
ከ 5 ሰአት በፊት
የሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ፣ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ጦራቸው በካርቱም የሚገኘውን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ካስለቀቀ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ “ካርቱም ነጻ ናት” ሲሉ አወጁ።
ጄነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ጦሩ በካርቱም የሚገኘውን የአገሪቱን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከተቆጣጠረ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በስፍራው የደረሱ ሲሆን፣ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥቱንም ጎብኝተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በስፍራው እንደደረሱ ደስታቸውን በሚገልጹ የአገሪቱ ጦር አባላት የተከበቡ ሲሆን፣ ዋና ከተማዋ ከፈጣን ደራሽ ኃይሉ አማፂያን እጅ “ነጻ” መውጣቷንም አውጀዋል።
“ካርቱም ነጻ ናት፣ አብቅቷል” ሲሉ ተናግረዋል።
ጦርነቱ ከጀመረ ከሁለት ዓመት ወዲህ ቡርሃን በፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት ሲገኙ ይህ የመጀመሪያቸው እንደሆነ ይታመናል።
የእርስ በእርስ ጦርነቱ እንደ ጀመረ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ዋና ከተማዋን የተቆጣጠረ ሲሆን በሀገሪቱ ጦር የሚመራው መንግሥት መቀመጫውን በቀይ ባህር ወደሚገኘው ፖርት ሱዳን ለማዞር ተገድዷል።
ቀደም ሲል አንድ የጦር አዛዥ ወታደሮቻቸው የአየር ማረፊያውን ሙሉ በሙሉ እንደተቆጣጠሩ እና የቀራቸው በየስፍራው የተንጠባጠቡትን የፈጥኖ ደራሽ ተዋጊዎችን ማጽዳት እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
አርብ እለት የአገሪቱ ጦር የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት በድጋሚ ከተቆጣጠረ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ስር የነበሩ ሌሎች የመንግሥት ተቋማትን ካስለቀቀ በኋላ በከተማዋ ያለውን ኃይል እያጠናከረ መጥቷል።
ጦርነቱ እአአ በሚያዝያ 2023 ከተጀመረ ወዲህ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ፣ የዋና ከተማዋ ካርቱምን አብዛኛውን ክፍል ተቆጣጥሮ ነበር።
በእርስ በርስ ጦርነቱ በአጠቃላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሲገደሉ፣ ሚሊዮኖች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል።
- የሱዳን ጦር በዳርፉር ገበያ ላይ ባደረሰው ጥቃት በመቶዎች መገደላቸው ተነገረ26 መጋቢት 2025
- ካርቱምን ለመቆጣጠር በሚደረገው ፍልሚያ አምስት ቁልፍ ጉዳዮች25 መጋቢት 2025
- የሱዳን ጦር የፕሬዚደንቱን ቤተ መንግሥት መልሶ መቆጣጠሩ የአገሪቱን ጦርነት አቅጣጫ ይቀይራል?22 መጋቢት 2025
የጦሩ ቃል አቀባይ በተጨማሪም የአገሪቱ ጦር ኃይል በናይል ወንዝ ላይ የሚገኙትን እና በደቡባዊ ካርቱም፣ ጀበል አውሊያ የሚገኘውን ወታደራዊ ካምፕ ጨምሮ ሦስት ከተሞችን የሚያገናኙትን ድልድዮች መልሰው መያዛቸውን ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ በዚህ ሳምንት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች ወደ ደቡብ አቅጣጫ፣ በጀበል አውሊያ ወታደራዊ ካምፕ አቅጣጫ፣ እያፈገፈጉ መሆኑን ሲናገሩ ነበር።
በሠራዊቱ የተለቀቀው እና በሰው አልባ አውሮፕላን የተነሳው ተንቀሳቃሽ ምስል ሰዎች በግድቡ ላይ ባለው ድልድይ ሲያቋርጡ ያሳያል።
ቢቢሲ የሚያቋርጡት እነማን እንደሆኑ ማረጋገጥ ባይችልም ወታደራዊ ኃይሉ ግን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች ካርቱምን ለቅቀው ሲሸሹ እንደሚያሳይ ተናግሯል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቁት ቪዲዮዎች በማዕከላዊ ካርቱም የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አገዛዝ አብቅቶ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ወደ ከተማዋ መግባቱ የፈጠረባቸውን ደስታ ሲገልጹ ያሳያሉ።
ከተማዋን ለቅቀው መውጣት ያልፈለጉ ወይም ያልቻሉ ነዋሪዎች በፈጥኖ ደራሽ አማፂያን ኃይሎች የጅምላ ዝርፊያ እንደተፈጸመባቸው ሪፖርት ተደርጓል።
ካርቱም፤ ገበያዎች በመዘረፋቸው እና በሁለቱ ተዋጊዎች እርዳታ እንዳይገባ በመከልከሉ የተነሳ የተባበሩት መንግሥታት ረሃብ እየተቃረበ ነው ካለባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች አንዷ ናት።
የመብት ተሟጋቾች በከተማዋ የተፈጸሙ ጾታዊ እና ሌሎች ጥቃቶችን ሰንደዋል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና ጦር ሰራዊቱ ያለልዩነት የሲቪል መኖርያዎች ላይ ድብደባ ፈጽመዋል በሚል ተከስሰዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የአገሪቱ አየር ኃይል በገበያ ላይ በፈጸመው ድብደባ በርካቶች መሞታቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
ካርቱምን መልሶ መያዝ ለሠራዊቱ ትልቅ ስኬት ሲሆን በጦርነቱ ውስጥ ስልታዊ ጥቅም ሊሰጠው ይችላል ተብሏል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አሁንም በምዕራብ ሱዳን የሚገኘውን ሁሉንም የዳርፉር ክልል የሚቆጣጣር ሲሆን በአገሪቱ የሚካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ገና አልተጠናቀቀም።
ሁለቱም ተዋጊ ወገኖች በውጭ ኃይሎች የሚደገፉ ሲሆን የጦር መሳሪያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በገፍ ይገባል።
በአገሪቱ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት እስካሁን አልተሳካም።
