ቤቲ ዌብ

ከ 6 ሰአት በፊት

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጠላትን ምስጢራዊ መልዕክት በመስበር እውቅና ያተረፉት እንግሊዛዊት በ101 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ቻርሎት ቤቲ ዌብ ሰኞ ምሽት ማረፋቸውን የሴቶች ሮያል አርሚ ኮር ማኅበር አስታውቋል።

ዌብ ‘ብሌችሊ ኮድ ብሬከርስ’ ተብለው ከሚታወቁት የምስጢራዊ መልዕክት ሰባሪዎች መካከል በሕይወት የቆዩ ብቸኛዋ ሰው ነበሩ።

ቤቲ ዌብ ገና በ18 ዓመታቸው ነው ባኪንግሀምሸር የሚገኘውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ የተቀላቀሉት። ወደ አሜሪካው ፔንታገን አቅንተው የጃፓን ምስጢራዊ መልዕክቶችን በመፍታትም አግዘዋል።

በ2021 የፈረንሳይ ከፍተኛውን ወታደራዊ ማዕረግ ተሸልመዋል።

የሴቶች ሮያል አርሚ ኮር ማኅበር በለቀቀው መግለጫ ቤቲ ዌብ “ለአስርታት ሴቶች በጦር ሠራዊቱ ያላቸውን ሚና እንዲነቃቃ ያደረጉ ናቸው” ብሏል።

ብሌችሊ ፓርክ ትረስት የተባለው ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢያን ስታንዴን፤ ቤቲ ዌብ በሥራቸው ብቻ ሳይሆን “እሳቸው እና አጋሮቻቸው የሠሩት ሥራ እንዳይረሳ በማድረጋቸውም ይታወሳሉ” ብለዋል።

ቤቲ ዌብ በአውሮፓውያኑ 2020 ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ-ምልልስ እንደተናገሩት የምስጢራዊ መልዕክት መስበሪያውን እንቅስቃሴ እስኪቀላቀሉ ድረስ ስለሙያው እውቀት አልነበራቸውም።

በወቅቱ በአቅራቢያው በሚገኝ ኮሌጅ እየተማሩ ነበር። ነገር ግን “ቋሊማ ከማዘጋጀት ባለፈ ሀገራችንን እናገልግል” በሚል ቡድኑን መቀላቀላቸውን ያወሳሉ።

በልጅነታቸው እናታቸው ጀርመንኛ ቋንቋ እንዳስተማሯቸው ተናግረው ይህ ምስጢራዊ መልዕክቶችን ለመፍታት እንዳገዛቸው ይመሰክራሉ።

ምስጢራዊ መልዕክት የሚፈታውን ቡድን ከተቀላቀሉ በኋላ ለቤተሰቦቻቸው የት እንዳሉ እና ምን እንደሚሰሩ ሳይናገሩ እስከ 1975 እንደቆዩም ያስታውሳሉ።

ባረፉበት ቤት ሁሉ ሥራቸውም ምን እንደሆነ ሲጠየቁ ፀሐፊ የሚል ነበር ምላሻቸው።

ለአራት ዓመታት ብሌችሊ ካገለገሉ በኋላ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1945 ሲቋጭ ወደ አሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ፔንታገን አቅንተው ማገልገል ጀመሩ።

በፔንታገን የነበራቸው ሥራ የተፈቱ በጃፓንኛ የተፃፉ ምስጢራዊ መልዕክቶችን ማሰባጠር እና መተንተን ነበር።

አሜሪካ ጃፓን ላይ አቶሚክ ቦምብ ልትጥል እንደምትችል እንደማያውቁ የሚናገሩት ቤቲ ዌብ ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ተመልሰው ሽሮፕሸር አካባቢ በሚገኝ ትምህርት ቤት ፀሐፊ ሆነው ማገልግል ጀመሩ።

በ2014 በፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ፋራንኳ ኦላንድ የፈረንሳይ ከፍተኛ ማዕረግ የሆነው ልጊዮን ደኦነር ከተሰጣቸው 6 ሺህ ብሪታኒያዊያን መካከል አንዷ ቤቲ ዌብ ነበሩ።

በ2023 ደግሞ የንጉሥ ቻርልስን የንግሥና ሲመት ለመታደም ከ203 ሀገራት ከተጋበዙ 2200 ሰዎች መካከል አንዷ ነበሩ።