አሊስ ሌል ጉኦ

ከ 5 ሰአት በፊት

እአአ በ 2022 መጀመሪያ ላይ ከማኒላ በስተሰሜን በምትገኘው ባምባን የፊሊፒንስ የገጠር ከተማ ነዋሪዎች አሊስ ሌል ጉኦ ለተባለች ወጣት ሴት ለከንቲባነት ለምታደርገው የምረጡኝ ዘመቻ ተሰብስበዋል።

ደጋፊዎቿ ለምርጫ ቅስቀሳ የምትጠቀምበትን ሮዝ ቀለም ያለው ልብስ ለብሰው መምጣትዋን በጉጉት ይጠባበቃሉ።

ከዚያም ጉኦን የጫነው ሂሊኮፕተር በአካባቢው ሲደርስ ደጋፊዎቿ ስሟን እየጠሩ በጋራ የድጋፍ ድምጻቸውን አሰሙ።

የ31 ዓመቷ ጉኦ ለከተማዋ ነዋሪዎች ድጎማዎችን ለማድረግ እና የምጣኔ ኃብት እድገት ለማምጣት በስሜት የተሞላ ንግግር አደረገች።

በከተማዋ በርካታ ደጋፊዎችን ከጎኗ ማሰለፍ የቻለችው ጉኦ የመጀመርያዋ ሴት ከንቲባ ለመሆን ተስፋ አድርጋለች።

ነገር ግን ድጋፋቸውን ለእርሷ ለመስጠት በዕለቱ ከተሰበሰቡት ጥቂቶቹ ብቻ መጨረሻዋ በፖለቲካው መድረክ እንደደመቁ መቆየት እንደማይሆን ጠርጥረዋል።

ሦስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጉኦ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ለቻይና መንግሥት በመሰለል ተወንጅላ ወደ ወህኒ ተወረወረች።

የፖለቲካ ከፍታዋ ማሽቆልቆል የጀመረው ከቢሮዋ ጀርባ ግዙፍ የማጭበርበር ተግባር ሲካሄድበት የነበረውን ግቢ በፖሊስ አሰሳ ከተደረገበት በኋላ ነው።

ነገር ግን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጠለቅ ብለው ሲመረምሩ ጉኦ ስለ ቀድሞ ሕይወቷ መሠረታዊ የሚባሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ስትታገል ስለ ማንነቷ ግራ አጋቢ ጥያቄ ተነሳ።

በእውነቱ አሊስ ጉኦ ማን ናት?

ሁሉም በፍቅሯ የወደቀው ከንቲባ

ከአነስተኛ የገበሬ ቤተሰብ እንደተገኘች የምታስረዳው ጉኦ፣ የቤተሰቦቿን የአሳማ ንግድ ከማስተዳደር ወደ ፖለቲካ እንደመጣች ትናገራለች።

ጉኦ ያደረገችው የሕይወት መስመር ለውጥ፣ ሊያውም ፖለቲካ፣ ረብጣ ገንዘቦችን የሚጠይቅ ነው።

ለፖለቲካ ገንዘብ የእናት ጡት ወተቱ ነው።

እና ይህንን ወጪ ከየት አምጥተሽ ሸፈንሽው ተብላ ስትጠየቅ በአሳማ እርባታ ንግድ ውስጥ ያሉ ጓደኞች እና የምታውቃቸው ግለሰቦች በከንቲባነት ለመወዳር የሚያስፈልጋት ገንዘብን እንደሸፈኑ ተናግራለች።

በርግጥ ጉኦ ከበርካታ ሐብታም የቻይና ነጋዴዎች ጋር ግንኙነት ነበራት።

ነገር ግን ስለ እነዚህ ቱጃሮች ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም፣ እንደውም አንዳንዶቹ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሕገወጥ ገንዘብን ወደ መደበኛው የገንዘብ ዝውውር በማስገባት ወንጀሎች ተከስሰዋል።

የምረጡኝ ዘመቻዋ ፍልቅልቅ ሰብዕናዋ ላይ ያተኮረ ነበር።

በአንድ ዝግጅት ላይ ጉኦ ለደጋፊዎቿ “የእኛ ቡድን ቁጥር አንድ መመርያ ማንንም ላይ ጉዳት አታድርሱ የሚል ነው፤ ማንም ላይ ጉዳት ማድረስ አይፈቀድም፤ በዙርያችን ፍቅርን ማንገስ አለብን! ፍቅር፣ ፍቅር!”

ያንን የመሰለ ፍቅልቅነት እና በጎ አሳቢነት ከጀርባው ከባድ ወንጀል ተሸክሟል የሚሉት የአገሪቱ ባለስልጣናት በጉኦ አስተዳደር ወንጀል ተፈጽሟል ብለው መወንጀላቸው ለብዙዎች ስላቅ ነበር።

በከተማው ውስጥ አትክልቶችን የምትሸጠው የ31 ዓመቷ ፕርስኪላ ሜይ አባን “አሊስ ቆንጆ ነበረች፣ ደግ እና ሌሎች ሴቶችን ትረዳ ነበር” ብላለች።

ለቢቢሲ ድምጽዋን ለጉዋ መስጠቷን የተናገረችው ፕርስኪላ፣ ሴት እንዲሁም የከተማዋ ከንቲባ በመሆኗ ሴቶች የከተማዋን ጽዳት ስራዎች እንዲሰሩ ማድረጓን ተናግራለች።

ቢቢሲ ከበርካታ የባምባን ነዋሪዎች ጋር ባደረገው ቃለምልልስ መረዳት እንደቻለው ጉኦ አሳቢ እና አዛኝ መሪ ተደርጋ ትታይ ነበር።

ከአሊስ የፖለቲካ አጋሮች መካከል የአንዱ ልጅ የሆነችው ሚያህ ሜጂያ በአካባቢው ለሚኖር እያንዳንዱ ቤተሰብ ነፃ የትምህርት እድል እንደሰጠች ተናግራለች።

ሌላ ቃለ መጠይቅ የተደረገለት ግለሰብ የኮሌጅ ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን ለትምህርት ቤት ወጪው የሚውል የገንዘብ ድጎማ እንደተደረገለት ተናግሯል።

የ75 ዓመቱ ፍራንሲስኮ ፍሎሬስ፣ “እዚህ በባምባን ብዙ ድሆችን ረድታለች፣ መድሃኒት በነጻ ትሰጠን ነበር፤ ከሰዎች ጋር የነበራት ሁኔታ ስትመለከት ምንም ችግር አይታይህም” ሲሉ በስሜት ተሞልተው ተናግረዋል።

በጉኦ የሥልጣን ዘመን ማክዶናልድ እና የፊሊፒንስ ፈጣን ምግብ አቅራቢው ጆሊቢ ቅርንጫፎቻቸውን በከተማዋ መክፈታቸውን በኩራት ጠቅሰዋል።

በኦንላይን ስለ ጉኦ የሰፈሩት መረጃዎች ተራማጅ ወጣት ከንቲባ መሆኗን ሲገልጹ፣ በሮዝ ቀለም የተንቆጠቆጠ አስደናቂ የሰልፍ ትርዒት እና የሙዚቃ ድግሶች ምስሎች በሰፊው ተጋርተዋል።

በከንቲባነት አንድ ዓመት ከግማሽ ካገለገለች በኋላ ግን ይህ በጥንቃቄ የተደራጀ የሰብዕና ግንባታዋ መፍረስ ጀመረ።

አሊስ ሌል ጉኦ

የባምባን ከተማ ሥውር ወንጀሎች

እአአ የካቲት 12 ምሽት ላይ የፊሊፒንስ ፖሊስ፣ በባምባን የሚንቀሳቀሰው ዙን ዩአን ቴክኖሎጂ ኢንኮርፖሬትድ የተሰኘ ኩባንያ እገታ ሥር የነበረ ቬትናማዊ ማምለጡ ጥቆማ ደረሰው።

መጋቢት 12 ምሽት የፖሊስ መኮንኖች እና ወታደሮች በማዘጋጃ ቤቱ ከሚገኘው የጉኦ ቢሮ የአንድ ደቂቃ የእግር መንገድ ርቀት ላይ የሚገኘውን ይህንን ስፍራ ለመውረር በማቀድ በአቅራቢያው ተሰበሰቡ።

የፕሬዚዳንቱ የተደራጀ ወንጀል አስወጋጅ ኮሚሽን (PAOCC) ባልደረባ የሆነው ማርቪን ዴ ላ ፓዝ ለቢቢሲ እንደተናገረው እኩለ ሌሊት አካባቢ ለፖሊስ መረጃ የሚያቀብሉ ግለሰቦች፤ ሰዎች ከግቢው በአውቶቡሶች ተሳፍረው እየወጡ መሆኑን ጠቆሙ።

ሚስተር ዴ ላ ፓዝ እና ባልደረቦቻቸው አካባቢውን የመቆጣጣር እቅዳቸው ሾልኮ እንደወጣ የተጠራጠሩት የጸጥታ ኃይሎች ዘልለው ወደ ቅጥር ግቢው ገቡ።

ወደተለያየ አቅጣጫ ለመሸሽ የሞከሩትን ሰዎች ተከታትለው በቁጥጥር ስር አዋልዋቸው።

ቦታው ላይ ሲደርሱ በፊሊፒንስ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ እና 36 ሕንጻዎችን የያዘ ፣ ወደ 20 ሄክታር የሚጠጋ ስፋት ያለው የሳይበር ወንጀል ካምፖች አገኙ።

ሚስተር ዴ ላ ፓዝ “ተደንቀን ነበር፤ ይህን የመሰለ ትልቅ መግቢያ [ወደ ማጭበርበርያው ግቢ] ስናይ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜያችን ነበር… ወድያውኑ በዚህ ግቢ ውስጥ ትንሽ እንደሆንክ ይሰማሃል።

ቅጽር ግቢው የተገነባው ጉኦ ቀደም ሲል በባለቤትነት ይዛው በነበረው መሬት ላይ እንደሆነ ታወቀ።

በከንቲባነቷም ለዙን ዩን የንግድ ፍቃድ ሰጥታለች። ስሟም ከስፍራው በተገኘ የኤሌክትሪክ ክፍያ ደረሰኝ ላይ ታይቷል።

የአሊስ ጉኦ ጠበቆች ለቢቢሲ ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።

ዙን ዩን፣ በፊሊፒንስ የባህር ማዶ ጨዋታዎች ኦፕሬተር ፈቃድ የያዘ፣ በኦንላይን የሚያቋምር የመዝናኛ ኩባንያ እንደነበር ተገልጿል።

ይህ ፈቃድ ቀደም ሲል እንደዚህ ያሉ አካላት በፊሊፒንስ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ እንዲሰሩ የተሰጠ ፈቃድ ነበር።

እአአ በ 2017 በቀድሞው ፕሬዝዳንት ሮድሪጎ ዱተርቴ ለቀቅ ያለው የአገሪቷ የአቋማሪነት ሕግ የንግድ እንቅስቃሴው እንዲስፋፋ አድርጓል።

ነገር ግን ብዙ የማጭበርበር ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት ይህንን ፈቃድ የወንጀል ተግባራቸውን ለመደበቅ ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል።

እናም ይህንን የሚቆጣጣረው የመንግሥት ቢሮ ለቢቢሲ እንደተናገረው ዙን ዩዋን በግቢው ውስጥ ‘ፒግ ቡቸሪንግ’ በተባለ የማጭበርበር መንገድ ላይ ተሰማርቷል።

ፒግ ቡቸሪንግ በግርድፉ ሲተረጎም አሳማ ማረድ ነው።

ይህ ስያሜ የተሰጠው ‘ፒግ ፋትንኒንግ’ አሊያም አሳማ ማደለብ ከሚለው ሐሳብ ነው። የተጭበርባሪዎችን እምነት መግዛት እንደማለት ነው።

ፒግ ቡቸሪንግ አጭበርባሪዎች ፍቅረኛሞች ወይም የወደፊት የንግድ አጋሮች መስለው ከተጠቂዎች ጋር በመቀራረብ መተማመን ለመፍጠር ጊዜ የሚወስዱበት እና ገንዘባቸውን ለማጭበርበር የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው።

ማጭበርበር የሚካሄድበት ሕንጻ

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የፖሊስ መኮንኖች በግቢው ሲገኙ፣ ቢቢሲ ጭር ያለውን ግቢ የጎበኘ ሲሆን፣ በወቅቱ የሠራተኞች ማደሪያ ክፍል ውስጥ ዒላማ የተደረጉ ግለሰቦችን እንዴት ማጭበርበር እንደሚቻል የሚያሳይ ጽሑፎችን አግኝቷል።

እንደ ዴ ላ ፓዝ ገለጻ፣ እሱና ባልደረቦቹ በባምባን ግቢ ውስጥ ከ300 በላይ የውጭ አገር ዜጎችን ያገኙ ሲሆን፣ ብዙዎቹም ከፍላጎታቸው ውጪ እየሠሩ ነበር።

በማይታዘዙ ወይም ዝቅተኛ አፈጻጸም በሚያሳዩ ሠራተኞች ላይ የሚደርሰው ቅጣት ድብደባ ሲሆን በዚህ ወቅት ሠራተኛው “ዒላማዬን ነገ አሳካለሁ” እያለ ደጋግሞ ቃል እንዲገባ ይደረጋል።

የሠራተኞቹ መኖርያ ተለይቶ የታጠረ እና የአደጋ መከላከያ ሽቦ የተደረገበት ሲሆን በራሱ ብቻውን ሌላ ዓለም ነው።

በዚህ ቅጽር ግቢ ውስጥ ቅርጫት ኳስ፣ የገበያ አዳራሽ እንዲሁም ምግብ ቤቶች ይገኛሉ።

ሠራተኞቹ በአንድ ክፍል ውስጥ ስድስት ሆነው የሚኖሩ ሲሆን እያንዳንዳቸው መጸዳጃ ቤት እና መታጠብያ ቤት አላቸው።

አለቆቻቸው የራሱ በር ያለው ለብቻው ተነጥሎ የሚገኝ ግቢ ውስጥ ይኖራሉ።

በእብነ በረድ ያጌጠ ሳሎን፣ የደህንነት ካሜራ የተገጠመለት እና ካጌጡ እንጨቶች በተሰሩ የቤት ዕቃዎችን ተሞልቷል።

ከቤቱ ጀርባ የመዋኛ ገንዳ ያለ ሲሆን፣ ከጎኑ ደግሞ ለማምለጫ እንዲያገለግሉ ሆነው ወደ ተዘጋጁ ዋሻዎች የሚወስድ ደረጃ ይታያል።

እአአ ማርች 12 ቀን 2024 ምሽት ላይ የጸጥታ ኃይሎች የባምባን ግቢን በቁጥጥር ስር ባዋሉበት ወቅት፣ በማጭበርበር ሥራ ላይ የተሰማሩት ኃላፊዎች አምልጠዋል።

ነገር ግን ይህ የመንግሥት እርምጃ በፖለቲካው ከባቢ ላይ ለውጥ መኖሩን አሳይቷል።

በጁን 2022 ልክ ጉኦ ከንቲባ ሆና ቃለ መሃላ ስትፈጽም የሮድሪጎ ዱተርቴ የፕሬዝዳንትነት ዘመን አብቅቷል።

ፕሬዝዳንቱን የተኩት ፈርዲናንድ ማርኮስ ጁኒየር ስልጣን ላይ ሲወጡ በአቋማሪነት የተሰማሩ ላይ እገዳ እንዲደረግ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥያቄዎች መቅረብ ጀመሩ።

በፊሊፒንስ በርካቶች ስለ እነዚህ ማጭበርበርያ ስፍራዎች ያላቸውን ቅሬታ ቢያሰሙም የሚያስገቡት በሚሊዮኖች የሚቆጠረው ገቢ ለእገዳው ሳንካ ሆኖ ቆይቷል።

የእነዚህ አቋማሪዎች ዋነኛ ደንበኞች ሀብታም ቻይናውያን የነበሩ ሲሆን፣ ይህም የውጭ ተጽዕኖ ስጋትን በአገሪቱ ላይ ደቅኗል።

በባምባን የሚገኘው የሳይበር ወንጀል ካምፕ በቁጥጥር ስር በዋለ ጊዜ ሌሎች የፊሊፒንስ ድብቅ የወንጀል ስፍራዎችን አጋልጧል።

እናም ከከንቲባዋ ቢሮ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የሳይበር ወንጀል ካምፕ እና በውብ ቃላት እና በአማላይ ተስፋ የተገነባው ሮዙ የፖለቲካ ጉዞ በአንድነት ወደቁ።

ጉኦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደጋጋሚ በመቅረብ የማጭበርበር ወንጀል ከሚፈጸምባቸው ካምፖች ጋር ስላላት ግንኙነት ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱላት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥታለች
የምስሉ መግለጫ,ጉኦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደጋጋሚ በመቅረብ የማጭበርበር ወንጀል ከሚፈጸምባቸው ካምፖች ጋር ስላላት ግንኙነት ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱላት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥታለች

ትዝታዋ እየደበዘዘው የመጣው ከንቲባ

ጉኦ በፊሊፒንስ ውስጥ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በአገሪቱ ከፍተኛ ምክር ቤት ፊት ቀርባ ከአጭበርባሪ አቋማሪዎች ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታስረዳ እስክትጠየቅ ድረስ በአገሪቱ ውስጥ በአንፃራዊነት የማይታወቅ ስም ነበር።

በአጭር ግዜ ውስጥ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መሳቅያ መሳለቅያ ሆነች።

በቤተሰቦቿ እርሻ ላይ እየሰራች እንዳደገች ለሕዘብ እንደራሴዎች ስትናገር ከፊሊፒንሳውያን ተክለ ሰውነቷ እና ድሎት የሚታይበት ፊቷ ለገጠር ኑሮ እንደሚበዛ በመጥቀስ ብዙዎች ተሳለቁ።

እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ፣ ግልጽ ያልሆኑ አስተያየቶችን ስትሰጥ ስትታይ፣ እንዲሁም የልጅነት ሕይወቷ ውስጥ የተከሰቱ መሠረታዊ ዝርዝሮችን መርሳቷ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታዋቂ አደረጋት።

በዚህም “ዝንጉዋ ልጅ” የሚል ቅጽል ስም እንዲሰጣት ሆነ።

ጉኦ ከቻይናዊ አባት እና ከፊሊፒንሳዊ እናት የተወለደች እና የተገለለ ልጅነት እንደነበራት ተናግራለች፤ ነገር ግን በፊሊፒንስ ቤተሰቧ የት አካባቢ ይኖር እንደነበረ ማስታወስ አልቻለችም።

በአንድ ወቅት፣ አንድ የሕዝብ እንደራሴ “እባክሽ ክብርት ከንቲባ፣ አንዳንድ አስፈላጊ ጥያቄዎችን ለመመለስ እስካሁን ካሳየሽው ትንሽ ቅንነት በላይ አሳዪ” ሲሉ ተማጽነዋታል።

እጅጉን በጥርጣሬ ይመለከቷት ለነበሩ ሴናተሮች ከንቲባ ከመሆኗ በፊት የመሬቱን ድርሻዋን እንደሸጠች እና ለዙን ዩዋን የንግድ ፍቃድ መስጠቷ ደግሞ ተራ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንደሆነ ተናግራለች።

በሲንጋፖር የሚገኝ ፍርድ ቤት በፊሊፒንስ የሚኖሩ እና የጉኦ የንግድ አጋር የነበሩ ሁለት ቻይናውያን በገንዘብ ማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ሲፈረድባቸው እርሷ ላይ ያለው ጥርጣሬ ጨመረ።

ከዛ ባለፈው ሐምሌ ወር በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ የሕዝብ ፍላጎት ቢኖርም፣ ጉኦ የተጣለባትን የጉዞ ገደብ አልፋ ወደ ኢንዶኔዢያ አምልጣለች። ከጥቂት ወራት በኋላ እንደገና ተይዛ ወደ ፊሊፒንስ ተመለሰች።

የፊሊፒንስ መርማሪዎች በሐምሌ ወር ጥርጣሬያቸውን የሚያጠናክር መረጃ በእጃቸው ገባ።

በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከቻይናዊ እናቷ ጋር ፊሊፒንስ መምጣታቸውን የሚያሳይ የጣት አሻራ ተገኘ።

ይህ መረጃ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ጉኦ ሰላይ ልትሆን ትችላለች የሚል ጥርጣሬ አስነሳ።

ይህም ጉዳዩን በንቃት በሚከታተለው ሕዘብ ዘንድ በሰፊው ተሰራጭቶ መነጋገርያ ሆነ።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የተካረረ ፖለቲካ መጦዝ ወጣቷ ከንቲባ በአገር ክህደት ውንጀላዎች መካከል አጣብቂኝ እንድትገባ አደረጋት።

ሌሎች ግን ከንቲባዋ ላይ የቀረበውን ክስ ይጠራጠራሉ። በቻይና-ፊሊፒኖ ማኅበረሰብ ውስጥ የሲቪክ መሪ የሆኑት ቴሬሲታ አንግ ሴ “ባምባን በመሰለ ቦታ ምን ልትሰልል ትችላለች? በማዕከላዊ ሉዞን ውስጥ ነው ያለው። ከየትኛውም ምስጢራዊ ተቋማት አቅራብያ አይደለም የሚገኘው፤ ለምን እርሷን ትጠቀማለች? ለእይታ የተጋለጠች ናት፣ አኗኗሯ ዓይን ገብ ነው። ለስለላ የምትጠቀመው የመጨረሻው ሰው እንደ አሊስ ጉኦ ያለ ነው” ብለዋል።

እአአ በ2024 አጋማሽ ላይ ፕሬዘዳንት ማርኮስ የተደራጀ ወንጀል መስፋፋቱን በመጥቀስ በሁሉም አቋማሪ ድርጅቶች ላይ እገዳ ጣሉ።

የምክር ቤት አባሉ ጋቻሊያን በአሊስ ጉኦ ላይ የተደረገው ምርመራ ይህንን የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ የበለጠ እንዲረዳ እንዳደረገው ይናገራል።

“በዚህ ምክንያት አቋማሪዎች እንዲታገዱ የሚወተውቱ ነበሩ፤ እናም ፕሬዚዳንቱ አቋማሪዎችን በይፋ ያገዱትያኔ ነው።”

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የፊሊፒንስ ፖሊሶች በመላ አገሪቱ በርካታ የሳይበር ወንጀል ካምፖች በቁጥጥር ስር አውለዋል።

ነገር ግን አቋማሪ ድርጅቶቹ እጃቸው ረዥም መሆኑ እንዲሁም በፀጥታ ኃይሉ መካከል ሰርገው በመግባት መረጃ ሾልኮ እንዲደርሳቸው በማድረግ የመንግሥት ተቋማት ወንጀለኞች ከመያዛቸው በፊት እንዲያመልጡ ማድረጋቸውን ዴ ላ ፓዝ ተናግሯል።

ቤኬማ በመጪው አገራዊ ምርጫ አንዳንድ እጩዎች አሁንም ከአቋማሪዎች በተገኘ ገንዘብ እየተደገፉ እንደሚገኙ ትጠራጠራለች።

በባምባን የመንግሥት ሰርጎ ገቦች ስጋት ከነዋሪዎቹ አእምሮ የራቀ ይመስላል።

ለመጪው የከተማዋ ከንቲባነት የሚወዳደሩ መንገዱን በደማቅ ቀለም ባሸበረቁ የቅስቀሳ ፖስተሮች አሸብርቀውታል።

ጉኦ በአሁኑ ጊዜ አስርት ዓመታት የሚያስፈርዱባት እና የመንግሥት ቢሮን ዳግመኛ እንዳትይዝ ሊያደርጓት የሚችሉ ስድስት የተለያዩ ክሶች ቀርበውባታል።

በሰዎች ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት ተከራክራለች።