March 28, 2025

በቤርሳቤህ ገብረ

የፌደራል ፖሊስ “በሽብር ወንጀል ጉዳይ” ጠርጥሬያቸዋለሁ ያላቸውን አምስት የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰራተኞችን በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት አቀረበ። ጉዳዩ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ፖሊስ በጠየቀው የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ላይ ብይን ለመስጠት ለመጪው ሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የፌደራል ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮውን የጠየቀው፤ በስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ እያካሄደ ያለውን የምርመራ ስራ “በሰው እና በሰነድ ማስረጃ በስፋት ለማጣራት” በሚል ነው። ከስምንቱ ተጠርጣሪዎች ውስጥ ባለፈው ሳምንት እሁድ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ በተሰራጨ ዝግጅት ላይ “የሀሰት ታሪኳ” ቀርቧል የተባለው ብርቱካን ተመስገን ትገኝበታለች።

የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና ስራ አስኪያጅ እና የመገናኛ ብዙሃኑ አንዱ ባለድርሻ የሆኑት አቶ ነብዩ ጥዑመልሳንም በተጠርጣሪነት ፍርድ ቤት ቀርበዋል። በቴሌቭዥን ጣቢያው በፕሮግራም ዳይሬክተርነት የሚሰራው ጋዜጠኛ ታሪኩ ኃይሌ፣ የስቱዲዩ ዳይሬክተሩ አቶ ንጥር ደረጀ፣ ረዳት የፕሮግራም አዘጋጇ ህሊና ታረቀኝ እና የካሜራ ባለሙያ የሆነው ቶማስ ደመቀም ፍርድ ቤት ቀርበው የዛሬውን ሂደት ተከታትለዋል።


በመጋቢት 17፤ 2017 ዓ.ም. በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ከተገለጸው ተጠርጣሪዎች ውስጥ ሁለቱ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 14 በኃላፊነት ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው። ፖሊስ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ዛሬ አርብ መጋቢት 19 ያቀረበው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ማመልከቻ፤ ስምንቱ ተጠርጣሪዎች “በሽብር ወንጀል ጉዳይ” እንደተጠረጠሩ ይገልጻል።  

ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን የፈጸሙት “የጦር መሳሪያ በመታጠቅ፣ በህገ ወጥ መንገድ በመደራጀት” በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ከተባለው “ጽንፈኛ” እና “ጸረ ሰላም” ቡድን አመራሮች ጋር “በጥቅም በመተሳሰር” እንደሆነ የፌደራል ፖሊስ በማመልከቻው ላይ አስፍሯል። ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ውጭ ሀገር ከሚገኙ “የጸረ-ሰላም ቡድኑ አመራሮች” ጋር” የተለያዩ መገናኛ መንገዶችን ተጠቅመው “ተገናኝተዋል፤ ተልዕኮ ተቀብለዋል” ሲል ወንጅሏል።  

ወንጀሉ የተፈጸመው “መንግስት የህዝብ ተቀባይነት እንዲያጣ እና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ እንዲያድርበት በማሰብ” እንደሆነ ፖሊስ በማመልከቻው ላይ ጠቅሷል። ተጠርጣሪዎቹ “በብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መካከል ቅራኔ በመፍጠር ወደ ግጭት እንዲገቡ ለማድረግ” ተልዕኮ መቀበላቸውንም ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል።

አምስቱ የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰራተኞች “የስራ ባህሪያቸውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም”፤ “ማህበራዊ ሚዲያዎች እና የብሮድካስት መገናኛ ዘዴ በመጠቀም” ሀሰተኛ ዶክመንተሪ ፊልም በማዘጋጀት እና በማሰራጨት ፖሊስ ወንጅሏቸዋል። እነዚህ ተጠርጣሪዎች ፖሊስ በማመልከቻው ላይ በቀዳሚነት የጠቀሳት ብርቱካን ተመስገን፤ “የደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳትሆን እንደሆነች” እና “ለትምህርት በሄደችበት ቦታ በአጋቾች ታግታ የአስገድዶ መድፈር የተፈጸመባት ሴት ናት በማለት” “የሀሰት ታሪክ ለህዝብ እንዲደርስ አድርገዋል” የሚል ውንጀላም ቀርቦባቸዋል። 

ተጠርጣሪዎቹ “እራሳቸው ደራሲ እና ተራኪ በመሆን” “ምንም አይነት ጥቃት ያልደረሰባትን ሴት”፤ “የአስገድዶ መደፈር ጥቃት እንደተፈጸመባት በማስመሰል” ቃለ መጠየቅ በማድረግ “በርካታ ህዝብ በሚከታተለው” ኢቤኤስ ቴሌቭዥን ጣቢያ አቅርበዋል ሲል ፖሊስ በማመልከቻው አትቷል። የቴሌቪዥን ጣቢያው ሰራተኞች “ጥቃቱን ለማግዘፍ እና በህዝብ ዘንድ ቅሬታና አመጽ እንዲቀሰቀስ ለማድረግ” ያዘጋጁትን “ሀሰተኛ ዶክመንተሪ ፊልም”፤ “በገለጻና ማብራሪያ እንዲሁም በምስል አስደግፈው” ማቀረባቸውንም ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። 

ተጠርጣሪዎቹ ፈጥረውታል በተባለው “ፍጹም ሀሰት የሆነ ታሪክ”፤ “በህዝቦች መካከል መቃቃር እንዲፈጠርና ግጭት እንዲቀሰቅስ በማድረግ” በዚህ ውጤት “ህገ መንግስቱ እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ ለመጣል” ሲንቀሳቀሱ በጸጥታ ኃይሎች መያዛቸውን ፖሊስ በማመልከቻው ገልጿል። የፌደራል ፖሊስ በማመልከቻው ማጠቃለያ ላይ፤ ተጠርጣሪዎቹ “በህዝብ አመኔታ አግኝቶ የተመረጠን መንግስት በኃይል አስገድዶ ከስልጣን ለማውረድ” ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውንም አክሏል።

የፌደራል ፖሊስ በማመልከቻው ማጠቃለያ ላይ፤ ተጠርጣሪዎቹ “በህዝብ አመኔታ አግኝቶ የተመረጠን መንግስት በኃይል አስገድዶ ከስልጣን ለማውረድ” ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን ገልጿል።

የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰራተኞች እነዚህን የፖሊስን ውንጀላዎች በራሳቸው አንደበት እና በጠበቆቻቸው በኩል ባቀረቧቸው መከራከሪያዎች አስተባብለዋል። ጋዜጠኛ ታሪኩን እና ረዳት የፕሮግራም አዘጋጇ ህሊናን የወከሉ ጠበቆች፤ ደንበኞቻቸው ቢጠረጠሩ እንኳን በሽብር ወንጀል ሳይሆን፤ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣ አዋጅ ላይ ባሉ ድንጋጌዎች መሆን እንደሚገባው ተከራክረዋል። 

የኢቢኤስ ቴሌቪዥን  ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ነብዩን እና ሌሎች ሁለት የጣቢያውን ሰራተኞች የወከሉ ጠበቆች በበኩላቸው ደንበኞቻቸው “ከሽብር ወንጀል ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም” ብለዋል። ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ የሆነው የካሜራ ባለሙያ ቶማስ ደመቀ፤ ቀረጻው በተከናወነበት ጊዜ በ“እረፍት ላይ እንደነበርም” በጠበቆቹ መከራከሪያ ላይ ተነስቷል።

ጠበቆቹ በዚሁ መከራከሪያቸው ደንበኞቻቸው የተጠረጠሩበት ጉዳይ፤ በመርህ ደረጃ በወንጀል ህጉ “በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት በሚደረጉ ወንጀሎች ተካፋይ መሆን” በተዘረዘረበት ክፍል ላይ ሊወድቅ የሚችል እንደሆነ አስረድተዋል። “በዚህ ደረጃ የወንጀል ኃላፊነት የሚያስከትለው ማን ላይ ነው? የሚለው በወንጀል ህጉ ላይ ተመልክቷል። ኃላፊነቱ የሚያርፈው አንድ [ግለሰብ] ላይ ነው። ይሄም የፕሮግራም ኃላፊ ነው” ሲሉ ከጠበቆቹ አንዱ ተከራክረዋል። 

በዚህ መሰረት ጠበቆቹ የወከሏቸው ሶስቱ የኢቤኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰራተኞች “የወንጀል ህጉ ሊያርፍበት ይችላል ከሚባለው ውጭ ናቸው” የሚል መከራከሪያም አቅርበዋል። ጠበቆቹ በመከራከሪያቸው ማጠቃለያ የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲጠበቅ ጠይቀዋል።

የጠበቆቹን መከራከሪያ ተከትሎ የመናገር ዕድል እንዲሰጣቸው የጠየቁት የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ፤ ስሜት በተሞላበት እና እንባ በተናነቀው ድምጸት በምርመራ ሂደት ውስጥ የነበራቸውን “ትብብር” ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ለምርመራ ሂደቱ የሚያግዙ የቪዲዮ ማስረጃዎች እና የሰራተኞችን ዝርዝርን የያዘ ሰነድ ለፌደራል ፖሊስ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። 

ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ወደ ቴሌቪዥን ጣቢያው ሲደርሱ ቅጽር ግቢው በጸጥታ ኃይሎች ተከብቦ ማግኘታቸውን አቶ ነብዩ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። የጸጥታ ኃላፊዎች ከመጡ በኋላ ሰራተኞች ከጣቢያው ህንጻ መውጣታቸውን እና የቴሌቪዥን ጣቢያውን ቻናሎች “በአንድ መርማሪ” ትዕዛዝ እንዲያጠፉ መደረጋቸውን አብራርተዋል።

ፎቶ፦ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተወሰደ

“የሚሊዮን ህዝብን ቻናልን አጥፍተናል። ‘ይህ political implication አለው’ ስል ማንም አልሰማኝም” ሲሉ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ለፍርድ ቤት የገለጹት አቶ ነብዩ፤ “አሁን ቻናሉ በመከፈቱ ደስ ብሎኛል” በማለት ስሜታቸውን አጋርተዋል። እርሳቸው በመታሰራቸው ለሰራተኞች ደመወዝ የሚከፍል እንደሌለ እና የዕለት ተዕለት የጣቢያው ስራም መስተጓጉሉንም ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል። 

ፖሊስ በማመልከቻው በጠቀሰው የቴሌቪዥን ፕሮግራም፤ በቅድመ ዝግጅት፣ በቀረጻ ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበረው ሂደት እርሳቸው ድርሻ እንዳልነበራቸው ለፍርድ ቤቱ የገለጹት አቶ ነብዩ፤ መታሰራቸው ትክክል እንዳልሆነ ተናግረዋል። ስራ አስኪያጁ በንግግራቸው መቋጫ፤ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል።

እንደ አቶ ነብዩ ሁሉ የመናገር ዕድል የተሰጠው የቴሌቪዥን ጣቢያው ፕሮግራም ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ታሪኩ፤ በፖሊስ ማመልከቻ ላይ የተጠቀሰው የቴሌቪዥን ፕሮግራም የተሰራበትን ሂደት ለፍርድ ቤት አስረድቷል። ፕሮግራሙ “የጋዜጠኝነት ስራ” መሆኑን የገለጸው ታሪኩ፤ “የፖለቲካ አጀንዳ” አንስቶ እንደማያውቅም አመልክቷል። 

“ተራ የቢሮ ተከፋይ ደመወዝተኛ ነኝ። ስለዚህ ተበዳይ ብርቱካንን በማታለል፤ ምንም ጥቅም የማገኝ አይደለሁም። ሙያዬን ነው እዚያ ጋር የሰራሁት” ሲልም ታሪኩ ተናግሯል። የፕሮግራም ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የእስረኞች ማቆያ “በጨለማ ክፍል” ታስሮ እንደሚገኝ እና “እዚያው እንደሚጸዳዳ” ለፍርድ ቤቱ አቤት ብሏል።

ይህን ተከትሎ የመርማሪ ፖሊስ ባቀረበው የማጠቃለያ ንግግር፤ ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ የ14 ቀን የምርምራ ማጣሪያ የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቅድለት ጠይቋል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፖሊስ ባቀረበው የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት፤ ጅምር የምርመራ መዝገቡ በመጪው ሰኞ ጠዋት እንዲቀርብለት ትዕዛዝ ሰጥቷል። 

ፍርድ ቤቱ በመጪው ሰኞ መጋቢት 22፤ 2017 ከሰዓት በሚኖረው የችሎት ውሎ ጥያቄን መርምሮ ብይን እንደሚሰጥም አስታውቋል። የዛሬውን ችሎት የጠዋት ክፍለ ጊዜ የተጠርጣሪ ቤተሰቦች እንዲታደሙ ቢደረጉም፤ እስከ 11 ሰዓት በቆየው የከሰዓቱ ክፍለ ጊዜ ግን “በቦታ ጥበት ምክንያት” ሂደቱን ሳይከታተሉ ቀርተዋል።   

በዛሬው የችሎት ውሎ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰራተኞች አምስት ቢሆኑም፤ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጨማሪ ስድስት የጣቢያው ሰራተኞች በፍርድ ቤት ተገኝተው እንደነበር ባልደረቦቻቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በቁጥጥር ስር የሚገኙ የሌሎች የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰራተኞች ጉዳይ፤ በመጪው ሰኞ በአንድ መዘገብ ተካትቶ በጋራ እንደሚታይ ፖሊስ ለችሎቱ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል። የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ተስፋለም ወልደየስ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል]