March 31, 2025

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “በየሁለት ሳምንት” ልዩነት፤ መደበኛ እና “ተከታታይ” የውጭ ምንዛሬ ሽያጭ ጨረታ ማካሄድ” ሊጀምር እንደሆነ አስታወቀ። “የማዕከላዊ ባንኩን የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ግብ ለማሳካት” የታቀደ ነው የተባለለት ጨረታ፤ ነገ ማክሰኞ መጋቢት 23፤ 2017 ይጀመራል። 

በነገው ጨረታ 50 ሚሊዮን ዶላር ለሽያጭ የቀረበ ሲሆን፤ ፍላጎቱ ያላቸው ባንኮች ሰነዶቻቸውን እንዲያስገቡ ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ጥሪ አድርጓል። ጨረታው ከረፋዱ አራት ሰዓት እስከ እኩለ ቀን ስድስት ሰዓት ድረስ እንደሚካሄድ የገለጸው ብሔራዊ ባንክ፤ ውጤቱ ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቋል።

ይህ ጨረታ የውጭ ምንዛሬ ግብይት በባንኮች እና በደንበኞቻቸው ድርድር እንዲወሰን ከተደረገ ወዲህ ለሶስተኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው። ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ማከፋፈል የጀመረው፤ በሐምሌ 2016 ዓ.ም. ተግባራዊ ከተደረገው የውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት ለውጥ በኋላ ነው። 


በመስከረም 2017 ዓ.ም በተደረገው በመጀመሪያው ጨረታ የተሸጠው የውጭ ምንዛሬ መጠን 175 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ብሔራዊ ባንክ ይህን የውጭ ምንዛሬ የመደበው “ከነዳጅ ጋር ለተያያዙ የገቢ ሸቀጦች” እንዲውል ነበር። በየካቲት 2017 ዓ.ም በተካሄደው ጨረታ ብሔራዊ ባንክ 60 ሚሊዮን ዶላር የሸጠ ሲሆን፤ በሂደቱ 27 ባንኮች መሳተፋቸው በወቅቱ ተገልጿል።

በዚህ ጨረታ የአንድ የአሜሪካ ዶላር በ135 ብር ከ61 ሣንቲም ገደማ እንደተመነዘረ ብሔራዊ ባንክ ይፋ አድርጓል። ይህ መጠን በወቅቱ በባንኮች ከነበረው የምንዛሬ ተመን ከፍ ያለ ልዩነት የታየበት ነበር። 

ከዘጠኝ ወራት በፊት ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት ማሻሻያ፤ ብሔራዊ ባንክን በግብይቱ ውስጥ ከነበረው ጉልህ ሚና ያስወጣ ነው። ይህ አካሄድ ብሔራዊ ባንክ “የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ተመን እና ስርዓት እንዲኖር” እንዲሁም “ገበያን በማረጋጋት ላይ ያተኮረ” ሚና እንዲኖረው ማድረጉም ሲገለጽ ቆይቷል።


ማሻሻያው ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚታወቅበት የውጭ ምንዛሬ እጥረት፤ “መሰረታዊ በሚባል ደረጃ እየተቃለለ” መምጣቱን እና “የውጭ ምንዛሬ ፍሰት” እየጨመረ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ዛሬ ምሽት በቪዲዮ ባቀረቡት ማብራሪያ ላይ አመልክተዋል። የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ የመጠባበቂያ ክምችት “በእጅጉ” ለመሻሻሉ አቶ ማሞ በማሳያነት ያቀረቡት፤ መጠኑ ከሐምሌ 2016 ወዲህ ባሉት ዘጠኝ ወራት ከ200 ፐርሰንት በላይ ማደጉን ነው።

ነገ የሚጀመረው የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ “ተከታታይ ጨረታ”፤ “ግልጽ” እንደሚሆን እና ቢያንስ እስከ ዘንድሮው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ እንደሚቀጥል አቶ ማሞ ጠቁመዋል። ለጨረታ የሚቀርበው የውጭ ምንዛሬ መጠን፤ “በወቅቱ ያለውን የውጪ ምንዛሬ ፍላጎት በማገናዘብ” እንደሚሆንም የብሔራዊ ባንክ ገዢው አስረድተዋል።

በውጪ ምንዛሬ ግብይቱ ወቅት “የተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘዴዎችን በመጠቀም” “ጥብቅ ቁጥጥር” እንደሚደረግ አቶ ማሞ በዛሬው ማብራሪያቸው ላይ ጠቅሰዋል። ይህ ቁጥጥር “እንደ አስፈላጊነቱ” ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና ሌሎች የህግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር እንደሚካሄድ ተናግረዋል።


“የውጭ ምንዛሬ ግብይት ከባንክ ስርዓት ውጪ በሚያካሄዱ፣ የውጭ ምንዛሬ ወደ ውጪ ሀገር በሚያሸሹ፣ በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር በሚሳተፉ እና የብሔራዊ ባንክን የቁጥጥር እና የአሰራር ስርዓት በሚጥሱ ግለሰቦች፣ የሐዋላ ኩባንያዎች እና የገንዘብ አዘዋዋሪዎች ላይ ጥብቅ የክትትል እና የቁጥጥር እርምጃዎችን ይወሰዳል” ሲሉ የብሔራዊ ባንክ ገዢው ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥተዋል።  

ይህን ተከትሎም ህገ ወጥ እና ፈቃድ የሌላቸው ኩባንያዎች እንዲሁም ግለሰቦች፤ “ከኢትዮጵያ የባንክ ስርዓት ጋር ያላቸው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ” እንደሚደረግም አቶ ማሞ ይፋ አድርገዋል። የብሔራዊ ባንክ ገዢው በዚሁ የቪዲዮ ማብራሪያቸው፤ “ህጋዊ ፈቃድ ያላቸው” የሐዋላ ኩባንያዎች ስም ዝርዝር በመስሪያ ቤታቸው ድረ ገጽ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀው ነበር። 

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ድረ ገጽ በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው በዚህ ዝርዝር የተካተቱት 87 ኩባንያዎች ናቸው። ከዚህ ዝርዝር ውጪ ያሉት በሙሉ “ፈቃድ ያልተሰጣቸው” እንደሆኑ ህብረተሰቡ ተገንዝቦ፤ “ራሱን ከአደጋ ስጋት፣ ከመጭበርበር እና ከስርቆት እንዲጠብቅ አቶ ማሞ አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]