ሰኞ ዕለት የሟች ቤተሰቦች እና ዘመዶች የ15 ሰዎች በጅምላ ሲቀበር ተገኝተው ሀዘናቸውን ሲገልጹ

ከ 7 ሰአት በፊት

አሜሪካ በጋዛ “የሚንቀሳቀሱ ሁሉም አካላት” ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግን እንዲያከብሩ እንደምትጠብቅ ገለጸች።

ነገር ግን የእስራኤል ጦር የድንገተኛ ሕክምና ባለሙያዎችን፣ሲቪል የመከላከያ ሠራተኞች እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊን ጨምሮ 15 ሰዎችን ተኩሶ ስለገደለበት ክስተት የራሷን ግምገማ ስለማካሄዷ ያለችው ነገር የለም።

ስለ ግድያው የተጠየቁት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ታሚ ብሩስ “በጋዛ ውስጥ የሚፈጸመው እያንዳንዱ ነገር በሃማስ ምክንያት ነው” ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው መጋቢት14/ 2017 ዓ.ም አምስት አምቡላንሶች፣ አንድ የእሳት አደጋ መኪና እና አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተሽከርካሪ በተናጠል እያንዳንዳቸው የተመቱ ሲሆን የደንብ ልብሳቸውን የለበሱ የሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ 15 አስከሬኖች ተሰብስበው በጅምላ መቃብር ውስጥ ተቀብረዋል።

የእስራኤል ጦር ሠራዊቱ በበኩሉ ተሽከርካሪዎቹ ያለ የፊት መብራት እና የአደጋ ጊዜ ምልክት “አጠራጣሪ በሆነ ሁኔታ እየገሰገሱ” እየመጡ ስለነበር መተኮሱን የተናገረ ሲሆን፣ የሃማስ እና ሌሎች ታጣቂዎች ከተገደሉት መካከል እንደሚገኙበት ገልጿል።

ነገር ግን ተሰብስበው ስለተቀበሩ አስከሬኖች ምንም አይነት ማብራርያ ከመስጠት ተቆጥቧል።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ በሲቪሎች ላይ ዒላማ ማድረግን የሚከለክል ሲሆን ለሕክምና ሠራተኞች የተለየ ጥበቃ እንዲደረግ ይጠይቃል።

የእስራኤል ትልቁ የጦር መሳሪያ አቅራቢ የሆነችው አሜሪካ እንዲሁ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት የጦር መሳሪያዎቿ በውጪ ኃይሎች የሰብዓዊ ሕግን በመጣስ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የመከታተል ኃላፊነት ተጥሎባታል።

በጋዛ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ኤጀንሲ ኃላፊ ጆናታን ዊትታል እንዳሉት የጅምላ መቃብሩ በእስራኤል ወታደሮች ተተኩሶ ከተመቱት አምቡላንሶች የአንዱ የአደጋ ጊዜ መብራት ምልክት ተደርጎበታል።

በኤክስ ገጻቸው ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት “የጤና ባለሙያዎች በጭራሽ ዒላማ መሆን የለባቸውም” ካሉ በኋላ “የተከሰተው ፍጹም አሰቃቂ ነገር ነው” ብለዋል።

እስራኤል ከሃማስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነትን በተመለከተ የምታደርገው ድርድር ከተቋረጠ በኋላ ከመጋቢት 18 ጀምሮ በጋዛ የአየር እና የምድር ዘመቻዋን አጠናክራ ቀጥላለች።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ከ1,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሃማስ አስተዳደር የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

እአአ ኦክቶበር 7 2023 የሃማስ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ በፈጸሙት ጥቃት ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ሲገደሉ 251 ታግተው ከተወሰዱ ቧኀላ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ሃማስ ላይ በምድር እና በአየር የተጠናከረ ዘመቻ ከፍቷል።

በጋዛ በተካሄደው ጦርነት ከ50,350 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።