የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ

ከ 3 ሰአት በፊት

ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ በጥቁር ባሕር ላይ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማክበር ማዕቀብ ይነሳልኝ ስትል ያቀረበችውን ቅድመ ሁኔታ በመቃወም፣ አሜሪካ በእነዚህ ፍላጎቶች ፊት “ጠንካራ ሆና ትቆማለች” የሚል እምነት እንዳላቸው ተናገሩ።

ሞስኮው የንግድ መርከቦች ደህንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴን እንዲያደርጉ ለመፍቀድ ማክሰኞ ዕለት የተደረሰው የባሕር ላይ ስምምነት ተግባራዊ የሚሆነው የምዕራቡ ዓለም በሩሲያ የምግብ እና የማዳበሪያ ንግድ ላይ የጣለው እገዳ ከተነሳ ብቻ ነው ብላለች ።

ዜሌንስኪ ይህንን ያሉት በፓሪስ ከአውሮፓ ለተሰባሰቡ ጋዜጠኞች ቃለ ምልልስ በሰጡበት ወቅት ነው።

ቢቢሲ፤ አሜሪካ የሩስያን ጫና ትቃወም እንደሆነ ላቀረበው ጥያቄ ፕሬዝደንቱ ሲመልሱ “ተስፋዬ እንደዚህ ነው። ፈጣሪ ይባርካቸው። ግን እናያለን” ብለዋል።

ኋይት ሐውስ ባለፈው ማክሰኞ እንዳስታወቀው የሩሲያ እና የዩክሬን ልዑካን በሳዑዲ አረቢያ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ለሦስት ቀናት የተናጠል ውይይት ካደረጉ በኋላ በጥቁር ባሕር ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምተዋል።

ከሰዓታት በኋላ ግን ክሬምሊን የቅድመ ሁኔታዎች ዝርዝር የያዘ መግለጫ አውጥታለች።

ከቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል በግብርና ንግድ ላይ በተሰማሩ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ምዕራባውያን ያስቀመጧቸው ማዕቀቦች እንዲሰረዙ እና የስዊፍት ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓትን ዳግም መልሶ መጠቀም መቻል የሚሉት ይገኙበታል።

ትራምፕ መንግሥታቸው ሞስኮው ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ ያቀረበችውን ጥያቄ “እየተመለከትነው ነው” ቢሉም፣ የአውሮፓ ኅብረት ግን ረቡዕ ዕለት የሩስያ ወታደሮች ከዩክሬን ግዛት “ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ” ካልወጡ በስተቀር ማዕቀቡን እንደማያነሱ ተናግረዋል።

ዜሌንስኪ በፓሪስ ለተሰበሰቡ ጋዜጠኞች ሲናገሩ አሜሪካ ለምታደርገው የሁለትዮሽ ድጋፍ “በጣም አመሰግናለሁ” ብለዋል።

ነገር ግን አንዳንዶች “በሩሲያ ትርክት ተጽዕኖ ስር ናቸው” ብለው እንደሚሰጉ አልሸሸጉም።

“በእነዚያ ትርክቶች መስማማት አንችልም” ሲሉም አክለዋል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከእርሳቸው ወይም ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንደነበራቸው ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ዜሌንስኪ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

“አላውቅም ፤ እንዲህ ነው ማለት ይከብደኛል” ብለዋል። “ምን ዓይነት ግንኙነቶች እንዳሏቸው አላውቅም፤ ምን ያህል ጊዜ እንደተወያዩ አላውቅም።”

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ባለፈው ሳምንት የትራምፕ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በአንድ ቃለ ምልልስ ላይ አውሮፓ ዩክሬንን ለመደገፍ “የፈቃደኞች ጥምረት” ለመመስረት የምታደርገውን ጥረት ስለማጣጣላቸው ያላቸውን አስተያየት ተጠይቀዋል ።

ዜሌንስኪ “በችኮላ ድምዳሜ” ላይ እንደማይደርሱ ተናግረው፣ ዊትኮፍ ያላቸው ልምድ በመኖሪያ ቤቶች ልማት ላይ መሆኑን በመጥቀስ “ልምድ አልነበራቸውም” ብለዋል።

“እኔ እስከማውቀው ድረስ ሪል እስቴት እንዴት እንደሚገዛና እንደሚሸጥ ጠንቅቆ ያውቃል፤ ነገር ግን ይህ በተወሰነ መልኩ የተለየ ነው” ብለዋል።

አውሮፓ በጦርነቱ ወቅት “ራሷን በተሻለ ሁኔታ አጠናክራለች” ሲሉም አክለዋል።

ቢቢሲ ዜሌንስኪ በታሪክ ውስጥ እንዴት መታወስ አንደሚፈልጉ ጠይቋቸው ሲመልሱም “የታሪክ መጻሕፍት ስለ እኔ ምን እንደሚጽፉ አላውቅም፤ ያ ዓላማዬ ወይም ግቤ አይደለም” ሲሉ ምለሽ ሰጥተዋል።

ዓላማቸው ዩክሬንን መከላከል እና ልጆቻቸው “ሳይደብቁ በዩክሬን ጎዳናዎች ላይ ሲሄዱ” ማየት እንደሆነ ተናግረዋል።

“ዩክሬንን በተቻለኝ መጠን ለመከላከል እስከ ዘመኔ መጨረሻ ድረስ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ” ሲሉም አክለዋል።

ዩክሬን የሰሜን ጦር ቃልኪዳንን (ኔቶ) እንድትቀላቀል ይፈቀድላት ወይስ አይፈቀድላት በሚለው ጉዳይ ላይ ዜሌንስኪ ሲመልሱ፣ የትራምፕ አስተዳደር የኪዬቭ አባልነትን እንደማይቀበለው ቢያስታውቅም “በትግል የጠነከረው” ሕዝባቸው ጥምረቱን ያፈረጥመዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ቃለ ምልልሱ የተካሄደው ዜሌንስኪ የፈረንሳዩን ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን በፓሪስ ካገኙ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነበር።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ወደ አውሮፓ የመጡት አጋሮቻቸውን የፑቲንን ስጋት በቁም ነገር እንዲመለከቱት ለማሳመን ነው።

የፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ የመጀመርያ ፈተና አውሮፓውያን ከቃላት ይልቅ በገንዘብ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ማስቻል ነው።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት በጦርነት ለተጎዳችው ዩክሬን 2 ቢሊዮን ዩሮ ወታደራዊ ዕርዳታ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ክሬምሊን ማዕቀብ እንዲነሳላት ላቀረበችው ጥያቄ ማክሮን በሰጡት ምላሽ ሞስኮ ለሰላም ” ቅድመ ሁኔታዎችን መወሰን” እንደማትችል በመግለጽ፣ አውሮፓውያን በሩሲያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ማንሳት ለማሰብ ጊዜው በጣም ገና ነው ብለዋል ።