የሚያንማር ርዕደ መሬት

ከ 7 ሰአት በፊት

በሚያንማር ርዕደ መሬት ከ2,000 በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን የአገሪቱ ወታደራዊ መንግሥትም የአንድ ሳምንት ብሔራዊ ሐዘን አውጇል።

በ7.7 ማግኒትዩድ የተለካው ርዕደ መሬት የተነሳበትን ሰዓት ለማስታወስ የኅሊና ፀሎትም ይደረጋል።

በርዕደ መሬቱ ሳቢያ የተጎዱት ሰዎች ከ4,000 በላይ መሆናቸው ተገልጿል።

በሚያንማር ጎረቤት ታይላንድ በርዕደ መሬቱ ንዝረት 20 ሰዎች ሞተዋል። በባንኮክ ሕንጻዎች በመሰነጣጠቃቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው ለመውጣት ተገደዋል።

በሁለቱም አገራት ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት ሙከራው ቢቀጥልም ሰዎችን በሕይወት የማግኘት ተስፋው እየተመናመነ መጥቷል።

ርዕደ መሬቱ ከተነሳ 72 ሰዓታት በማለፋቸው ሰዎችን በሕይወት የማግኘት ዕድሉ ጠቧል።

ለአምስት ቀናት የሚያንማር ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ ወታደራዊ መንግሥቱ ገልጿል።

ዜጎች በያሉበት ሆነው ለተጎጂዎች የኅሊና ፀሎት ያደርሳሉ።

ወታደራዊ መንግሥቱ ሩሲያ፣ ቻይና እና አሜሪካን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እርዳታ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተራድኦ ድርጅቶች እንዳሉት በቀጣይ የሚኖረው ሥራ ከባድ ይሆናል። የተለያዩ በሽታዎች ሊነሱ የሚችሉ ሲሆን፣ የመሠረተ ልማት ውድመት የእርዳታ ሥራውን የሚያስተጓጉልም ይሆናል።

ቢቢሲ በርሚዝ የተመለከታቸው አካባቢዎች የእርዳታ ሥራ በሁሉም ሥፍራ አለመጀመሩን ያሳያሉ።

በይፋ የሟቾች ቁጥር 2,000 ይደርሳል ቢባልም ወታደራዊው መንግሥት የተፈጥሮ አደጋ ሲደርስ የተጎዱ ሰዎችን ቁጥር በማሳነስ ይታወቃል።

የሚያንማር ርዕደ መሬት

በባንኮክ በርካታ የግንባታ ሠራተኞች በሥራ ላይ ሳሉ ርዕደ መሬቱ ስለተነሳ በፍርስራሽ ሥር ተቀብረዋል። ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት የሚደረገው ጥረትም እምብዛም ውጤታማ አልሆነም።

የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው ርዕደ መሬቱ በሚያንማር ያለውን አስከፊ ሁኔታ የበለጠ ያባባሰ ነው።

ሚያንማር ለአራት ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ናት።

ርዕደ መሬቱ ጉዳት እያደረሰ ባለበት ወቅትም ወታደራዊ መንግሥቱ ለዴሞክራሲ በሚታገሉ አማጺያን ላይ የአየር ጥቃት እያደረሰ ነው።

የሚያንማር ርዕደ መሬት

ርዕደ መሬቱ በተነሳበት ከተማ በቅርብ ርቀት በሚገኘው ሳጋይንግ የሚታየው ሰብዓዊ ቀውስ የከፋ ነው።

የእርዳታ ተቋማት ሰብዓዊ ቀውሱ እየተባባሰ ሊሄድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

በባንኮክ በተደረመሰ ሕንጻ ምክንያት ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ 70 ሰዎች እስካሁን ያሉበት አልታወቀም።

የሚያንማር ርዕደ መሬት ከታይላንድ በተጨማሪ በቻይናም ንዝረቱ ተሰምቷል።