
ከ 7 ሰአት በፊት
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ዕድሜያቸው ከ18-30 ለሚሆኑ 160 ሺህ ወንዶች ወታደራዊ ጥሪ አድርገዋል።
ይህ ከአውሮፓውያኑ 2011 በኋላ የመጀመሪያው ሲሆን ሀገሪቱ ወታደራዊ ኃይሏን ለማስፋፋት ቆርጣ መነሳቷን ያሳያል ተብሏል።
በፀደይ ወቅት የሚጀምረው ወታደራዊ ሥልጠና ለአንድ ዓመት የሚቆይ ፑቲን ከወራት በፊት የወታደሮቿን ቁጥር 2.39 ሚሊዮን ማድረስ አለባት ብለው ነበር።
አክለው በተጠንቀቅ የሚጠብቁ ወታደሮችን ቁጥር 1.5 ሚሊዮን ማድረስ እንደሚፈልጉ አሳውቀዋል።
ይህ ማለት በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የሩሲያ ወታደር ቁጥር በ180 ሺህ ይጨምራል ማለት ነው።
ምክትል አድሚራል ቭላድሚር ሲምሊያንስኪ እንዳሉት አዳዲሶቹ ምልምሎች ሩሲያ “ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን” ወደምትለው የዩክሬን ጦርነት የሚላኩ አይደሉም።
ነገር ግን የዩክሬን ጦርነት የተጀመረ ሰሞን በሩሲያ ድንበር አካባቢ አዳዲስ ምልምል ወታደሮች በጦርነቱ መገደላቸው ተነግሮ ነበር።
ዩናይትድ ስቴትስ በዩክሬን ያለውን ጦርነት እንዲቋጭ ሙከራ እያደረገች ባለበት ወቅት ነው ሩሲያ አዳዲስ ምልምሎችን ለመመዝገብ ጥሪ ያቀረበችው።
ማክሰኞ ዕለት ሩሲያ በኼርሶን ከተማ በሚገኝ የኃይል ማመንጫ ላይ ባደረሰችው ጥቃት 45 ሺህ ሰዎች ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደቀሩ ዩክሬን ተናግራለች።
ምንም እንኳ ሩሲያ ሙሉ በሙሉ የተኩስ አቁም ይደረግ የሚለውን ባትቀበለውም የኃይል ማመንጫዎችን ላለመምታት ተስማምታ ነበር።
ሩሲያ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት የ150 ሺህ የምልምል ወታደሮች ምዘገባ ማድረጓ ይታወሳል።
- የአእምሮ ዕድገት መዛባት (Autism) ያለባቸው መኪና እንዲያሽከረክሩ የሚረዳ ጥናት ለኳታር ያቀረቡት ኢትዮጵያዊ ተመራማሪከ 8 ሰአት በፊት
- በቀን እስከ 24 ሺህ ሕጻናትን መግቤያለሁ፡ እማሆይ ጽጌ ግርማይከ 8 ሰአት በፊት
- ከአሜሪካ ተባረው በፓናማ ሆቴል እንዲቀመጡ የተደረጉት ኢትዮጵያዊያን እና ሌሎች ስደተኞች የገቡበት አጣብቂኝከ 8 ሰአት በፊት
ከዚህ ቀደም የወታደሮች ምልመላ ዕድሜ ገደብ 27 የነበረ ቢሆንም ይህ የዕደሜ ገደብ 30 እንዲሆን ከተደረገ በኋላ በርካታ ሰዎች ተመዝግበዋል።
የምዝገባ ጥሪው የሚካሄደው በፖስታ እና ጎሱስሉጊ በተባለው የመንግሥት ድረ-ገፅ አማካይነት ነው።
በርካታ ሩሲያዊያን ወታደራዊ ግዴታውን ላለመወጣት “አማራጭ የሲቪል ሥራ” መውሰድ መጀመራቸው እየተነገረ ነው።
ነገር ግን የሰብዓዊ መብት ጠበቃ የሆኑት ቲሞፌይ ቫስኪን ለገለልተኛ ሚድያ እንደተናገሩት ከጦርነቱ በኋላ የሚደረጉ ጥሪዎች ሎተሪ ሆነዋል ይላሉ። “ባለሥልጣናቱ የጦር ሠራዊቱን ለመሙላት አዳዲስ መንገዶችን እየተከተሉ ነው” ሲሉ ያብራራሉ።
ሩሲያ በዓመት ሁለት ጊዜ ከምታደርገው የምልምሎች ምዝገባ በተጨማሪ በርካታ በኮንትራክት የተቀጠሩ እንዲሁም ከሰሜን ኮሪያ የመጡ ወታደሮች አሏት።
ቢቢሲ እና ሚደያዞና ባጣሩት መሠረት ሩሲያ በጦርነቱ 100 ሺህ ገደማ ወታደሮችን አጥታለች። ነገር ግን ሞስኮው ለዚህ እስካሁን ምላሽ ሰጥታ አታውቅም።
በአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የሩሲያ ጦር ሠራዊት ቁጥር ሶስት እጥፍ የጨመረ ሲሆን ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ “ከዩክሬን የሚመነጭ ስጋት” እና “የኔቶ መስፋፋት” እንደሆነ ሞስኮው ትናገራለች።
ከዩክሬን ጦርነት በኋላ ፊንላንድ እና ስዊድን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን (ኔቶ) አባላት ሆነዋል።
ፊንላንድ ከሩሲያ ጋር 1342 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ድንበር ትጋራለች።