ፕ/ር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ
የምስሉ መግለጫ,ፕ/ር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ

የጽሁፉ መረጃ

የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር መርከብ ቢሆን ካፒቴኗ ፕሮፌሰር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ ይሆናሉ።

ፕ/ር ኤልሳቤጥ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ስነ ጥበብ እና ኪነ ጥበብ ሂስ አንቱታን አትርፈዋል። ወዳጆቻቸው እና ጓደኞቻቸውን ጨምሮ ብዙዎች ፕ/ር ኤልሳቤጥን ‘አንቺ’ ስለሚሏቸው እኛም በዛው እንቀጥል።

“ወንዳዊ፣ ሰሜናዊ እና ተዋረዳዊ የኃይል ግንኙነት (hierarchical power relation) ላይ የተመሰረተ” የምትለውን እና ብዙዎች ያለ ጥያቄ እና ፍተሻ የሚቀበሉትን ዘልማዳዊ የኢትዮጵያ የታሪክ አጻጻፍ ስነ-ዘዴ ሞግታች።

ፕ/ር ኤልሳቤጥ ወደ አካዳሚው መድረክ ከመጣች በኋላ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር በተለይም ድግሞ የታሪክ አጻጻፍ ተቀይሯል። ወንዳዊ እና ፖለቲካ ላይ ያተኮረው ስነ ዘዴ ከታሪክ እና ከታሪክ አጻጻፍ የተሰወሩ ማኅበረሰቦችን እንዲያካትት ደክማለች። ይህ ድካሟ ፍሬ አፍርቷል።

ፕ/ር ኤልሳቤጥ ከ1996 እስከ 2002 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ዳይሬክተር ሆና ሰርታለች። ከዚህ በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲውን የጥበባት ኮሌጅ ለሶስት ዓመታት በዲንነት መርታለች።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የገብረ ክርስቶስ ደስታ የዘመናዊ ስነ ጥበብ ቤተ መዘክር ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን መስርታ የማዕከሉ ዳይሬክተር ነበረች።

በዚህ ማዕከል ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን የትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ጁሊ ምህረቱ እና ዴንማርካዊው ኦላፉር ኤልያሰን ስራዎች ለህዝብ ዕይታ እንዲቀርቡ አድርጋለች።

በ2010 ዓ.ም. የአሊ ማዙሪ ፌሎው ሆና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በምትገኘው ሻርዣ ከተማ በሚኘው ዓለም አቀፍ ጥናት ዩኒቨርሲቲ አፍሪካ ኢንስቲትዩትን ተቀላቅላ ነበር። ከዛ በመቀጠል በተቋሙ የድኅረ ምረቃ እና የዶክትሬት ትምህርት ምስረታ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ነበራት።

በተቋሙ የስነ ሰብ ትምህርት ክፍል ሊቀመንር እንዲሁም የስነ ጥበብ ታሪክ፣ ንድፈ ሃሳብ እና ሂስ ፕሮፌሰር ሆና አገልግላለች።

ከዚህ በተጨማሪም በብራውን ዩኒቨርሲቲ እና ቬይና የስነ ጥበብ አካዳሚ ትርፍ ሰዓት ፕሮፌሰር እንዲሁም ጣሊያን አገር በሚገኘው የሮክፌለር ቤላጂዮ ሴንተር ፌሎ ነበረች።

ፕ/ር ኤልሳቤጥ ከሌሎች ሁለት የሙያ አጋሮቿ ጋር በመሆን ‘Ethiopia: Modern Nation–Ancient Roots’ የተሰኘ መጽሃፍ ከጥቂት ወራት በፊት አሳትማለች። የሰዓሊ ሄኖክ መልካምዘር የጠልሰም ትርዒትንም በቅርቡ አሳትማለች።

በ2005 ዓ.ም. ‘What is ‘Zemenawinet’? Perspective on Ethiopian Modernity” የተሰኘ መጽሃፍ አርትዖት ሰርታለች። መጽሃፉ የኢትዮጵያን ዘመናዊነት በታሪክ፣ ሥነ ጽሁፍ፣ ኪነ ህንጻ እና ሥነ ጥበብ መነጽር ይፈትሻል።

ይህቺ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ማገር፣ የኢትዮጵያ ዘመናዊ የስነ ጥበብ ሂስ ምልክት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መጋቢት 7/ 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።

ፕ/ር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ ከጓደኞቿ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ፕ/ር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ ከጓደኞቿ ጋር

ፕ/ር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ ማን ናት?

ባልንጀሮቿ “ኤልሲ፣ ዕድሜን፣ የትምህርት ደረጃን፣ መደብን፣ ተዋረዳዊ ግንኙነትን ጨምሮ በርካታ ግንቦችን (boundaries) ያፈረሰች ሰው ነበረች” ሲሉ ይገልጿታል።

ፕ/ር ኤልሰቤጥን ለ13 ዓመታት የምታውቃት አንድ ወዳጇ “ከትንሽ እስከ ትልቅ ተማሪዎቿ ጭምር ኤልሲ ነበር የሚሏት፣ በተለይም ተዋረዳዊ ግንኑነትን (hierarchichy) ማለፍ ችላለች” ትላለች።

ኤልሳቤጥ ወይም ወዳጆቿ እንደሚጠሯት ‘ኤልሲ’ ከእናቷ ዋካ ድንቄ እና ከአባቷ ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደ ዮሀንስ የግንቦት ልደታ ቀን 1948 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደች።

ኤልሳቤጥ የቤተሰቦቿ የመጨረሻ ልጅ ብትሆንም “ከሰባታችንም የምትበልጠው እጅግ በጣም ብሩህ አዕምሮ የነበራት እና ባለተሰጥዖዋ እሷ ነበረች” ሲሉ ወንድሟ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ያስታውሳሉ።

ኤልሳቤጥ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በናዝሬት ትምህርት ቤት ከጨረሰች በኋላ በአብዮቱ ጊዜ ወደ አሜሪካ ተጓዘች።አሜሪካን አገር ከሚገኘው በኋላ ከሞርጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች።

ወደ አሜሪካን አገር ከተጓዘች በኋላ የተማሪዎች ንቅናቄ ንቁ ተሳታፊ ነበረች። ከባለአፍሮ ጓዲት እና ጓዶች ጋር ሆና

“በ20ኛው ዘመን ጨረቃ ስትወጣ

ያንቺ ኑሮና ዕድል ከወፍጮም አልወጣ

ታገዬ ታገዬ ሴት በርቺ ታገዬ

ነጻነት ለማግኘት ወደኋላ አትበዬ” እያለች ለጨቆኑ ሴት እህቶችዋ ግራ እጇን እያነሳች ታግላለች።

ኤልሳቤጥ እሷን ጨምሮ አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ሸሽተው ከአገር ለኮበለሉ ወጣቶች “የዜግነት እና የአገር ባለቤትነት ሃሳብ ባልተረጋጋ እና አያዎ በሆነ የተቃርኖ ማንነት ውስጥ ገብቷል” ትላለች።

እነዚህ ወጣቶች “በአንድ በኩል፣ የሀገራቸውን የቅርብ ጊዜ መከራና ጭንቀት መርሳት አልቻሉም፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሩቅ ላሰቡትን ቦታ ሥርዓትና መዋቅር ለመስጠት ያንን የወቅቱን አሳዛኝ ክስተት ለመካድ ይፈልጋሉ’ ስትል ትገልጻለች።

ኤልሳቤጥ ጊዮርጊስ ስደትን፣ የዘር ማጥፋትን እና እንግልትን በመፍራት በለጋ እድሜያቸው ወደ አሜሪካ የፈለሰው የዚህ የተፈናቀለ የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ ውጤት መሆኗን በፒ.ኤች.ዲ ማሟያ ጽሁፏ ላይ አስፍራለች።

ኤልሳቤጥ ወደ አሜሪካ ከተጓዘች በኋላ የመጀመሪያ ዲግሪያዋን የያዘችው ከፋይናንስ ጋር ተዛማጅነት ባለው የትምህርት ዘርፍ ነበር። የመጀመሪያ እና የድህረ ምረቃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ የባንክ ስራ ላይ ለአስራ ሰባት ዓመታት ቆይታለች።

በሰሜን ካሊፎርኒያ ለባንክ ኦፍ አሜሪካ ረዳት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆና ሰርታለች። ከዛ በመቀጠልም በኒው ዮርክ ለሚገኝ አንድ ትልቅ የጃፓን ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ነበረች።

ኤልሳቤጥ ኮብልላ የሄደችባት አገረ አሜሪካ መቅደሷን እና ጥበቃዋን ብትሰጣትም ለሃያ ሰባት አመታትን የኖረችው ግን ባካኝ እና ባይተዋር ነፍስ ሆና ነበር። እነዛ 27 ዓመታት የትላንት አሰቃቂ የዘር ማጥፋት በመርሳት እና በማስታወስ ያለፉ ዥረቶች ነበሩ።

ይህ የውስጧ ተቃርኖ ለረጅም ጊዜ ያላየቻትን አገሯን የቀረጸውን ተጨባጭ ሁኔታ እንዳታይ አደረጋት።

ከሃያ ዓመታት ቆይታ በኋላ በ1980ዎቹ መጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የመጀመሪያ ሙከራዋ ነበር። ወደ ኢትዮጵያ ስትሄድ ያጋጣማት በአሰቃቂ ለውጦች ውስጥ ያለፈው የአገሪቱን እውነታ ነው። ከዚያ በኋላ ሶስት ጊዜ ተመልሳ ሂዳለች በእያንዳንዱ ጉዞዋና በእያንዳንዱ ጉብኝት ለብዙ ጊዜ ሸክሟ የነበረውን ያለፈውን ትላንት የማወደስ (romanticizing the past) ቅዠቶች ማፍረስ መቻሏን ትገልጻለች።

ፕ/ር ኤልሳቤጥ ለምሁራዊ ውይይቶች እና ንግግሮች ትልቅ ትኩረት ትሰጥ ነበር። እነዚህ ውይይቶች በአካዳሚያዊ ቅጥር ግቢዎች እና በመመሪያ ክፍሎች ውስጥ ብቻ የተቀነበቡ አልነበሩም። መኖሪያ ቤቷም የወጣት ምሁራን መገናኛ የሰሉ ውይይቶች የሚካሄዱበት መድረክ ነበር።

በመኖሪያ ቤቷ ለሚሰባሰቡ ወጣት የሥነ ጥበብ ታሪክ፣ የጾታ እና ሴቶች ጥናት ምሁራን ለእውቀት፣ ለትምህርት፣ ለጥናት እና ምርምር ትኩረት እንዲኖራቸውና እንዲተጉ ትወተውታቸዋለች።

ሻለቃ ዳዊት ቄስ ሰፈር የሚገኘው እና የፕ/ር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ መኖሪያ ቤት “የወጣቶች መሰባሰቢያ ነበር” ይላሉ።

የፕ/ር ኤልሳቤጥ የ13 ዓመት ወዳጅም ይህን ሃሳብ ታጠናክራለች።

“ለምትወዳቸው ጓደኞቿ፣ ወዳጆቿ ። በየትኛውም ሰዓት ቤቷ ክፍት ነበር” የምትለው ይህች ባልንጀራዋ፤ “ወዳጅ ከሆነች አቅጣጫ ለማሳየት ትሞክራለች- እውቀትን ማቀብ የሚባል የላትም። ስለ ወዳጆቿ ትምህርት፣ ሙያ፣ ቤተሰቦች ሁሉንም ትጠይቃለች” ስትል ፕ/ር ኤልሳቤጥን ትገልጻታለች።

“ቤቷ ራሱ ሙዝየም ነበር የሚመስለው። ጸሓፊ፣ ሰዓሊ፣ ወዳጆች የምትላቸው ሰዎች መሰባሰቢያ ነበር። ቤቷ ለወዳጆቿ በሙሉ ክፍት ነበር። ሙዚቃ፣ ምግብ፣ ጥበብ፣ ሳቅ፣ ደስታ የተሞላበት ነበር” ስትል የፕ/ር ኤልሳቤጥ ወዳጅ ታስታውሳለች።

ሰዓሊ እና ቀራጺ በቀለለ መኮነን “ብዙ ተማሪዎችን አስተምራለች ትልልቅ ተስፋ ያላቸው የስነ ጥበብ፣ የባህል እና የታሪክ ተማሪዎችን የእውቀት እና የሞራል ደረጃ ከፍ በማረድግ ብዙ ሰው ማውጣት ችላለች” ሲል አበርክቶዋን ይገልጻል።

ፕ/ር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ

ወደ ማኅበራዊ ሳይንስ ጉዞ

እ.አ.አ መስከረም 11/ 2001 በዓለም የንግድ ማዕከል ላይ የደረሰው ጥቃት ኤልሳቤጥ የሙያ ዘርፏን እንድትለውጥ ካደረጓት ምክንያቶች መካከል ወሳኙ ነው።

ኤልሳቤጥ በዓለም የንግድ ማዕከል ከደረሰው ጥቃት ከተረፉት ዕድለኞች መካከል አንዷ ነበረች።

ከጥቃቱ በህይወት በትተርፍም የብዙ ባልደረቦቿን ሞት አይታለች። ክስተቱንም “የሰው ልጅ የመጨረሻ ጭካኔን የሚያስታውስ” ስትል ትገልጸዋለች።

የመስከረም 11 ጥቃት ብዙ አሰቃቂ ትዝታዎችን መዝዟል” የምትለው ኤልሳቤጥ፤ ነገር ግን በዚህን ጊዜ ትዝታ ለውጥ ዳና ሆኗል ትላለች።

ከጥቃቱ በኋላ በፈጠራ እና በባህል ተዋስዖ (discourse) ማኅበራዊ ለውጥን ወደ ሚያጎለብት ሙያ ለመሰማራት ወሰነች።

በአገሯ የባህል እና የፖለቲካ ማንነት የተወሳሰቡ መሆናቸውን የተገነዘበችው ኤልሳቤጥ የባንክ ስራዋን እርግፍ አድርጋ ትታ ወደ ኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ አቀናች። በኢትዮጵያ የሚገኝ የባህል ተቋምን ለማስተዳደር በማሰብ በሙዚየም ጥናት የድህረ ምረቃ ዲግሪዋን ሰራች።

የባህል እና ታሪክ ተዋስዖ ላይ የተሰማሩ ተቋማትን ማፍራት አሁንም ኢትዮጵያ ላለችበት ሁከት አዎንታዊ ለውጥ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቷ ፖለቲካዊ ከባቢ እና የእድገት ሂደት ወሳኝ መሆኑን መረዳቷን ገልጻለች።

የኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪዋን ይዛ፣ ጓዟን ሸክፋ በ1996 ወደ አገሯ ጠቅላላ ገባች።

ወደ አገር ቤት ስትመለስ የአገሯ መገለጫ የሆኑትን የከፋ ድህነት እና የማህበረሰብ ውል መፈራረስ ለማስታረቅ አዳግቷታል።

ሆኖም መመለሷ ራሱን ያለፈውን ከማሽሞንሞን አስተሳሰብ ጋር ያጠላለፈው እና የቅርብ ጊዜውን የዕዳ፣ የጅምላ ስደት እና የእርስ በርስ ጦርነት ታሪክ ከቁብ ያልቆጠረው የዲያስፖራውን ምፀት እንድትገነዘብ አድርጓታል።

በዚህ ስሜት ውስጥ እያለች ነው የሀገሪቱ ዋና የምርምር ማዕከል፣ ሙዚየም እና የጥበብ ጋለሪ የሆነውን የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም በዳይሬክተርነት እንድትመራ ኃላፊነት የተጣለባት።

በኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩት በሶስት አመታት ቆይታዋ ተቋሙን ከፈዘዘ የአካዳሚክ ማዕከልነት ወደ ደማቅ የውይይት መድረክ ቀይራዋለች።

ከሶስት ዓመት ቇይታ በኋላ ፒ.ኤች.ዲዋን ለመስራት ወደ ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ አመራች። በ2000 ዓ.ም. “በኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ታሪክ ስኮላርሺፕ ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት” በሥነ ጥበብ ታሪከ እና ሂስ ዶክትሬቷን ሰራች።

ፕ/ር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ እና ሰዓሊ ሄኖክ መልካምዘር
የምስሉ መግለጫ,ፕ/ር ኤልሳቤጥ ሰዓሊ ሄኖክ መልካምዘር የጠልሰም ትርዒትን በቅርቡ አሳትማለች

የኢትዮጵያ ዘመናዊነት ተዋስዖ

የኢትዮጵያ ዘመናዊነት ንግግር ውስጥ የፕ/ር ኤልሳቤጥ ድርሻ ጉልህ ነው። ዘመናዊነት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ላይ በብዙ አሰላስላለች፣ ጽፋለች አስተምራለች።

ኤልሳቤጥ ለዶክትሬት ድግሪዋ ማሟያ ዘመናዊነት እና የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ ጥበብ ላይ ትኩረት አድርጋ ያካሄደችው ጥናት እና ምርምር በ2011 ዓ.ም. “Modernist Art in Ethiopia” በሚል ርዕስ ላሳተመችው መጽሃፍ እርሾ ሆኗል።

መጽሃፏ በአዲስ አበባ በተመረቀበት ወቅት “የመጽሃፉ ዋና ሃሳብ በመመረቂያ ጽሁፌ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ከመመረቂያ ጽሁፏ በፍጹም ተለይቶ በአገሪቱ የባህል፣ የፖለቲካ እና የምሁራን ታሪክ ላይ አውጠንጥኖ ስነ ጥበብን እና ኪነ ጥበብን መሰረታዊ ከአገሪቷ ባህል ፖለቲካ እና የምሁራን ታሪክ ሊመለከት ይሞክራል” ብላ ነበር።

በኦሀዮ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የታተመው “Modernist Art in Ethiopia” በ2012 ዓ.ም. የአፍሪካ ጥናቶች ማኅበር ሽልማትን አግኝቷል።

በመጽሃፏ የዘመናዊ ስነ ጥበብ እና ኪነ ጥበብን ታሪክ ከፖለቲካ ለውጦች ጋር እያመሳከረች የመጡት የፖለቲካ ለውጦች እና ፍልስፍናቸው የስነ ጥበብ እና ኪነ ጥበቡ መግለጫ ላይ እንዴት እንዳንጸባረቁ ታሳያለች።

“ስነ ጥበብ እና ኪነጥበብ የአገሪቱ ፖለቲካ እና ምሁራን ታሪክ ነጸብራቅ ስለሆኑ ገነጣጥለን ማየት አንችልም” ትላለች።

የዘመናዊነት ታሪክ ላይ በሚያጠነጥነው እና በአምስት ክፍሎች በተዘጋጀው መጽሃፏ ዝመና የሚለውን ሃሳብም በሰፊው ትተነትናለች። በዘመናዊነት እሳቤ ዘመናዊ ስነ ጥበብ እና ኪነ ጥበብ ስንል ምን ማለት ነው? የሚለው ነው የመጽሃፉ ዋና ማጠንጠኛ ነው።

“እስካሁንም ምሁራኖቻችንም ሆኑ ፖለቲከኞቻችን በሚገባ ያላብላሉት ነገር ቢኖር ይሄው የዘመናዊነት ንድፈ ሃሳብ እና ታሪክ [ነው]” ትላለች።

“ዘመናዊነት በጣም ቁልፍ ነገር” መሆኑን የምታነሳው ፕ/ር ኤልሳቤጥ፤ “ተደጋጋሚ የምንሰማው የስልጣኔ እና ልማታዊነት ሃሳብ እንጂ ይሄንን ያቀፈውን እና ዋናውን ፍልስፍና የዘመናዊነት ታሪክ በአገራችን ምሁራኖች የሚተነተነው በጥቂቱ ነው”።

ለፕ/ር ኤልሳቤጥ “የዝመና ታሪክ በአንድ በኩል (emanicipatory) የነጻነት እና የመብት ታሪክ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ (violance) የጭካኔ ታሪክ ነው’።

ይህን ሃሳቧን ስታብራራ “በዘመናዊነት ስም ነው ቅኝ አገዛዝ የመጣው፤ በጭካኔ እና በግድያ ነው ገዢው ተገዢውን በእግሩ ውስጥ ያስገባው” ትላለች። በተጨማሪም “ቅኝ ግዛት. . . የዘመናዊነት አካል ነው ያለ ቅኝ ግዛት ዘመናዊነት የለም” ስትል አርጀንቲናዊውን ፕሮፌሰር ዋልተር ሚግኖሎ ትጠቅሳለች።

“Modernist Art in Ethiopia” የኢትዮጵያ ዘመናዊነት እና ዘመናዊ ስነ ጥበብን እሳቤ ከአድዋ ጦርነት ማግስት ጀምሮ ይተነትናል።

በብርሃን እና ሰላም ጋዜጣ ይወጡ በነበሩ ጽሁፎች እና እንደነ ደጃዝማች ተክለሀዋርያት እነ ብላታ መርስዔኃዘን ወልደቄርቆስ የመሰሉ በዘመኑ የነበሩ ጸሐፊዎች ይዛ ስለዘመናዊነት ተንትናለች።

“የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር በፈረንጆቹ ተመስርቶ በፈረንጆቹ አተናተን ስነ ዘዴ የተቀመጠ” መሆኑን ትተቻለች።

ከዛም አልፍ ብላ በ1960ዎቹ የነበሩትን ምሁራን ታሪክ፣ አስተሳሰብ እና አመለካከት ትዳስሳለች። “የዘመናዊነትን ፍልስፍና በመጠቀም እነዚህ መሰረታዊ ለውጥ ያመጡ ምሁራን በመያዝ ከዘመናዊነት ጋር የሚመጣውን ቀደም ብሎ የቅኝ ግዛት ህልውና የሚባለውን እንዴት ተመለከቱት” ብላ ትገመግማለች።

ዘመነኞቹ ሰሎሞን ደሬሳ፣ በዓሉ ግርማ፣ መንግሥቱ ለማ፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ ጸጋዬ ገብረመድኅን እና ሌሎቹን ምሁራንን በመመልከት የዘመና ዊነትጽንሰሃሳብ እንዴት ተተነተነ ስትል ትጠይቃለች።

“የዘመኑ ፖለቲከኞች የዛን ዘመን ታሪክ ያጣጥሉታል የዛን ዘመን ታሪክ በቅጡ ካላጠናነው አገራችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ ወይም የሚያጋጥማትን ችግር በፍጹም መፍታት አንችልም” የምትለው ፕ/ር ኤልሳቤጥ፤ የዛ ዘመን ታሪክ አሁንም እንዴት እንደዘለቀ በመጽሃፏ ትጠቁማለች።

ከተጠቀሱት የስነ ጽሁፍ ሰዎች በተጨማሪ የ1960ዎቹ ዋና ዘመነኞች የነበሩት የሰዓሊዎቹ የገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ እስክንድር ቦጎስያን እና ተማሪዎቻቸውን ስራ እና ታሪክ ታስረዳለች።

በዚህ ጊዜ “መጀመሪያ ጊዜ የሴቶችም ታሪክ በዝመና ታሪክ ውስጥ ይገባል” የምትለው ፕ/ር ኤልሳቤጥ የዘመኑም የሴቶች ውክልና በፖለቲካ እና በማኅበረ ኢኮኖሚው አውድ እንዴት እንደነበር ትዳስሳለች።

“ከተለመደው የጣይቱ ብጡል ሸዋረገድ ገድሌ ወጥተን የደስታ ሀጎስን ዘመነኝነት እንመለከታለን” ትላለች ፕ/ር ኤልሳቤጥ።

‘እናት ሐገር ወይም ሞት’ ስትል በሰየመችው ምዕራፍ ደግሞ ከአብዮቱ በኋላ በደርግ ጊዜ የነበረውን እሳቤ ትመለከታለች።

ከስዕሎቹ እና ከአገሪቱ ፖለቲካ በላይ የጊዜውን ስነ ጽሁፍ በተለይ ደግሞ በዓሉ ግርማን ኦሮማይ እና የጊዜውን የሙዚቃ ታሪክ አያይዛለች። በጣም ብዙ የሆኑ አርቲስቶችን ቃለ መጠይቅ አድርጋለች።

በዚህ ምዕራፍ የዘመኑን የብሄርተኝነት ምልከታ በሰፊው ይተነተናል። በተለይም ደግሞ የብሄርተኝነትን እና የርሃብን ታሪክ አሰናስላ የበቀለ ኃይሌን ‘ኢትዮጵያ በየካቲት 66’ ተሰኘ ስዕል እንዲሁም የገብረ ክርስቶስ ደስታን አስደናቂ የርሃብ መግለጫ ስዕል አቅርባለች።

የእሸቱ ጥሩነህ ‘ረሃብ ፈታው’ እንዲሁም የእሰየ ገብረመድኅን ርዕስ ያልተሰጠውን ስዕል አካትታለች።

በመጨረሻው የመጽሃፉ ምዕራፍ ከ1980ዎቹ መጨረሻ ወዲህ ያሉ ስምንት ዘመነኛ (contemporary) አርቲስቶችን ይዛ የዘመኑን ፖለቲካ እያብራራለች ስራው ላይ እንዴት እንዳንጸባረቁ ትገመግማለች።

“Modernist Art in Ethiopia” መደምደሚያ ላይ ፕ/ር ኤልሳቤጥ “የዘመናዊነት እና የቅኝ ግዛት ታሪክ በተደገጋሚ መጻፍ እንዳለበት እና ይሄንን ካላደረግን የልማትን ሆነ የብሄርን አመለካከቶችን ለመረዳት ያስቸግራል” ትላለች።

ከዚህ በተጨማሪም “ፈረንጆቹ የሚያቀርቡትን የእኛን አገር ታሪክ ወይም የዘመናዊነት መድኃኒት ከማስተጋባት ይልቅ በጥርጣሬ ልንመለከተው ይገባል” ስትል ታሳስባለች።

ፕ/ር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ

ስነ ጥበብ እና ውክልና በኢትዮጵያ ታሪክ

ፕ/ር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ “ከታሪክ የተሰወረን ህዝብ ለማየት እንግዲህ በይነ ዲስፕሊናዊ የሆነ ስነ ዘዴ መጠቀም ወሳኝ ይሆናል” የሚል እምነት ነበራት።

ለዚህም ነው ስነ ጥበብን እና ኪነ ጥበብን ከታሪክ ጋር አስተሳስራ የምትመለከተው።

አንድ የጥበብ ስራ የተሰራበትን ወቅት ይዛ ‘እንዴት ነበር ወቅቱ?’ ብላ በመጠየቅ ከታሪካዊ ሂደቱ ጋር አብረው ተያይዘው የሚመጡ ጥያቄዎችን ትተነትናለች። ይህ መንገድ የአንድ የጥበብ ስራ ባለቤት አስተሳሰብ እና አመለካከት ለመረዳት ያስችላታል።

“አንድን ወቅት የማይገልጽ አንድን የታሪክ ናሙና የማያንጸባርቅ ተብሎ ስለሚገመት ስዕል እንደቀልድ የሚታይ ቤት ማስጌጫ” ተደርጎ እንደሚወሰድ ትገልፋለች።

ለፕ/ር ኤልሳቤጥ ግን አንድ የጥበብ ስራ ከስነ ውበት የዘለለ ፋይዳ አለው።

ዘመናዊ ስነ ጥበብ እና ኪነ ጥበብ ማለት ምንድን ነው? እንዴትስ ይንጸባረቃል? ከኃላ ያለውስ ፖለቲካ ምንድን ነው? የልሂቃን ታሪኩ ምን ይመስላል የሚሉ ጥያቄዎች በአያሌው አብላልታለች።

ከዚህ በተጨማሪም ፕሮፌሰር ኤልሳቤጥ ካሰላሰለችባቸው፣ ከጻፈችባቸው ጉዳዮች መካከል የሴቶች ውክልና በኢትዮጵያ ታሪክ እና ስነ ጥበብ ውስጥ ምን ይመስላል የሚለው አንደኛው ነው።

በጽሁፎቿ በታሪክ፣ በፖለቲካ በማኅበረሰብ ግንኙነት ውስጥ የጾታ ውክልና እና የጾታ ምናብን (imagination) ዳስሳለች።

“የሴቶች ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያ በምትባለው እና በሚኖሩባት በሚወለዱባት በሚሞቱባት አገር ውስጥ እንዴት ተተረከ የሴቶች ታሪክ እንዴት ተተረጎመ ተሰየመ” ስትል ጠይቃለች።

ታሪክ ፍጹም እውነት አይደለም በጣም ተለዋዋጭ ነው” የምትለው ፕ/ር ኤልሳቤጥ “ይሄ ነው የምንለውን የኢትዮጵያ ታሪክ መጀመሪያ በማን ነው የተጻፈው ብለን መጠየቅ አለባብን” ስትል ታሳስባለች።

በ1920ዎቹ በብርሃን እና ሰላም ጋዜጣ ላይ በወንድ ፀሐፊዎች የስልጣኔ እና ዘመናዊነት ሙግት ሲጀመር “ሴቶች ግን የስልጣኔው እና የዝመናው አባል ተብለው አልተገመቱም ነበር። የኢትዮጵያ ዘመናዊ አገረ መንግስት ግንባታ ውይይት በሰፊው ሲጀመር ሴቶች የተገለሉ እንጂ ተሳትፎ እንዳልተሰጣቸው ማየት ይቻላል” ትላለች ፕ/ር ኤልሳቤጥ።

ለአመል ያህል በታሪክ ድርሳናት ስማቸው ተጠቅሶ ስራቸው ተዘክሮ የሚታዩትንም የገዢው መደብ አባል የሆኑት ነገስታት ሴቶች ነበሩ።

እንደ ጣይቱ እና እቴጌ መነን ከመሳሰሉ ነገስታት ሴቶች በስተቀር ሌሎቹ ሴቶች ከታሪክ አጻጻፍ ስነ ዘዴ የተገለሉ እንደነበሩ ስትናገር ትደመጣለች። ለዚህም ኢትዮጵያ ታሪክ በኃይል ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ወንዳዊ የሆነ ገዢ አስተሳሰብ የተጠናወተው መሆኑን በምክንያትነት ታነሳለች።

“ይህን የተዛነፈውን ታሪክ ለመለየት ጥያቄ ሴቶች እንዴት እንደተወከሉ መመርመር ዋናው መሰረት ይሆናል” ትላለች። ይህ ውክልና በታሪክ መጽሃፎች፣ በስነ ጽሁፍ፣ በጋዜጣ፣ በአፈ ታሪክ፣ በትውፊት ወይም በስዕል ሊሆን እንደሚችልም ትጠቁማለች።

ዘመናዊ የብሔር ግንባታ ፕሮጀክት የተዋቀረው ከአድዋ ጦርነት በኋላ መሆኑን የምታነሳው ፕ/ር ኤልሳቤጥ ራሱ አድዋ ድል አተራረክ የተዛባ እና ወንዳዊ አስተሳሰብ የተጫነው ስለመሆኑ ሞግታለች።

በአንድ ወቅት “አድዋ ሲነሳ ጣይቱ በተደጋጋሚ ትነሳሳለች እንደ ብቸኛ ሴት ነው የምትነሳው ጣይቱ ከሰማይ አልወረደችም ከህብረተሰቡ የወጣች ሴት ናት። ንግሥት ሴት ትሁን እንጂ የዛ ኅብረተሰብ ውልድ ናት። በዛን ጊዜ እንደሷ አይነት ሴቶች አልነበሩም ብዬ መገመት ያዳግተኛል፤ ነገር ግን ውክልናው የሚያስቀምጣት ብቻዋን የነበረች ሴት ከሴቶች ሁሉ ተለይታ ከወንድ ጋር የምትወዳደር አድርጎ ነው የሚያቀርባት፤ ሌሎቹ ሴቶች አይመጥኗትም ማለት ነው። ወንዳዊ ሃቲቱ እሷ የተጫወተችውን ሚና መካድ አይችልም ታሪኳን ያወድሳል ግን ሁሉም ከታሪክ የተሰወሩ ሴቶች ከአድዋ ጦርነት ትረካ ይሰረዛሉ” ስትል የአድዋ ድልን የታሪክ አጻጻፍ ተችታለች።

ባለብዙ ገጿ ኤልሳቤጥ፤ ወጣቶችን አሰባሳቢዋ ‘ኤልሲ’፤ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ስነ ጥበብ ሂስን እና የታሪክ አጸጻፍ ምሉዕ ያደረገችው ፕ/ር ኤልሳቤጥ፥ ባለ ግርማ ሞገሷ ኤልሳቤጥ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ስርዓተ ቀብሯ ተፈጽሟል።

ፕ/ር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ