
ከ 8 ሰአት በፊት
“በዚህ የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ሰርቲፊኬቴ ስራ ማግኘት እፈልጋለሁ” ትላለች በሴራሊዮኗ መዲና ፍሪታውን ማረሚያ ቤት ታራሚ የሆነች ሴት።
በማረሚያ ቤቱ ባለስልጣናት ስሟ አይገለጽም የተባለችው ይህች ታራሚ ስትፈታ በእግር ኳስ አሰልጣኝነት መሰማራት የሚል ህልምን ሰንቃለች።
እሷን ጨምሮ ሌሎች 25 ታራሚዎች እንዲሁም አምስት ፖሊሶች እግር ኳስ ለማሰልጠን የሚያስችላቸውን ስልጠና አጠናቀዋል።
ስልጠናውን ያዘጋጀው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ነው።
በታሪኩም ለመጀመሪያ ጊዜ ለሴት ታራሚዎች በሚል ነው ይህ ስልጠና የተዘጋጀው።
“ስልጠናው በቃላት መገለጽ ከሚችለው በላይ በጣም ገራሚ ነው። ሰርቲፊኬቴን በማግኘቴ ኩራት ይሰማኛል” ብላለች በማረሚያ ቤት አራት ዓመታት ያህል የቆየችው ይህች ታራሚ።
ስልጠናው ስምንት ቀናትን ይፈጃል።
የሚሰጣቸውም ፈቃድ ‘ላይሰንስ ዲ’ የተሰኘ ሰርፊቲኬት ነው።
ታራሚዎቹ የካፍን የአሰልጣኝነት እውቅናን ያገኛሉ።
ከማረሚያ ቤቶች ከወጡ በኋላ እግር ኳስን ወደ ማህበረሰቦቻቸው ወርደው እንዲያሰለጥኑ ያስችላቸዋል።
እስካሁን ድረስ ስልጠናዎቹ በምዕራብ አፍሪካውያኖቹ በሴራሊዮን፣ በጋና እና ላይቤሪያ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ተካሂደዋል።
በሌሎች የአህጉሪቱ ክፍሎች ለማዳረስ ዕቅድ ተይዟል።
ሴት ታራሚዎችን በእግር ኳስ አሰልጣኝነት የማብቃት ፕሮግራም የምዕራብ አፍሪካ ታላላቅ ሴት እግር ኳስ ኮከቦችን ስቧል።
ለምሳሌ ያህል የሴራሊዮን እግር ኳስ ማህበር ፕሬዚዳንት የነበረችው ኢሻ ጆሃንሰን እና የጋና ብሄራዊ ቡድን የቀድሞ ተጫዋች የሆነችው ሜርሲ ታንጎ ተጠቃሾች ናቸው።
የፊፋ እና የካፍ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆነችው ኢሻ ጆሃንሰን በፍሪታውን የሚገኘውን ማረሚያ ቤት ከጎበኘች በኋላ በዚህ ፕሮጀክት መሳተፍ እንደጀመረች ተናግራለች።

- የእንግሊዝ ትልቁ ክለብ የትኛው ነው?28 መጋቢት 2025
- “ኬንያ ለመጪው የዓለም ዋንጫ በማለፍ ብዙዎችን ማስደነቅ ትችላለች” አዲሱ አሠልጣኝ ቤኒ ማካርቲ7 መጋቢት 2025
- ሶማሊያ ለአሜሪካ ቁልፍ ወደብ ለመስጠት ያቀረበችውን ሃሳብ ሶማሊላንድ ውድቅ አደረገች30 መጋቢት 2025
“እዚህ [በማረሚያ ቤቱ] በጣም ትንንሽ ታዳጊዎችን አየሁ። በማረሚያ ቤቱ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ታራሚዎች የገቡት በድህነት ወይም ከጥቃቅን ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ነው። አምስት፣ ስድስት ወይም ስምንት ዓመታትን ምንም ሳያደርጉ ይቀመጣሉ” ትላለች።.
አክላም ” ማረሚያ ቤቱ መገኘት አልነበራቸውም። ለውጥ ማምጣት ነበረብኝ። አንድ ነገር ለማድረግ ወሰንኩ፤ እናም እግር ኳስ በእጄ ያለኝ ትልቅ መሳሪያ ስለሆነም ተጠቀምኩበት” ስትል ገልጻለች።
በሴራሊዮን የሚገኝ አድቮክ ኤይድ የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መረጃ መሰረት የፍሪታውን የሴቶች ማረሚያ ማዕከል በአሁኑ ወቅት ወደ 90 የሚጠጉ ሴት ታራሚዎች እና ልጆቻቸው ይገኛሉ።
በማረሚያ ቤቱ ጥቂት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሲኖሩ የመጀመሪያው ስልጠና የተካሄደው ፍሪታውን በሚገኘው የሴራሊዮን እግር ኳስ ማህበር አካዳሚ ውስጥ አስትሮተርፍ በተሰኘው ሜዳ ነው።
ማህበሩ ለታራሚዎቹ የማሊያዎች እና የሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል።
ሆኖም ኢሻ በማረሚያ ቤቱ እግር ኳስ ሜዳ በአጭር ጊዜ የመገንባት እቅድ እንደተያዘ ገልጻለች።
“በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ የማረሚያ ማዕከሉ ሜዳ እንደሚኖረው ስናገር በኩራት ነው። የመጀመሪያው ይሆናል” ስትል ኢሻ ገልጻለች።
በእግር ኳስ አሰልጣኝነት በቀጥታ መሳተፍ ለማይፈልጉ ታራሚዎች ካፍ ሌሎች ፕሮግራሞችን ይዟል። አንዳንዶቹም የእግር ኳስ ማሊያዎችን እየሰፉ በተጫዋችነት እየሰለጠኑ ይገኛሉ።
“እነዚህ ታዳጊዎች ወደ ማህበረሰቡ ከተመለሱ በኋላ ማረሚያ ቤት ተመልሰው የሚገቡበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ነው የምፈልገው” ብላለች ኢሻ።
ኢሻ እንደምትለው “ከማረሚያ ቤት ሲወጡ ክህሎት አዳብረው ነው። ወደ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሄደው ስራ መፈለግ እንዲሁም በትምህርት ቤቶች ማሰልጠን ይችላሉ።”
በሌላኛዋ የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋናም እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ትልቁ የሴት ማረሚያ ቤት የሆነው ናሳዋም ታራሚዎች ፊታቸውን ወደ እግር ኳሱ አዙረዋል።
“ማረሚያ ቤት መሆን በጣም ፈታኝ ነው። በሁሉም ነገር ላይ ቁጥጥር ይደረግብናል። ራስ የሚያሳምም ነው” ስትል አንዲት ታራሚ ገልጻለች።

“እግር ኳስ ማሰልጠን የምመኘው ነገር ነው። እናም ስለ ስልጠናው ስሰማ የዚህ አካል መሆን መቻሌ በጣም አስደሰተኝ። ብዙ ክህሎቶችን አዳብረናል” ብላለች ይህችው ታራሚ።
በጋና ከሚገኙ አሰልጣኞች መካከል አንዷ የሆነችው ሜርሲ ታጎዬ ስልጠናው በታራሚዎች ዘንድ በጣም ተወዳጅ እንደሆነ እንዲሁም ታራሚዎችን ወደ ህብረተሰቡ መልሶ ለመቀላቀል በሚደረገውም ጥረት መሰረታዊ ነው ስትል ታስረዳለች።
“በአሰልጣኝነት ፈቃዳቸው አንድ ነገር ማከናወን ይችላሉ። ከማረሚያ ቤቶች ከወጡ በኋላ ወደ ማህበረሰባቸው ሄደው ማሰልጠን ይችላሉ” ብላለች ሜርሲ።
አሰልጣኟ እንደምትለው “ወደ እስር ቤት የሚገቡት እንዲሻሻሉ ነው። ይህ ስልጠናም በቀጣዩ ህይወታቸውን እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ነው።”
ወደ ፍሪታውን ስንመለስ ኢሻ ከካፍ እና ከፊፋ ጋር በመጣመር የሴት ታራሚዎች የእግር ኳስ አሰልጣኝነት መርሃ ግብር በሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንዴት ይተገበራል የሚለውን እያየች ነው።
በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በእስያ እና በደቡብ አሜሪካ ቢተገበር ትላለች።
ኢሻ እግር ኳስ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን የነዚህን ታዳጊ ሴቶች ህይወት የሚቀይር ኃይል አለው ብላ ታምናለች።
“እግር ኳስን ለአዎንታዊ ማህበራዊ ለውጥ መጠቀም እንችላለን። እግር ኳስ በሜዳ ላይ ካለው ከ90 ደቂቃ ጨዋታ በላይ ነው። ይህም አንዱ ተምሳሌት ነው” ብላለች።