ፑቲን

ከ 6 ሰአት በፊት

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ተናድጃለሁ፤ እጅግም ተበሳጭቻለሁ” ቢሉም ሩሲያ ግን “ከአሜሪካ ጋር መሥራት ቀጥለናል” ብላለች።

ትራምፕ ቁጣቸውን ከገለጹ በኋላ ሩሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠችው ምላሽ በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል ያለውን ውጥረት አቅልላ አቅርባለች።

የአገሪቱ ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “ከአሜሪካ ጋር ግንኙነታችንን ለማስቀጠል እየሠራን ነው” ብለዋል።

በሁለቱ መሪዎች መካከል በዚህ ሳምንት የታቀደ የስልክ ጥሪ ባይኖርም “አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ” ግን ፑቲን ለመደዋወል ዝግጁ መሆናቸውን አክለዋል።

ትራምፕ ያሳለፍነው ቅዳሜ ለኤንቢሲ ኒውስ ፑቲን እንዳበሳጯቸው ከተናገሩ በኋላ የመሪዎቹን ግንኙነት ለማለሳለስ እየተሞከረ ነው።

ፑቲን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪን ተዓማኒነት ለማጣጣል ሞክረዋል በሚል ነበር ትራምፕ የተበሳጩት።

ፑቲን በተኩስ አቁም ካልተስማሙ የሩሲያን ነዳጅ በሚገዙ አገራት ላይ 50% ታሪፍ ለመጣል ዝተዋል።

ትራምፕ በፑቲን ጉዳይ ላይ የከረረ አስተያየት ሲሰጡ አይደመጥም ነበር።

የአሜሪካና የሩሲያ ባለሥልጣናት ለሳምንታት የዩክሬንን ጦርነት ለመግታት ሲወያዩ፣ ትራምፕ ዜሌንስኪን እንጂ ፑቲንን አልወቀሱም ነበር።

ፑቲን በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፍ ጊዜያዊ መንግሥት ዘለንስኪን እንዲተካቸው ሐሳብ ማቅረባቸውን ተከትሎ ትራምፕ ደስተኛ አይደሉም።

“በጣም ነው የተበሳጨሁት። የተናደድኩ። ፑቲን የዜሌንስኪን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱ መሄድ የምንፈልግበት አቅጣጫ አይደለም። አዲስ አስተዳደር ከመጣ ለረዥም ጊዜ ስምምነት ላይ አንደርስም ማለት ነው” ሲሉ ትራምፕ ለኤንቢሲ ኒውስ ተናግረዋል።

የሩሲያ ቃል አቀባይ ግን የትራምፕ ንግግር “የተወሰነ ማሻሻያ ተደርጎበት” እንደቀረበ ገልጸዋል።

የክሬምሊን ደጋፊው ጋዜጣ ሞስኮቫስኪ ባልተለመደ ሁኔታ ትራምፕን ተችቷል። ትራምፕ ዩክሬን የሩሲያን መሠረተ ልማት እንዳታጠቃ ለማድረግ የገቡትን ቃል አላከበሩም ሲልም ወርፏል።

“ከትራምፕ ጋር የሚደረግ ስምምነት ሁሉ ዋጋ ያለው ለተወሰነ ጊዜ ነው። ሞስኮ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጋር መስማማት ትፈልጋለች” ብሏል ጋዜጣው።