በመቀለ የሚገኝ ባዶ ነዳጅ ማደያ

ከ 59 ደቂቃዎች በፊት

የትግራይ ክልል ንግድ እና ኤክስፖርት ቢሮ ላለፉት 11 ቀናት ከሌሎች ክልሎች “በተለየ ሁኔታ” ወደ ትግራይ ክልል ነዳጅ ምንም አይነት ነዳጅ አለመጫኑን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለሁሉም ክልሎች የሚያጋራው የነዳጅ ስርጭት መረጃ፤ የነዳጅ አቅርቦት ሙሉ ለሙሉ የቆመው “በትግራይ ክልል ብቻ” እንደሆነ እንደሚያመለክት በቢሮው የሸማቾች ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ክንደያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል የንግድ እና ኤክስፖርት ቢሮ ከትናንት በስቲያ፣ ሰኞ መጋቢት 15/ 2017 ዓ. ም የነዳጅ አቅርቦትን ለሚመለከታቸው የፌደራል መንግሥት ተቋማት በጻፈው ደብዳቤ ወደ ክልሉ የሚላከው ነዳጅ ላይ የተደረገው “ክልከላ አሁንም መቀጠሉን” አስታውቆ ነበር።

ለንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን እንዲሁም ለነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተጻፈው ደብዳቤ፤ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ክልሉ ነዳጅ የገባው መጋቢት 6/2017 ዓ.ም. እንደሆነ ይገልጻል።

ከጥር ወር ጀምሮ ወደ ክልሉ የሚገባው የነዳጅ መጠን “በእጅጉ መቀነሱን” በደብዳቤው ያስታወሰው ቢሮው፤ በመጋቢት 4 እና 5/2017 ዓ.ም. ለክልሉ የሚቀርበው ነዳጅ “ሁለት የነዳጅ ጭነት መኪና መውረዱን” ገልጿል።

“ይባስ ብሎ ከመጋቢት 6/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ትግራይ የተጫነ ነዳጅ አለመኖሩ ችግሩ እንዲቀጥል እና እንዲወሳሰብ” እያደረገ መሆኑን ጠቅሷል። ለትግራይ ክልል የሚቀርበውን ነዳጅ በተመለከተ “በተደጋጋሚ ጥያቄ” መቅረቡን እና “ተደጋጋሚ ውይይቶች” መካሄዳቸውን ያስረዳል።

ደብዳቤው፤ “ወደ ትግራይ ነዳጅ እንዲጫን እንደተፈቀደ በቃል ተነግሮን ተስፋ አድርገን ብንቆይም እስካሁን ችግሩ ሳይፈታ ወደ ትግራይ የሚላከው ነዳጅ ክልከላ አሁንም ቀጥሏል” ሲል ችግሩ አለመፈታቱን ይገልጻል። በቢሮው የሸማቾች ጥበቃ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ካሳሁን፤ “ከመጋቢት 6 ጀምሮ አንዳንችም ነዳጅ ወደ ክልል አልተጫነም” ሲሉ ይህንኑ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የመቀለ ከተማ ነዳጅ ማደያዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ኪሮስ አባይም በተመሳሳይ የከተማዋ በስራ ላይ ያሉት 13 ማደያዎች ለመጨረሻ ጊዜ ነዳጅ ያገኙት ከሁለት ሳምንት በፊት መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ኪሮስ፤ በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ነዳጅ ማደያ የመጨረሻውን የነዳጅ አቅርቦት ያገኘው የካቲት 24/2017 ዓ.ም. እንደሆነ ገልጸዋል።

አቶ ኪሮስ፤ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ማደያዎች የሚፈልጉት የነዳጅ መጠን በመግለጽ ለነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ገንዘብ እንደሚከፍሉ እና እንደሚጫንላቸው ያስረዳሉ።

“እንዲጫንልን ብለን ጠይቀን፣ ገንዘብ ከፍለን፤ የከፈልነው ገንዘብ እዛው እንደቆመ ነው” በከተማዋ የሚገኙ ማደያዎች ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ ነዳጅ እንዳላገኙ ገልጸዋል።

ወደ ትግራይ ክልል ነዳጅ ለመጫን ሁሉንም ሂደት ጨርሰው ጅቡቲ የቆሙ ተሽከርካሪዎች ብዛት 22 እንደሆነ የትግራይ ክልል ንግድ እና ኤክስፖርት ቢሮ የሸማቾች ጥበቃ ዳይሬክተሩ አቶ ካሳሁን ተናግረዋል።

ባለሶስት እግር ተሽከርካወዎች መቐለ ከተማ ውስጥ

ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች፤ ተሽከርካሪዎቹ ጭነው ላለመነሳታቸው የሚሰጡት ምክንያት “ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ቆዩ እያለን ነው” የሚል እንደሆነ አቶ ኪሮስ ገልጸዋል።

ቢቢሲ፤ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል ነዳጅ እየጫኑ ያልሆነበትን ምክንያት ለመረዳት ያነጋገራቸው ሶስት የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ተወካዮች “ጉዳዩ የሚመለከተው መንግሥትን” እንደሆነ በመጥቀስ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የሸማቾች ጥበቃ ዳይሬክተሩ አቶ ካሳሁን እንደሚናገሩት በጅቡቲ የሚገኙት ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ጭነው ለመንቀሳቀስ ለሚያቀርቡት ጥያቄ የሚሰጣቸው ምላሽ “አትገቡም፣ አልተፈቀደም፣ ጀምሩ አልተባልንም” የሚል እንደሆነ ይናገራሉ።

ወደ ትግራይ ክልል የሚገባውን ነዳጅ ላይ ያለውን ችግር ከፌደራል መንግሥት ተቋማት ጋር ለመነጋገር ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአዲስ አበባ የሚገኙት አቶ ካሳሁን፤ ወደ ትግራይ ክልል ነዳጅ መግባት ስለቆመበት ምክንያት “በቂ ምላሽ” አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።

“እኛ እስካሁን [የነዳጅ አቅርቦት ለምን እንደቆመ] እየጠየቅን ነው ያለነው። የሚሰጠን መልስ የሚያረካ አይደለም። ትክክለኛ፣ መሬት ላይ ያለው ነገር በሚፈታ መልኩ አይደለም” ወደ ትግራይ ክልል ነዳጅ መግባት ስለቆመበት ምክንያት “በቂ መረጃ የሚሰጥ አካል እንደሌለ” ገልጸዋል።

የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ፤ ወደ ትግራይ ክልል ነዳጅ አለመግባቱን አረጋግጠው፤ ነገር ግን “ትግራይ ላይ ብቻ በልዩ ሁኔታ ነዳጅ እንዳይገባ የተደረገበት ነገር የለም” ብለው ነበር።

ዋና ዳይሬክተሯ፤ በጅቡቲ በሚገኝ የነዳጅ ዴፖ ላይ ባጋጠመ ብልሽት ምክንያት በሀገሪቱ የነዳጅ እጥረት ማጋጠሙን ተናግረዋል። ትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን “ምንም ነዳጅ ያልገባባቸው ሌሎች ክልሎችም” መኖራቸውን ሳህረላ ገልጸዋል።

“ትግራይ ላይ ብቻ ሳይሆን ነዳጅ ምንም ያልገባባቸው ቤኒሻንጉል [ጉሙዝ ክልል አንዱ ነው። ጋምቤላ እንደ ክልል 47 ሺህ ሊትር ብቻ ነው የገባው። ትልቁ ክልል አማራ የምንለውም ምናልባት ናፍጣ የተወሰነ አግኝቷል። ቤንዚን ግን 25 ሺህ [ሊትር] አካባቢ ብቻ ነው ያገኘው” በማለት አስረድተዋል።

ሀረሪ ክልልም በተመሳሳይ “ምንም ነዳጅ እንዳልገባ” እንዲሁም ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል “ከምባታ ዞን ብቻ 24 ሺህ ሊትር” መቅረቡን ጠቅሰዋል። ባጋጠመው እጥረት ምክንያት ነዳጅ ሲቀርብ የነበረው “ለየትኛዎቹ ከተሞች ነዳጅ አቅርቦቱን ቅድሚያ እንስጣቸው” የሚለው ታይቶ እንደሆነ አስረድዋል።

“አዲስ አበባ ላይ እንግዲህ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ [ፍላጎት]፣ ብዙውም የመኪና እንቅስቃሴ ያለው እዚህ ከመሆኑ ጋር [ተያይዞ]፤ የተለያዩ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ያሉባቸው አንገብጋቢ የሆኑትን ቅድሚያ ሰጥተን የማስተናገድ ነው እንጂ፤ የትግራይ ክልል ለብቻው የተደረገ ምንም ነገር አይደለም ያለው” ብለዋል።

የነዳጅ ማደያ ሠራተኛ ነዳጅ እየቀዳ

ሳህረላ አክለውም፤ “ለመቀለ ዩኒቨርሲቲ”፣ “ስደተኛ ካምፕ ላይ ለሚሰራ ለውጭ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት” እና “በመስኖ ስራ ላይ ለተሰማራ ድርጅት” ከማደያዎች ሳይሆን ቀጥታ ነዳጅ እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።

የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ለመቅረፍ በአዋሽ እና ሱሉልታ ከሚገኙ “ኦፕሬሽናል ዴፖዎች ” ሲቀርብ እንደነበር የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ያጋጠመው ችግር “አሁን ሙሉ በሙሉ ‘maintain’ [እንዲስተካከል] ተደርጓል” ብለው ነበር።

ሳህረላ፤ “ስለዚህ በቀጣይ ጊዜያት ጅቡቲ ካሉት ኦፊስ [ቢሮ] ጋር ተነጋግረን፤ አቅርቦቱንም ለማስተካከል እና ቢያንስ ዛሬ እና ነገ ባሉት ጊዜያት ውስጥ ነዳጅ ተጭኖላቸው እንዲሄድ የማድረጉን ስራ በእኛ በኩል የመጀመሪያው የቤት ስራችን ነው” ሲሉ ባላፈው ሳምንት በሰጡት ምላሽ ገልጸው ነበር።

ዋና ዳይሬክተሯ፤ ይህንን ምላሽ ከሰጡ ከአንድ ሳምንት በኋላም ግን አሁንም ወደ ክልሉ ነዳጅ እንዳልገባ የትግራይ ክልል ንግድ እና ኤክስፖርት ቢሮ የሸማቾች ጥበቃ ዳይሬክተሩ አቶ ካሳሁን እና የመቀለ ከተማ ነዳጅ ማደያዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ኪሮስ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ቢቢሲ፤ ሌሎች ክልሎችም የነዳጅ አቅርቦት አለማግኘታቸውን ለማረጋገጥ ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም። ወደ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አመራሮች የተደረጉ የስልክ ጥሪዎችም ምላሽ አላገኙም።

የሸማቾች ጥበቃ ዳይሬክተሩ አቶ ካሳሁን ግን የነዳጅ አቅርቦት “ሙሉ ለሙሉ የተቋረጠው ትግራይ ክልል ብቻ” መሆኑን ይናገራሉ። አቶ ካሳሁን ለዚህ መከራከሪያቸው በዋቢነት የሚጠቅሱት የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለክልሎች የሚያቀርበውን የነዳጅ ስርጭት መረጃ ነው።

“እኛ [መረጃውን] እናየዋለን ወደ ሁሉም ክልል ይሄዳል። የሚሄድበት ቦታ የተለያ ሊሆን ይችላል። ዛሬ ወደ አንዱ ከተጫነ ነገ ሊቆምበት ይችላል። አለፍ አለፍ እያለ እንደዛ ሊያጋጥመው ይችላል እንጂ እንደኛ ሙሉ በሙሉ የተዘጋ የለም” ሲሉ ከአስር ቀናት በላይ ነዳጅ ያልገባበት “ብቸኛ ክልል” ትግራይ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት በየቀኑ “ከስምንት ሚሊዮን ሊትር በላይ” ነዳጅ እየጫነ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ካሳሁን፤ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ይህንን ያህል መጠን ያለው ነዳጅ ሲጫን ትግራይ ክልል ከአራት እስከ ስድስት መኪና ነዳጅ በየቀኑ ያገኝ እንደነበር ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የነዳጅ አቅርቦት በመቋረጡ ምክንያት የህክምና ተቋማት እና ተፈናቃዎችን የሚረዱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስራቸውን ማከናወን እንዳልቻሉ አስረድተዋል።

የትግራይ ክልል የንግድ እና ኤክስፖርት ቢሮ ሰኞ ዕለት በጻፈው ደብዳቤም ነዳጅ አቅርቦት በመቋረጡ “የሰብአዊ እርዳታ፣ የሆስፒታሎች እና አምቡላንሶች፣ የመድሃኒት አቅርቦት እና ስርጭት እንዲሁም በተፈናቃይ መጠለያ ማዕከላት የሚከናወኑ የምግብ እና መድሃኒት አቅርቦት” ስራዎች መቆማቸውን አስታውቋል።