በገበያ ላይ የተፈጸመው ጥቃት

ከ 4 ሰአት በፊት

የሱዳን ጦር በአገሪቱ ምዕራባዊ ዳርፉር ግዛት በገበያ ላይ ባደረሰው ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መግደሉን በሱዳን ጦርነት የሚፈጸሙ ጥሰቶችን የሚከታተል ቡድን አስታወቀ።

ቱራህ ገበያ ላይ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት “አሰቃቂ ጭፍጨፋ ነው” ሲል በሱዳን ጦርነት በሁለቱ ተፋላሚዎች እየደረሰ ያለውን ጥሰት እየሰነደ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ የጠበቆች ቡድን ገልጿል።

በዚህ ጥቃት ከሞቱት በተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ መቁሰላቸውን ቡድኑ አክሏል ።

የዳርፉርን አብዛኛውን ግዛት የሚቆጣጠረው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ጨምሮ በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ የተለጠፉ ቪዲዮዎች ማንነታቸውን ለማወቅ ጭምር አዳጋች በሆነ ሁኔታ የተቃጠሉ አስክሬኖችን እና ወደ ዶግ አመድ የተቀየሩ የገበያ ድንኳኖችን አሳይተዋል።

ሁለቱም የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በሲቪል ስፍራዎች ላይ ጥቃቶችን በመፈጸም በተደጋጋሚ ይከሰሳሉ።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በዳርፉር ያሰማራ ቢሆንም ጦሩ ያሉትን የጦር አውሮፕላኖች በመጠቀም በግዛቲቱ የተፋላሚው ይዞታዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ይፈጽማል።

በጦሩ ይዞታ ስር ከምትገኘው ኤል ፋሽር 35 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ገበያ ላይ የተፈጸመው ጥቃት መቼ እንደሆነ ወይም ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ቢቢሲ ማረጋገጥ አልቻለም።

የዳርፉር የመብት ተሟጋች ቡድን ዘ ዳርፉር ኢንሺዬቲቭ ፎር ጀስቲስ ኤንድ ፒስ በበኩሉ ሰኞ ዕለት ጥቃት መፈጸሙን ገልጾ “ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እጅግ የከፋ የቦምብ ጥቃት” ሲል ጠርቶታል።

በአገሪቱ የተከሰተው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ በሰላማውያን ዜጎች ላይ የሚደረገው የቦምብ ጥቃት እንዲሁም የሲቪሊያን ሞት ከቅርብ ወራት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

ደም አፋሳሹ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ህይወትን ከመቅጠፍ በተጨማሪ ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ተገደዋል።ግምቱ ቢለያይም በጦርነቱ ቢያንስ 150 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል።

በአገሪቱ ረሃብ በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱን ተከትሎ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ህዝብ “ከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት” ላይ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

በአገሪቱ በረሃብ እና በቸነፈር በርካቶች መገረፋቸውን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለማችን የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንደሆነ ፈርጆታል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በዳርፉር የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን መግደል እና እንደ ዘር ማጽዳት መሳሪያ በመጠቀም አረብ ያልሆኑ ሴቶችን ይደፍራል የሚሉ ማስረጃ የቀረበበትን ክሶች ውድቅ አድርጓል።