በመጀመሪያው የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን ዘመናቸው ቲክ ቶክ እንዲታገድ የጠየቁት ዶናልድ ትራምፕ አሁን  አካውንት ከፍተው ቪዲዮዎችን መጫን ጀምረዋል

ከ 3 ሰአት በፊት

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በባይትዳንሰ ባለቤትነት የተያዘው ቲክቶክን ለመሸጥ ከስምምነት ለመድረስ ለቻይና የታሪፍ ቅናሽ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተናገሩ።

ትራምፕ ቻይናዊ ያልሆኑ ገዢዎችን ለማግኘት በሚል መጋቢት 27 2017 ዓ.ም. ድረስ ተቀምጦ የነበረውን ቀነ ገደብ ለማራዘም ፈቃደኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ፕሬዝደንቱ ወደ ስልጣን እንደመጡ በጆ ባይደን አስተዳደር ቲክቶክን ለማገድ ወጥቶ የነበረው ሕግ ተግባራዊነቱ እንዲዘገይ አድርገው ነበር።

እአአ በ2024 የጸደቀው ሕግ የብሔራዊ ደህንነት ስጋቶችን በመጥቀስ የቲክቶክ ባለቤትነት በሽያጭ ወደሌሎች እንዲተላለፍ ወይም እንዲታገድ ሲል መወሰኑ ይታወሳል።

ትራምፕ ረቡዕ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “ከቲክ ቶክ ጋር በተያያዘ ቻይና በዚህ ውስጥ ሚና መጫወት ይኖርባታል፣ ተሳትፎዋ በማፅደቅ ነው የሚሆነው፤ ያንን ያደርጋሉ ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።

“ምናልባት ታሪፍ ላይ ትንሽ ቅነሳ ወይም ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ አንድ ነገር እናደርጋለን” ሲሉ አክለዋል።

ትራምፕ መጋቢት 27 2017 ዓ.ም. ቢያንስ የስምምነቱ ዝርዝር ሁኔታ ላይ ይደረሳል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል ።

ዶናልድ ትራምፕ ይህንን ያሉት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሁሉም መኪኖች እና የመኪና መለዋወጫዎች ላይ የ25 በመቶ አዲስ ታሪፍ ከጣሉ በኋላ ነው ።

ቢቢሲ ቲክ ቶክን እና በዋሽንግተን የሚገኘውን የቻይና ኤምባሲ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት የጠየቀ ቢሆንም ምላሽ አላገኘም።

በአስር ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመተውን ቲክ ቶክን ለመሸጥ ስምምነት ላይ ለመድረስ ትልቁ ተግዳሮት የቤጂንግ ይሁንታን ማግኘት ነው።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም በድርድር ለማሸነፍ ታሪፍን እንደማስፈራርያ ተጠቅመው ያውቃሉ።

ፕሬዝዳንቱ በጥር ወር መጨረሻ ላይ ወደ ኋይት ሐውስ በተመለሱበት የመጀመሪያ ቀን ቻይና የቲክ ቶክ ስምምነትን ካላፀደቀች ተጨማሪ የአስመጪ ቀረጦችን እንደሚጥሉ አስፈራርተዋል።

ታዋቂው የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ በአሜሪካ ብቻ 170 ሚሊዮን ሰዎች ይጠቀሙታል።

በመጀመሪያው የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን ዘመናቸው ቲክ ቶክ እንዲታገድ የጠየቁት ዶናልድ ትራምፕ አሁን አካውንት ከፍተው ቪዲዮዎችን መጫን ጀምረዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ከ15 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሏቸው ሲሆን በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘመቻው ወቅት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ እይታዎችን አግኝተዋል።

አሜሪካ በዚህ ወር ከቻይና በሚገቡ ሁሉም ምርቶች ላይ 20 በመቶ ቀረጥ መጣሏ ይታወሳል።

ቤጂንግ የተለያዩ የአሜሪካ የአቪዬሽን፣ የመከላከያ እና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን “የማይታመኑ ተቋማት ዝርዝር” ውስጥ በማስገባት የወጪ ንግድ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ላይ አተኩራለች።

ቻይና በተቻለ ፍጥነት አሜሪካ ከቤጂንግ ጋር ለውይይት እንድትቀመጥ ጠይቃለች።