የጋዛ ህጻናት

ከ 8 ሰአት በፊት

እስራኤል እንደ አዲስ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በጋዛ በጀመረችው ጥቃት 322 ህጻናት መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ።

በተጨማሪም በዚሁ ወቅት ቢያንስ 609 ህጻናት መቁሰላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ገልጿል።

“የጋዛ የተኩስ አቁም ለህጻናቱ የወደፊት ህይወታቸውን የሚያስቀጥል እንዲሁም የማገገምን ተስፋን የከፈተ ነበር” ሲሉ የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል ተናግረዋል።

አክለውም “ነገር ግን ህጻናቱ እንደገና አዙሪቱ ወደማያልቅ አስከፊ ጥቃቶች እንዲገቡ አድርጓቸዋል” ብለዋል።

የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያው ምዕራፍ ከተጠናቀቀ በኋላ እስራኤል ከሁለት ሳምንት በፊት እንደ አዲስ ጥቃቷን አጠናክራ ቀጥላለች።

እስራኤል የመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነትን መራዘምን ሐማስ እንዲቀበል ትፈልጋለች።

ሐማስ በበኩሉ ሁሉም ታጋቾች እንዲለቀቁ እንዲሁም የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ እና ዘላቂ መረጋጋትን ማምጣት ያለመው ሁለተኛው ምዕራፍ ተግባራዊ ይሁን እያለ ነው።

ሆኖም እስራኤል እና አሜሪካ ስምምነቱን በመቀየር አንደኛው ምዕራፍ እንዲራዘም እና ታጋቾች እንዲለቀቁ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።

ይህም የእስራኤል ጦር ከጋዛ መውጣትን እንዲሁም ዘላቂ የተኩስ አቁምን የሚያዘገየው ይሆናል።

ዩኒሴፍ በጋዛ “የማያቋርጥ እና ማንንም ባልለየ ሁኔታ የአየር ጥቃት” እየተፈጸመ እንደሆነ ገልጾ፤ ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ በየቀኑ 100 ህጻናት ተገድለዋል ወይም የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።

አብዛኞቹ የተገደሉት ህጻናት የተፈናቀሉ እና በጊዜያዊ ድንኳኖች ወይም ጉዳት በደረሰባቸው ቤቶች ተጠልለው የነበሩ ናቸው።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በበኩሉ በጋዛ በሚያደርገው “ወታደራዊ ዘመቻ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ እና በጦርነት ላይ ያሉ ህጎችን ጨምሮ አለም አቀፍ ግዴታዎችን አከብራለሁ” ብሏል።

የጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ባሉት 18 ወራት ዩኒሴፍ 18 ሺህ ህጻናት መገደላቸውን፣ ከ34 ሺህ በላይ መቁሰላቸውን እንዲሁም አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት በተደጋጋሚ መፈናቀላቸውን ገልጿል።

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ማንኛውም ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ ከአንድ ወር በፊት ክልከላ ማስቀመጧን ተከትሎ የሰብዓዊ ቀውሱ መክፋቱን የረድዔት ድርጅቶች እየገለጹ ነው።

በተጨማሪም በቅርቡ ስምንት የፍልስጤም የቀይ ጨረቃ ማህበር የህክምና ባለሙያዎች፣ ስድስት የሲቪል መከላለከያ ኤጀንሲ የመጀመሪያ እርዳታ ሰጭዎች እንዲሁም አንድ የተባበሩት መንግሥታት ሰራተኛ በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት በጋዛ የሚያደርገውን እንስቃሴ ገታ ማድረጉን አስታውቋል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ50 ሺህ 399በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሦስተኛው የጋዛ ሕንጻዎች መውደማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።