥማቸው ፈተና ብዙ ነው። ቪድዮዎቹ ግን አመለካከቶቹን ለማስወገድ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው” ትላለች የቀድሞው አስተዳዳሪ።

በቅርቡ የ61 ዓመቷ የቀድሞ አስተዳዳሪ ዩቲዩበር ጉዳዩን በተመለከተ ቪድዮ ሠርታለች።

“ሴቶች መከበር እንዳለባቸው በቪድዮው አሳይቻለሁ። ስለ እኩልነትም በቪድዮው ውስጥ ይነገራል” ስትል ቪድዮውን ትገልጻለች።

ራሁል ቨርማ ሌላው የመንደሩ ዩቲዩበር ነው። የ28 ዓመቱ ራሁል ፎቶ አንሺ ነበር። ከመንደሩ ነዋሪዎች ነው ስለ ዩቲዩብ የተማረው።

“መጀመሪያ ላይ እናቶቻችንና እህቶቻችን ያግዙን ነበር። አሁን የራሳቸውን ዩቲዩብ ከፍተዋል። እንዲህ ያለ ነገር ይፈጠራል ብሎ የገመተ አልነበረም” ይላል።

የ15 ዓመት የአክስቱ ልጅም ዩቲዩብ ጀምሯል።

“የመንደሩ ሰዎች ከፍተኛ ቢዝነስ የሚሠሩት በዩቲዩብ ነው” ይላል።

ሕንድ በ2020 ቲክቶክን ሳታግድ በፊት በተለይ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በየመንደሩ የሚሠሩ ቪድዮዎች ቁጥር ጨምሮ ነበር።

በሕንድ ማኅበራዊ ሚና ያለውን ሚና የምታጠናው ሽሪራም ቨንትራማን እንደምትለው መጀመሪያ ላይ በወንዶች የበላይነት የነበረው ዘርፍ ቢሆንም አሁን የሴቶች ተሳትፎ ጨምሯል።

“ለውጥ እየመጣ ነው። አንዳንዶች ለዩቲዩብ ተከታዮቻቸው ቅመም፣ ዘይትና ሌሎችም ምርቶች ይሸጣሉ” ትላለች።

የ56 ዓመቷ ራማኪሊ ቨርማ ገንዘብ ከማግኘት ባሻገር ፈጠራን ማሳደግ ያስደስታታል።

ልጆቿንና የልጆቿን ሚስቶች የምታበረታታ እናት ሆና በመተወን ትታወቃለች።

“ሴቶች እንዲማሩና ስኬታማ እንዲሆኑ ንቅናቄ አደርጋለሁ። እኔ ሕልሜን ካሳካሁ ወጣት ሴቶችም ማሳከት ይችላሉ። ሴቶች ሕልማቸውን ለማሳካት ሲሠሩ ማየት ትልቅ ደስታ ይሰጠኛል” ትላለች።