March 31, 2025

በተጨማሪ አራት የጣቢያው ሰራተኞች ላይ የቀረበው የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ለነገ ተቀጥሯል
በቤርሳቤህ ገብረ
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ፖሊስ “በሽብር ወንጀል ጉዳይ ጠርጥሬያቸዋለሁ” ባላቸው አራት የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰራተኞች ላይ የ14 ቀናት የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ። ባለፈው አርብ ፍርድ ቤት ከቀረቡ የጣቢያው ሰራተኞች መካከል፤ የካሜራ ባለሙያ የሆነው አቶ ቶማስ ደመቀ ከእስር ተለቅቋል ተብሏል።
የአቶ ቶማስን ከእስር መለቀቅ ከፖሊስ የምርመራ ምዝገባ መረዳቱን የገለጸው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ነው። ችሎቱ የኢቤኤስ ሰራተኞች የተካተቱበት የስምንት ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ መመልከት የጀመረው ባለፈው አርብ መጋቢት 19፤ 2017 ነበር።
የፌደራል ፖሊስ ለችሎቱ ባቀረበው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ማመልከቻ ላይ በተጠርጣሪዎቹ ላይ እያካሄደ ያለውን ምርመራ “በሰው እና በሰነድ ማስረጃ በስፋት ለማጣራት” የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ ነበር። ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ በዛሬው ዕለት ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ከመስጠቱ አስቀድሞ፤ የፖሊስ ጅምር የምርመራ መዝገብ እንዲቀርብለት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ችሎቱ ዛሬ ሰኞ መጋቢት 22 ከሰዓት በነበረው ውሎው፤ ተጠርጣሪዎቹን በሽብር ወንጀል ለመጠርጠር አመላካች የሆኑ ነገሮች ከፖሊስ ምርመራ መዝገብ ተመልክቼያለሁ ብሏል። የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች፤ ደንበኞቻቸው ቢጠረጠሩ እንኳን “የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣ አዋጅ ስር ባሉ ድንጋጌዎች” እንደሆነ ያቀረቡት መከራከሪያ “የተፈጸመ ጥፋት መኖሩን” የሚያሳይ እንደሆነ ችሎቱ በተጨማሪነት ጠቅሷል።
ሆኖም ተጠርጣሪዎቹ “ፈጽመዋቸዋል” የተባሉ የወንጀል ድርጊቶች ሊያስጠረጥሩ የሚችለው በዚህ አዋጅ መሰረት እንደሆነ የቀረበውን መከራከሪያ ፍርድ ቤቱ “የህግ አግባብ የሌለው” መሆኑን በመጥቀስ አለመቀበሉን ገልጿል። ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ማመልከቻ ለጠቀሳቸው ድርጊቶች “ተጠያቂ መሆን ያለበት የፕሮግራም ኃላፊ ነው” በሚል ጠበቆች ያቀረቡትን መከራከሪያም ችሎቱ በተመሳሳይ ውድቅ አድርጓል።
ችሎቱ ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸው በኩል ባቀረቡት “የዋስትና መብት ይከበርልን” ጥያቄ ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን ያልተቀበለው፤ ተጠርጣሪዎች በዋስ ቢለቀቁ የማስረጃ ማሰባሰብ የምርመራ ሂደቱን በማደናቀፍ ውጤት እንዳይገኝ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረሱ መሆኑን አስረድቷል።

የሽብር ወንጀል ምርመራ “ውስብስብነት” “አጠያያቂ አለመሆኑን” የገለጸው ችሎቱ፤ በዚህ ምክንያት ተጠርጣሪዎቹ “በእስር ቆይተው ምርመራው ሊከናወን ይገባል” ሲል በይኗል። ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ የፈቀደው ተጠርጣሪዎቹ ከተያዙበት ቀን ጀምሮ እንደሆነ ገልጾ፤ ለሚያዝያ 3፤ 2017 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዛሬውን ውሎውን ከማጠናቀቁ በፊት፤ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ በፕሮግራም ዳይሬክተርነት የሚሰራው ጋዜጠኛ ታሪኩ ኃይሌ ባለፈው አርብ በነበረው ችሎት ላቀረበው አቤቱታ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ጋዜጠኛ ታሪኩ በአርቡ የችሎት ውሎ፤ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የእስረኞች ማቆያ “በጨለማ ክፍል” ታስሮ እንደሚገኝ እና “እዚያው እንደሚጸዳዳ” አቤቱታውን ለፍርድ ቤቱ አሰምቶ ነበር።
ይህንን የጋዜጠኛውን አቤቱታ እንዲያጣራ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠው ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ነው። ኮሚሽኑ “የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸም አለመፈጸሙን” እንዲሁም “ማነው የፈጸመው?” የሚለውን በስፍራው በመገኘት ጉብኝት አድርጎ ካጣራ በኋላ እና ሪፖርቱን በመጪው ቀጠሮ እንዲያቀርብ ችሎቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ከሰዓት በኋላ በተካሄደው የችሎት ውሎ፤ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ በተሰራጨ ዝግጅት ላይ “የሀሰት ታሪኳ” ቀርቧል የተባለው ብርቱካን ተመስገንን ጨምሮ ሰባት ተጠርጣሪዎች በአካል ተገኝተው ሂደቱን ተከታትለዋል። ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ ጥዑመልሳን እና የጣቢያው የፕሮግራም ዳይሬክተር ታሪኩ ኃይሌ፣ የስቱዲዩ ዳይሬክተሩ አቶ ንጥር ደረጀ እና ረዳት የፕሮግራም አዘጋጇ ህሊና ታረቀኝ ይገኙበታል።
ባለፈው አርብ በነበረው ችሎት፤ የብርቱካን ተመስገን “ሀሰተኛ ታሪክ” ተላልፎበታል የተባለው ዶክመንተሪ ቀረጻ ሲከናወን “በእረፍት ላይ እንደነበር” የተገለጸው የኢቢኤስ የካሜራ ባለሙያ ቶማስ በከሰዓቱ የፍርድ ቤት ውሎ አልቀረበም። ዛሬ ጠዋት በተመሳሳይ ችሎት በተካሄደ ሌላ የፍርድ ቤት ውሎ፤ ተጨማሪ አራት የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰራተኞች የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።
የፌደራል ፖሊስ በተመሳሳይ “የሽብር ወንጀል እንደጠረጠራቸው” በመግለጽ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀባቸው፤ የኢቤኢስ ቴሌቪዥን ጣቢያ የፕሮግራም ስራ አስኪያጇ ቅድስት ጌታቸው፣ የስቱዲዮ ስራ አስኪያጁ አቶ ግርማ ተፈራ፣ የኤዲቲንግ ሱፐርቫይዘሩ አቶ ሄኖክ አባተ እና ኤዲተሩ አቶ ሀብታሙ አለማየሁ ናቸው።

ጠዋት ፍርድ ቤት ከቀረቡት ከአራቱ የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰራተኞች ጋር ሌሎችም ሶስት ተጠርጣሪዎች በተመሳሳይ መዝገብ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የወንጀል ችሎት፤ ፖሊስ ያቀረበውን የጊዜ ቀጠሮ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለነገ ማክሰኞ መጋቢት 23፤ 2017 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)