March 31, 2025

በተስፋለም ወልደየስ
የፌደራል መንግስት በክልሎች የሚያቋቁመውን ጊዜያዊ አስተዳደር የስራ ዘመን፤ ለሁለት ጊዜ የማራዘም ስልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሚሰጥ የአዋጅ ማሻሻያ በነገው ዕለት ለፓርላማ ሊቀርብ ነው። የአዋጅ ማሻሻያው፤ የአፈ ጉባኤው ውሳኔ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ተቀባይነት ካላገኘ፤ ጊዜያዊ አስተዳደር በተቋቋመበት ክልል “በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ” “ምርጫ እንዲደረግ” ያስገድዳል።
ይህ የህግ ረቂቅ፤ የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበትን ስርአት ለመደንገግ በ1995 ዓ.ም የወጣውን አዋጅ የሚያሻሽል ነው። የአዋጅ ማሻሻያው በነገው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ የሚቀርበው፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን የስልጣን ዘመን ለማራዘም “የህግ ማሻሻያ” እንደሚያስፈልግ ከተገለጸ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን “ዕድሜ” በአንድ ዓመት ለማራዘም መታሰቡን እና ለዚህም የህግ ማሻሻያ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያስታወቁት፤ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት መጋቢት 11፤ 2017 በተወካዮች ምክር ቤት በተገኙበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ለትግራይ ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክትም ይህንኑ ጉዳይ ደግመው አንስተውታል። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በአዋጅ የተፈቀደለት የስራ ዘመን “ሁለት ዓመት ብቻ” እንደሆነ በዚሁ መልዕክታቸው ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ተጨባጭ ምክንያት ካለ” ግን የአስተዳደሩ ዕድሜ ሊራዘም እንደሚችል አመልክተዋል።
አብይ ይህን ጥቆማ የሰጡት፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሲቋቋም መሰረት ያደረገውን በ1995 ዓ.ም የወጣ አዋጅ በማጣቀሻነት በመጠቀም ነው። የፌደራል መንግስት “በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ስርዓት” የሚደነግገው ይህ አዋጅ፤ በአንድ ክልል ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት ከተፈጸመ፤ የፌደራል መንግስት ለራሱ ተጠሪ የሆነ “ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም” ሊያደርግ እንደሚችል ያትታል።
በዚህ መልክ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር በአንድ ክልል የሚቆየው “ከሁለት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ” እንደሆነም አዋጁ ይገልጻል። በነገው ዕለት ለፓርላማ የሚቀርበው የአዋጅ ማሻሻያ ይህንኑ የጊዜ ገደብ ሳይነካ እንዲቀጥል ቢያደርግም፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የመቆያ ጊዜ “ከ6 ወር ላልበለጠ ጊዜ ማራዘም” እንደሚቻል በተቀመጠው ድንጋጌ ላይ ግን ማሻሻያዎች አክሏል።

በነባሩ አዋጅ ላይ የጊዜያዊ አስተዳደሩን የመቆያ ጊዜ “አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ” የማራዘም ስልጣን የተሰጠው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ነበር። በዚህ ድንጋጌ ትግበራ ሂደት ላይ “ባለፉት ዓመታት የተስተዋሉ ሁለት ችግሮች” እንዳሉ የአዋጅ ማሻሻያውን ለማብራራት የቀረበ ሰነድ ያስረዳል።
የመጀመሪያው ችግር “የጊዜያዊ አስተዳደሩን ቆይታ ለማራዘም ውሳኔ የሚሰጠው የፌደሬሽን ምክር ቤት፤ በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ የሚሰበሰብ” ከመሆኑ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ማብራሪያው ይገልጻል። የምክር ቤቱ አባላት “በየክልላቸው ከፍተኛና ተደራራቢ የመንግስት ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ፤ የጊዜያዊ አስተዳደር ቆይታን ማራዘም ሲያስፈልግ በአጭር ጊዜ ስብሰባ በመጥራት ውይይት አድርጎ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስቸግር” እንደሆነ ሰነዱ ያታትል።
በማብራሪያ ሰነዱ የተቀመጠው ሁለተኛ ችግር በነባሩ አዋጅ ለጊዜያዊ አስተዳደር የተቀመጠው የጊዜ ገደብ “ሁለት ዓመት ከግማሽ” መሆኑ ነው። ይህ መነሻ “ከነባራዊው ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ሆኖ ተገኝቷል” የሚለው ሰነዱ፤ “በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የማይፈቱ እክሎችም ተስተውለዋል” ሲል ያክላል። በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት ያለው “ነባራዊ ሁኔታ” ለዚህ “በአብነት መጥቀስ ይቻላል” ሲልም ያክላል።

አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ ላይ ለተስተዋሉ “ውስንነቶች” “መፍትሔ ለመስጠት” እና “የህጉን ክፍተት ለማሟላት የሚያስችል ግልጽ አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ” ማሻሻያ መደረጉን የማብራሪያ ሰነዱ ያስረዳል። በአዋጅ ማሻሻያው፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩን የቆይታ ጊዜ ከአንድም ሁለት ጊዜ የማራዘም ስልጣን የተሰጠው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ነው።
“በክልሉ ውስጥ የፌደራል መንግስቱን ጣልቃ መግባት አስፈላጊ ካደረገው ሁኔታ ውስብስብነት አኳያ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፤ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ቆይታ እስከ አንድ ዓመት ድረስ እንዲራዘም ሊወስን ይችላል” ሲል የአዋጅ ማሻሻያው ይደነግጋል። አዋጁን ለማብራራት የቀረበው ሰነድ “ይህ የሆነበት ምክንያት አስቸኳይ ሁኔታ ሲፈጠር በአፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት እንዲያስችል ነው” ሲል መነሻውን ያስረዳል።
“በፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የጊዜያዊ አስተዳደር ቆይታ እንዲራዘም የተላለፈ ውሳኔ ለሁለተኛ ጊዜ ማራዘም ቢያስፈልግ፤ አፈ ጉባዔው ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ እንዲራዘም ሊወስን” እንደሚችልም በአዋጅ ማሻሻያ ላይ ተቀምጧል። ሆኖም በአፈ ጉባኤው የሚሰጡ የማራዘሚያ ውሳኔዎች፤ በፌደሬሽን ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርበው መጽደቅ እንዳለባቸው የአዋጅ ማሻሻያው ደንግጓል።
“በፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የጊዜያዊ አስተዳደር ቆይታ እንዲራዘም የተላለፈ ውሳኔ ለሁለተኛ ጊዜ ማራዘም ቢያስፈልግ፤ አፈ ጉባዔው ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ እንዲራዘም ሊወስን ይችላል ”– የፌደራል መንግስት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ስርዓት ለመደንገግ የወጣ የአዋጅ ማሻሻያ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የአፈ ጉባኤውን ውሳኔ ውድቅ ቢያደርጉ፤ ቀጣዩ ሂደት ምን ሊሆን እንደሚችልም በአዋጅ ማሻሻያው ላይ በግልጽ ሰፍሯል። “የአፈ ጉባኤው ውሳኔ በምክር ቤቱ ቀጣይ መደበኛ ጉባኤ ተቀባይነት ካላገኘ፤ ውሳኔው ውድቅ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ በሚቆጠር አራት ወራት ጊዜ ውስጥ ምርጫ ተደርጎ መደበኛ የክልል መንግስት አስተዳደር መመስረት ይኖርበታል” ይላል የአዋጅ ማሻሻያው።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በሚያስተላልፈው የጊዜ ማራዘሚያ ውሳኔ ላይ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ “ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ሊመላከቱ” እንደሚችሉም በአዲሱ የአዋጅ ማሻሻያ ላይ ተካትቷል። በአፈ ጉባኤው ውሳኔ ሊመላከቱ የሚችሉ እነዚህ የትኩረት አቅጣጫዎች፤ “ጊዜያዊ አስተዳደር ያስፈለገበትን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ እና ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ለማጽናት አስፈላጊ የሆኑ” ጉዳዮች ሊሆኑ እንደሚችሉ የአዋጅ ማብራሪያው አመልክቷል።
ይህን የአዋጅ ማሻሻያ፤ ነገ ማክሰኞ መጋቢት 23፤ 2017 መደበኛ ስብሰባውን የሚያካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርምሮ ያጸድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል። ፓርላማው በልዩ ሁኔታ ለሚያያቸው ህጎች እንደሚያደርገው ያለ “ሁለተኛ ንባብ” ያጸድቀዋል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ የአዋጅ ማሻሻያ፤ በተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን በረቂቅ ሰነዱ ላይ ተቀምጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)