
31 መጋቢት 2025
በክልሎች የሚቋቋም ጊዜያዊ አስተዳደር የሥልጣን ዘመን፤ ለሁለት ጊዜ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ እንዲራዘም የሚያስችል የአዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ በነገው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሊጸድቅ ነው።
የአዋጅ ማሻሻያ ረቂቁ፤ ከዚህ ቀደም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣን የነበረውን የክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቆይታ ጊዜን የማራዘም ኃላፊነት፤ ለምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ይሰጣል።
እነዚህ አዲስ ድንጋጌዎች የተካተቱት በ1995 ዓ. ም. የወጣውን የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት የሚደነግግ አዋጅ ለማሻሻል በተዘጋጀ ረቂቅ ሕግ ላይ ነው።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ማክሰኞ 23/2017 ዓ. ም. በሚያደርገው ስብሰባ ላይ ቀርቦ የሚጸድቀው ይህ አዋጅ፤ የሥልጣን ዘመኑ የተጠናቀቀው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሥልጣን ዘመን ለተጨማሪ ዓመት እንዲራዘም የሚያስችል ነው።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጊዜያዊ አስተዳደር የተመሰረተው በ2015 ዓ. ም. የወጣውን ማቋቋሚያ ደንብ መሠረት አድርጎ ነው።
ጊዜያዊ አስተዳደሩን ያቋቋመው ደንብ ደግሞ መሠረት ያደረገው ከ22 ዓመት ገደማ በፊት የጸደቀውን የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት የሚደነግግ አዋጅ ነው።
ይህ አዋጅ የፌደራል መንግሥት በሦስት ሁኔታዎች በክልሎች ውስጥ ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል ደንግጓል።
በቀዳሚነት የተጠቀሰው ምክንያት በክልሉ ውስጥ የሚፈጠር የጸጥታ መደፍረስ ሲሆን በዚህ ጊዜ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የክልሉ መንግሥት ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል።
በክልሉ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰት ከተፈጸም እና የክልሉ መንግሥት ድርጊቱን በቁጥጥሩ ሥር ማዋል ካልቻለም ፌደራል መንግሥት ጣልቃ ይገባል።
በአዋጁ ላይ የተጠቀሰው ሦስተኛ ሁኔታ፤ እንደ “በትጥቅ የተደገፈ የአመጽ እንቅስቃሴ” ያሉ ድርጊቶች በሚፈጸሙበት ወቅት የሚከሰት “የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አደጋ ላይ መውደቅ” ነው።
በእነዚህ ሁኔታዎች መከሰት ምክንያት ወደ በክልሎች ጣልቃ የሚገባው የፌደራል መንግሥት ሊያከናውን ከሚችላቸው ጉዳዮች መካከል “የክልሉን ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል በማገድ ለፌደራል መንግሥት ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር” ማቋቋም የሚለው ይገኝበታል።
በዚህ መልኩ የሚቋቋም ጊዜያዊ አስተዳደር የሚቆየው ከሁለት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ እንደሆነ አዋጁ ደንግጓል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጊዜያዊ አስተዳደሩን የቆይታ ጊዜ ማራዘም “አስፈላጊ ሆኖ” ካገኘው “ከስድስት ወር ላልለጠ ጊዜ” ሊያራዝመው እንደሚችልም በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።
- የትግራይ ክልል ቀውስ፡ ከፕሪቶሪያ ወዲህ መቼ ምን ተከሰተ?15 መጋቢት 2025
- በደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የእጩ ጥቆማ ጥሪ “የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ” ነው አለ27 መጋቢት 2025
- ለትግራይ ከሌሎች ክልሎች “በተለየ ሁኔታ” ላለፉት 11 ቀናት ነዳጅ እንዳይጫን መደረጉ ተገለጸ26 መጋቢት 2025
ነገ በፓርላማ ለሚጸድቀው የአዋጅ ማሻሻያ የተዘጋጀው ማብራሪያ፤ በነባሩ ሕግ ላይ የተቀመጠው የሁለት ዓመት ከስድስት ወር የቆይታ ጊዜ “ከነባራዊው ሁኔታ ጋር የማይጣጣም” እንደሆነ ያትታል።
በክልሎች ውስጥ ለሚከሰቱ “እጅግ ውስብስብ የጸጥታና የፖለቲካ ችግሮች” መፍትሔ ለመስጠት የሚያስፈልገው ጊዜ “እንደ ጉዳዩ ክብደት ሊለያይ የሚችል” እንደሆነ ማብራሪያው ያስረዳል።
በአዋጁ ላይ በተቀመጠው “የጊዜ ገደብ ውስጥ የማይፈቱ እክሎችም” እንደተስተዋሉ በማብራሪያው ላይ ሰፍሯል።
ማብራሪያው፤ “ለአብነት በትግራይ ክልል ያለው ነባራዊ ሁኔታን መጥቀስ ይቻላል” ሲል ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላም ምርጫ አድርጎ መደበኛ ክልላዊ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ሁኔታ ያልተፈጠረበትን የትግራይ ክልል በማሳያነት ጠቅሷል።
ለፓርላማው የሚቀርበው አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ፤ በክልሎች ውስጥ የሚመሠረት የጊዜያዊ አስተዳደር የቆይታ ጊዜ ሁለት ጊዜ እንዲራዘም ያስችላል።
“በክልሉ ውስጥ የፌደራል መንግሥቱን ጣልቃ መግባት አስፈላጊ ካደረገው ሁኔታ ውስብስብነት አኳያ አስፈላጊ ሆኖ” ከተገኘ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የቆይታ ጊዜ እስከ አንድ ዓመት እንዲራዘም ሊደረግ እንደሚችል ረቂቁ ያመለክታል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ የቆይታ ጊዜ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲራዘም የሚያስፈልግ ከሆነም በድጋሚ “ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ እንዲራዘም” ሊደረግ እንደሚችል በረቂቁ ላይ ሰፍሯል።
በስራ ላይ ባለው አዋጅ በክልሎች ውስጥ የሚመሰረት ጊዜያዊ አስተዳደርን የቆይታ ጊዜ የማራዘም ስልጣን ፌዴሬሽንም ምክር ቤት እንደሆነ ደንግጓል።
አዲሱ ማሻሻያ ረቂቅ በበኩሉ ይህንን ስልጣን ወደ ምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አዘዋውሯል።
የጊዜያዊ አስተዳደርን የቆይታ ዘመን የማራዘም ውሳኔ የሚሰጠው አካል ጉዳይ በስራ ላይ ባለው አዋጅ “ትግበራ ሂደት ላይ ከተስተዋሉ ሁለት ችግሮች” አንዱ እንደሆነ የረቂቁ ማብራሪያ ያስረዳል።
ማብራሪያው፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚሰበሰበው “በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ” መሆኑን እንዲሁም የምክር ቤቱ አባላት “በየክልላቸው ከፍተኛና ተደራራቢ የመንግሥት ኃላፊነት” እንዳለባቸው ያትታል።
በዚህም ምክንያት “የጊዜያዊ አስተዳደር ቆይታን ማራዘም ሲያስፈልግ በአጭር ጊዜ ስብሰባ በመጥራት ውይይት አድርጎ ውሳኔ ለመሥጠት የሚያስቸግር” ሁኔታ መፈጠሩን ያብራራል።
“ስለሆነ የምክር ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ የምክር ቤቱ ስብሰባ እስኪደረግ ድረስ አፈ ጉባኤው የጊዜያዊ አስተዳደር የቆይታ ጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል” በማለት ማሻሻያው ያስፈለገበትን ምክንያት አስፍሯል።
የማሻሻያ ረቂቁ፤ የጊዜያዊ አስተዳደርን ቆይታ ጊዜ የማራዘም ስልጣንንን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቢሰጥም፤ ምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤውን በሚያካሂድበት ወቅት ውሳኔው ቀርቦ መጽደቅ እንዳለበት ይደነግጋል።
ምክር ቤት የሚቀርብለትን የቆይታ ጊዜ ማራዘም ውሳኔ ካልተቀበለው፤ “ውሳኔው ውድቅ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ በሚቆጠር አራት ወራት ጊዜ ውስጥ ምርጫ ተደርጎ መደበኛ የክልል መንግሥት አስተዳደር መመሥረት” እንደሚኖርበት በማሻሻያው ላይ ተካትቷል።
ጊዜያዊ አስተዳደር በተመለከተ በአፈ ጉባኤው በሚተላለፍ ወይም በምክር ቤቱ በሚጸድቅ ውሳኔ ውስጥ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ሊመላከቱ” እንደሚችሉ ማሻሻያው ያስረዳል።
እነዚህ ጉዳዮች “ለፌደራል መንግሥት ጣልቃ መግባት ምክንያት የሆነውን ሁኔታ በዘላቂነት ለመቅረፍ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማጽናት አስፈላጊ የሆኑ” ተግባራት እንደሚሆኑ ተጠቅሷል።

እነዚህን አዲስ አሠራሮች የሚያስተዋውቀው ረቂቅ አዋጅ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርበው ነገ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ ቢሆንም በዚሁ ጉባኤ ላይ እንዲጸድቅ ዕቅድ ተይዟል።
በመደበኛው አሠራር አዋጆች ለምክር ቤቱ ከቀረቡ በኋላ ጉዳዩን ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርተው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ይደረግባቸዋል።
ባለፉት ጊዜያት፤ ይህ መደበኛ አሠራር እንዲታለፍ የሚያስችሉ ሞሽኖች ቀርበው አዋጆች በቀረቡበት የምክር ቤት ጉባኤ ላይ ጸድቀዋል።
ነገ የሚቀርበውን ይህንን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተም ተመሳሳይ ሞሽን እንደሚቀርብ ይገመታል።
በተለመደው አሠራር የጸደቁ አዋጆች ሥራ ላይ የሚውሉት በነጋሪት ጋዜጣ ከታተሙበት ቀን ጀምሮ ነው።
ይህ የአዋጅ ማሻሻያ በአንጻሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን በረቂቁ ላይ ሰፍሯል።
ይህ ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤቱ የቀረበው ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን የቆይታ ጊዜ ለአንድ ዓመት የማራዘም እቅድ እንዳለ ካስታወቁ ከቀናት በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው በትግርኛ ባሰፈሩት ጽሑፍ በ2015 ዓ. ም. የተቋቋመው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የሁለት ዓመት የሥልጣን ዘመን ማብቃቱን ገልጸው ነበር።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ በሁለት ዓመት ቆይታው ሊሠራቸው ይገባ የነበሩ “ቁልፍ ተግባራቶች በወቅቱ ማከናወን እንዳልቻለ” ገልጸዋል።
ከእነዚህ ቁልፍ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በክልሉ መደበኛ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ምርጫ ለማካሄድ “ሁኔታዎችን ማመቻቸት” እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
በክልሉ ያለውን “ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት” የጊዜያዊ አስተዳደሩ የቆይታ ጊዜ በአንድ ዓመት እንደሚራዘም ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ የሚከናወነውም የሕግ ማሻሻያ ተደርጎ እንደሆነ ገልጸው ነበር።
በዚሁ መልዕክታቸው በአቶ ጌታቸው ረዳ ሲመራ ለቆየው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፤ ፕሬዝዳንት ለመሾም የትግራይ ሕዝብ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ማቅረባቸውም ይታወሳል።