
ከ 3 ሰአት በፊት
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 22ኛ መደበኛ ስብሰባ በክልሎች የሚቋቋም ጊዜያዊ አስተዳደር የሥልጣን ዘመን፤ለሁለት ጊዜ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ እንዲራዘም የሚያስችል የአዋጅ ማሻሻያን አጸደቀ።
የአዋጁ ማሻሻያ፤ ከዚህ ቀደም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣን የነበረውን የክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቆይታ ጊዜን የማራዘም ኃላፊነት፤ለምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የሰጠ ነው።
አዋጁ እስከ አሁን በሥራ ላይ የነበረውን አዋጅ ቁጥር 359/ 1995 የሚተካ ሲሆን፤ አዋጅ ቁጥር 1373/2017 ሆኖ በሁለት ድምጸ ተዐቅቦ መጽደቁ ተገልጿል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ 23/2017 ዓ. ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርቦ የጸደቀው ይህ አዋጅ፤ የሥልጣን ዘመኑ የተጠናቀቀው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሥልጣን ዘመን ለተጨማሪ ዓመት እንዲራዘም የሚያስችል ነው።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጊዜያዊ አስተዳደር የተመሰረተው በ2015 ዓ. ም. የወጣውን ማቋቋሚያ ደንብ መሠረት አድርጎ ነው።
ጊዜያዊ አስተዳደሩን ያቋቋመው ደንብ ደግሞ መሠረት ያደረገው ከ22 ዓመት ገደማ በፊት የጸደቀውን የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት የሚደነግግ አዋጅ ነው።
ይህ አዋጅ የፌደራል መንግሥት በሦስት ሁኔታዎች በክልሎች ውስጥ ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል ደንግጓል።
በቀዳሚነት የተጠቀሰው ምክንያት በክልሉ ውስጥ የሚፈጠር የጸጥታ መደፍረስ ሲሆን በዚህ ጊዜ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የክልሉ መንግሥት ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል።
በክልሉ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰት ከተፈጸም እና የክልሉ መንግሥት ድርጊቱን በቁጥጥሩ ሥር ማዋል ካልቻለም ፌደራል መንግሥት ጣልቃ ይገባል።
በአዋጁ ላይ የተጠቀሰው ሦስተኛ ሁኔታ፤ እንደ “በትጥቅ የተደገፈ የአመጽ እንቅስቃሴ” ያሉ ድርጊቶች በሚፈጸሙበት ወቅት የሚከሰት “የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አደጋ ላይ መውደቅ” ነው።
በእነዚህ ሁኔታዎች መከሰት ምክንያት ወደ በክልሎች ጣልቃ የሚገባው የፌደራል መንግሥት ሊያከናውን ከሚችላቸው ጉዳዮች መካከል “የክልሉን ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል በማገድ ለፌደራል መንግሥት ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር” ማቋቋም የሚለው ይገኝበታል።
በዚህ መልኩ የሚቋቋም ጊዜያዊ አስተዳደር የሚቆየው ከሁለት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ እንደሆነ አዋጁ ደንግጓል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጊዜያዊ አስተዳደሩን የቆይታ ጊዜ ማራዘም “አስፈላጊ ሆኖ” ካገኘው “ከስድስት ወር ላልበለጠ ጊዜ” ሊያራዝመው እንደሚችልም በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።
- የክልል ጊዜያዊ አስተዳደሮች የቆይታ ጊዜ እስከ ሁለት ዓመት እንዲራዘም የሚያስችል አዋጅ ዛሬ ሊጸድቅ ነውከ 7 ሰአት በፊት
- የትግራይ ክልል ቀውስ፡ ከፕሪቶሪያ ወዲህ መቼ ምን ተከሰተ?15 መጋቢት 2025
- ለትግራይ ከሌሎች ክልሎች “በተለየ ሁኔታ” ላለፉት 11 ቀናት ነዳጅ እንዳይጫን መደረጉ ተገለጸ26 መጋቢት 2025
ምክር ቤቱ ዛሬ ያጸደቀው አዋጅ፤ በክልሎች ውስጥ የሚመሠረት የጊዜያዊ አስተዳደር የቆይታ ጊዜ ሁለት ጊዜ እንዲራዘም ያስችላል።
“በክልሉ ውስጥ የፌደራል መንግሥቱን ጣልቃ መግባት አስፈላጊ ካደረገው ሁኔታ ውስብስብነት አኳያ አስፈላጊ ሆኖ” ከተገኘ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የቆይታ ጊዜ እስከ አንድ ዓመት እንዲራዘም ሊደረግ እንደሚችል በአዋጁ ላይ ተጠቅሷል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ የቆይታ ጊዜ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲራዘም የሚያስፈልግ ከሆነም በድጋሚ “ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ እንዲራዘም” ሊደረግ እንደሚችል አዲስ በጸደቀው አዋጅ ላይ ተቀምጧል።
በሥራ ላይ ባለው አዋጅ በክልሎች ውስጥ የሚመሠረት ጊዜያዊ አስተዳደርን የቆይታ ጊዜ የማራዘም ሥልጣን ፌዴሬሽንም ምክር ቤት እንደሆነ ደንግጓል።
አዲሱ ማሻሻያ ረቂቅ በበኩሉ ይህንን ሥልጣን ወደ ምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አዘዋውሯል።
አዋጁ የጊዜያዊ አስተዳደርን ቆይታ ጊዜ የማራዘም ሥልጣንን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቢሰጥም፤ ምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤውን በሚያካሂድበት ወቅት ውሳኔው ቀርቦ መጽደቅ እንዳለበት ይደነግጋል።
ምክር ቤት የሚቀርብለትን የቆይታ ጊዜ ማራዘም ውሳኔ ካልተቀበለው፤ “ውሳኔው ውድቅ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ በሚቆጠር አራት ወራት ጊዜ ውስጥ ምርጫ ተደርጎ መደበኛ የክልል መንግሥት አስተዳደር መመሥረት” እንደሚኖርበት በአዋጁ ላይ ተካትቷል።
ጊዜያዊ አስተዳደር በተመለከተ በአፈ ጉባኤው በሚተላለፍ ወይም በምክር ቤቱ በሚጸድቅ ውሳኔ ውስጥ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ሊመላከቱ” እንደሚችሉ አዋጁ ያስረዳል።
እነዚህ ጉዳዮች “ለፌደራል መንግሥት ጣልቃ መግባት ምክንያት የሆነውን ሁኔታ በዘላቂነት ለመቅረፍ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማጽናት አስፈላጊ የሆኑ” ተግባራት እንደሚሆኑ ተጠቅሷል።
ይህ አዋጅ የጸደቀው ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን የቆይታ ጊዜ ለአንድ ዓመት የማራዘም እቅድ እንዳለ ካስታወቁ ከቀናት በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው በትግርኛ ባሰፈሩት ጽሑፍ በ2015 ዓ. ም. የተቋቋመው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የሁለት ዓመት የሥልጣን ዘመን ማብቃቱን ገልጸው ነበር።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ በሁለት ዓመት ቆይታው ሊሠራቸው ይገባ የነበሩ “ቁልፍ ተግባራቶች በወቅቱ ማከናወን እንዳልቻለ” ገልጸዋል።
ከእነዚህ ቁልፍ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በክልሉ መደበኛ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ምርጫ ለማካሄድ “ሁኔታዎችን ማመቻቸት” እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
በክልሉ ያለውን “ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት” የጊዜያዊ አስተዳደሩ የቆይታ ጊዜ በአንድ ዓመት እንደሚራዘም ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ የሚከናወነውም የሕግ ማሻሻያ ተደርጎ እንደሆነ ገልጸው ነበር።
በዚሁ መልዕክታቸው በአቶ ጌታቸው ረዳ ሲመራ ለቆየው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፤ ፕሬዝዳንት ለመሾም የትግራይ ሕዝብ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ማቅረባቸውም ይታወሳል።