ወደ ኤልሳልቫዶር የተጓጓዙ እስረኞች

ከ 6 ሰአት በፊት

የትራምፕ አስተዳደር የወንበዴ ቡድን አባላት ናቸው ያላቸውን ተጨማሪ 17 ሰዎች ወደ ኤል ሳልቫዶር መላኩን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካ መንግሥት እስረኞችን መካከለኛው አሜሪካ ወደሚገኝ ጥብቅ እስር ቤቶች እንዳያጓጉዝ በፍርድ ቤት ክርክር ተጀምሮ ነበር።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው በአሁኑ ወደ ኤል ሳልቫዶር ከተላኩት መካከል የትሬን ዲ አራግዋ እና ኤምኤስ-13 የወንጀል ቡድኖች አባላት መካተታቸውን ተናግረዋል።

የኤል ሳልቫዶር መንግሥት ባለስልጣናት ከአሜሪካ ወደ አገራቸው የተሸኙት የቬንዙዌላ እና የኤል ሳልቫዶር ዜጎች መሆናቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአገሪቱ የፌደራል ፍርድ ቤት ቀደም ሲል በጦርነት ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የዋለውን እና እአአ በ1798 በወጣው ሕግ መሰረት ግለሰቦችን ከአገር ማስወጣት እንዲቆም ትዕዛዝ ሰጥቶነበር።

ሆኖም የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን በመንግሥት ውስጥ ያሉ ምንጮችን ጠቅሰው እንደዘገቡት በቅርቡ ከአገር እንዲወጡ የተደረጉ ግለሰቦች በአገሪቱ የኢሚግሬሽን ሕግ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

ሩቢዮ በሰጡት መግለጫ ከአገር እንዲወጡ የተደረጉት “ገዳዮችን እና ደፋሪዎችን” ያካተተ ነው ቢሉም፣ የግለሰቦችን ስም ወይንም ስለተጠረጠሩበት ወንጀሎች ዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

የኤል ሳልቫዶር ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬሌ በኤክስ ገጻቸው ላይ በለጠፉት የተቀነባበረ ቪዲዮ ላይ የታሰሩ ሰዎች ከአውሮፕላን ሲወርዱ እና ጸጉራቸውን እየተላጩ ወደ ወህኒ ቤት ቤት ሲሄዱ ያሳያል።

“ሁሉም ግለሰቦች ነፍሰ ገዳዮች መሆናቸው የተረጋገጠ እና ስድስት ሕጻናትን ጨምሮ የደፈሩ ከፍተኛ ወንጀለኞች ናቸው” ሲሉም ጽፈዋል።

“ይህ ተግባር ሽብርተኝነትንና የተደራጁ ወንጀሎችን በመዋጋት ረገድ ሌላ እርምጃ ነው” ሲሉ አክለዋል።

ፕሬዚደንት ትራምፕ መልዕክቱን በድጋሚ ያጋሩት ሲሆን፣ ከአገር እንዲወጡ የተደረጉት ሰዎች ወደ አሜሪካ እንዲገቡ በመፍቀዱ የቀድሞ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደርን ወቅሰዋል።

ዶናልድ ትራምፕ የኤል ሳልቫዶር አቻቸውን “እንዲህ ያለ አስደናቂ የመኖሪያ ቦታ ስለሰጣችኋቸው” በሚል ምስጋና ቸረዋቸዋል።

ኤል ሳልቫዶር ከአሜሪካ የሚባረሩ ሰዎችን ለመቀበል 6 ሚሊየን ዶላር ተከፍሏታል።

ቀደም ሲል ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግበት እስር ቤት ከተላኩት መካከል የተወሰኑት ቤተሰቦች ከወንጀል ቡድን ጋር ግንኙነት የላቸውም ሲሉ አስተባብለዋል።

ትራምፕ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከ100 የሚበልጡ ቬንዙዌላውያንን ከአሜሪካ እንዲወጡ ለማድረግ ‘ኤሊየን ኢነሚስ አክት’ የተሰኘውን ሕግ መጠቀሟን በርካታ የመብት ተሟጋቾች በመቃወም ክስ መስርተዋል።

ክሱን ማርች 15 በዋሽንግተን ዲሲ የተመለከቱት የፌደራል ከፍተኛ ዳኛ፣ ጄምስ ቦአስበርግ፣ ጊዜያዊ የእገዳ ትዕዛዝ ጥለው ነበር።

ይኹን አንጂ አሁንም ግለሰቦቹን በኃይል ከአገር ማስወጣቱ ቀጥሏል።