
1 ሚያዚያ 2025
በሶማሊያ አንዲት የ8 ዓመት ሕፃን መጥፋቷ ከተነገረ ከስድስት ወራት በኋላ አግብቻታለሁ የሚሉ ግለሰብ ቤት መገኘቷ ቁጣ ቀስቅሷል።
በራስ ገዟ ፑንትላንድ የሚገኙት ቤተሰቦቿ ሕፃኗ ጠፍታለች ሲሉ ያሳወቁት ባለፈው መስከረም ነበር።
ከወራት በኋላ ሊታወቅ እንደቻለው አባቷ አግብቻታለሁ ለሚሉት ሼኽ ማሕሙድ ለተባሉ ግለሰብ እንድትዳር ፈቃድ ሰጥተዋል።
የፀጥታ አካላት ባለፈው ሳምንት አግብቻታለሁ ወደሚሉት ሰው ቤት ሰብረው ገብተው ሕፃኗን መታደግ ችለዋል። ፖሊስ ሰብሮ ሊገባ የቻለው ግለሰቡ አላስገባም ብለው ቤቱን በመቆለፋቸው ነው።
ይህ ዜና ከተሰማ በኋላ በማኅበራዊ ሚድያ ከፍተኛ ቁጣ የተቀሰቀሰ ሲሆን በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞጋዲሹ ተቃውሞ ሰልፍ ተደርጓል።
በርካቶች የሕፃናት ጥበቃ ሕግ ሊወጣ ይገባል ይላሉ። በሶማሊያ በአሁኑ ወቅት ትዳር ለማድረግ ዝቅተኛ የዕድሜ ገደብ የለም።
“ሁኔታው የሚያሳዝን ሆኖ ሳለ ተጠልፋ ተወስዳ ቤተሰቦቿ ለወራት የት እንዳለች አለማወቃቸው በጣም የሚያስደነግጥ ነው” ሲሉ ሶማሊ ዉሜን ቪዥን ኦርጋናይዜሽን የተባለው የመብት ተሟጋች ድርጅት ሊቀ-መንበር ፋዱሞ አሕመድ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
“የሚመለከታቸው ተቋማት ትክክለኛውን ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳሉ የሚል እምነት አለን።”
የ8 ዓመቷ ሕፃን አጎት እንደሚሉት ባለፈው መስከረም ነው በሴት ዘመዷ ቦሳሶ ከሚገኘው ቤቷ የተወሰደችው። ይህች ዘመድ ሕፃኗን ሌላ አጎቷን እንድታይ እንደወሰደቻት ትናገራለች።
- የክልል ጊዜያዊ አስተዳደሮች የቆይታ ጊዜ እስከ ሁለት ዓመት ማራዘም የሚያስችል አዋጅ ጸደቀ1 ሚያዚያ 2025
- አሜሪካ በጋዛ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም አካላት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግን ማክበር አለባቸው አለች1 ሚያዚያ 2025
- 2,000 ሰዎች ከሞቱበት የሚያንማር ርዕደ መሬት የተረፉ ሰዎችን የማግኘት ዕድል መጥበቡ ተገለጸ1 ሚያዚያ 2025
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ነገር ግን ከወራት በኋላ ሕፃኗ ቁራን ስትቀራ የሚያሳይ ቪድዮ በማኅበራዊ ሚድያ ተሰራጨ።
ቤተሰቦቿ ከዚህ በኋላ ልጃቸውን የማፈላለግ ሥራ ጀመሩ። ቤተሰቦቿ ቀድመው ለምን ይህን እንዳላደረጉ የሚታወቅ ነገር የለም።
ሼክ ማሕሙድ መጀመሪያ ሕፃኗን ቁራን እያስጠኑ እንደሆነ ተናገሩ። ነገር ግን ክስ ሲመሰርትባቸው አቋማቸውን ቀይረው በአባቷ ፈቃድ መሠረት ሕፃኗን እንዳገቧት አሳወቁ።
እንዴት የስምንት ዓመት ሕፃን ያገባሉ ተብለው በቢቢሲ ሲጠየቁ በነብዩ ሞሐመድ አስተምህሮት እና በሻፊ ሕግ መሠረት ሕፃናትን ማግባት ይፈቃድል ሲሉ ሼኽ ማሕሙድ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሼኽ ማሕሙድ ትዳራቸውን እንደማይፈቱ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነው የፑንትላንድ ፖሊስ እና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ባለፈው ሳምንት ሕፃኗን ከግለሰቡ እጅ ያስወጧት።
ሕፃኗ አሁን ከቤተሰቦቿ ጋር እንደምትገኝ የፑንትላንድ ፖሊስ ኃይል ለቢቢሲ ተናግሯል።
የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት የሕፃኗን መጥፋት በተለመከተ ምርመራ ተከፍቷል።
በሶማሊያ ሕፃናት ዕድሜያቸው ሳይደርስ ትዳር እንዲመሰርቱ ይደረጋሉ።
በአውሮፓውያኑ 2020 በተባበሩት መንግሥታት ፖፑሌሽን ፈንድ እና በሶማሊያ መንግሥት የተሰራ ጥናት እንደሚያሳየው ዕድሜያቸው ከ20-24 የሚሆኑ 35 በመቶ ሴቶች ትዳር የመሰረቱት 18 ዓመት ሳይሞላቸው ነው። በ2017 ይህ ቁጥር 45 በመቶ ነበር።
ድኅነት፣ የፀጥታ ሁኔታ እና ባሕላዊ አመለካከቶች ሴቶች ያለዕድሜያቸው እንዲያገቡ ምክንያት ተደርገው ይወሰዳሉ።
ይህን ሁኔታ ለመግታት በሚል የሶማሊያ የሴቶች እና ሰብዓዊ መብት ሚኒስቴር በ2023 የሕፃናት መብት ረቂቃ አዋጅ ለፓርላማው አቅርቦ ነበር።
ነገር ግን ይህ ረቂቅ አዋጅ ተቀባይነት ሳይገኝ ቀርቷል። ሕጉ ተሻሽሎ ድጋሚ ለፓርላማ እንደሚቀርብ ቢነገርም መች የሚለው ምላሽ አላገኘም።