የኦቲዝም እክል ባለበት ልጇ ጥቃት የደረሰባት ክሌር ሚለር
የምስሉ መግለጫ,የኦቲዝም እክል ባለበት ልጇ ጥቃት የደረሰባት ክሌር ሚለር

ከ 9 ሰአት በፊት

ልጆች ማሳደግ ቀላል አይደለም።

ከዕለት ጉርሳቸው፣ ትምህርታቸው፣ በሥነ ምግባር መቅረጽ፣ ሌላም ሌላም ከፍተኛ ኃላፊነት በወላጆች ላይ ወድቋል።

ልጆችን በመንከባከብም ሆነ በሌሎች ኃላፊነት ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ ሲደጋገፉ ሁኔታዎች ቀለል ይላሉ።

ሆኖም ምንም ዓይነት ድጋፍ አለመኖር ልጅ ማሳደግን የበለጠ ከባድ ያደርገዋል።

የአእምሮ ዕድገት ሥርዓት መዛባት የሆነው ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ደግሞ ያለ ድጋፍ፣ በራስ ብቻ መንከባከብ የበለጠ ፈታኝ ነው።

የሰሜን አየርላንድ ነዋሪ የሆነችው ክሌር ሚለር ኦቲዝም ያለበት ልጇ በእሷም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት ያደርሳል።

እናቱም የዚህ ተጠቂ ናት፤ በእሷ ላይ ጥቃት ፈጽሞ ለሆስፒታል ዳርጓታል።

ለዚያም ነው “ከልጄ ጋር ስሆን ደኅንነት አይሰማኝም” የምትለው።

ልጇ ዳኒ ከኦቲዝም በተጨማሪ ከፍተኛ የመማር ውስንነት አለበት።

በራሱ እንዲሁም በሌሎች ላይ ጉዳቶችን የሚያስከትሉ ባህርያትን ጨምሮ ሁኔታዎችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎባታል።

“ከልጄ ጋር ብቻዬን ስሆን ደኅንነት አይሰማኝም። ሆኖም የእሱ ጥፋት አይደለም” ትላለች።

እናቱ በድጋፍ እጦት ምክንያት ልጇን ብቻዋን ለማሳደግ ተስኖኛል ትላላች።

ልጇንም መንከባብ ለሚችለው ለማኅበራዊ አገልግሎት ለመስጠት አስባለች።

የክሌር እና ሌሎች ሦስት እናቶች ከልጆቻቸው ጋር የገቡትን ምስቅልቅል ጉዞ ቢቢሲ በሠራው ‘አይ አም ኖት ኦኬይ’ በተሰኘ ፊልም ላይ ተዳስሷል።

ፊልሙ ለዕይታ ከበቃ በኋላ የሰሜን አየርላንድ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ማይክ ነስቢት በርካታ ሚሊዮን ፓውንድ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ነገር ግን ድጋፉ ለእናቶቹ ገና አልደረሰም።

ድጋፉ የአካል ጉዳተኛ ልጆችን የሚንከባከቡ ቤተሰቦች በመኖሪያ ቤታቸው እንዲሁም በውጭ እረፍት እንዲያገኙ ወይም ሁኔታቸው እንዲሻሻል የሚደረገውን ጥረት “እንዳፋጠነው” አንድ የጤና ጥበቃ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

የአካል ጉዳተኛ ልጆች ቁጥር መጨመር ያሉ አገልግሎቶች ሽፋን እንዲሰጡ ከአቅም በላይ መለጠጥን ጨምሮ በርካታ ያልተሟሉ ጉዳዮች መኖራቸውን ባለሥልጣኑ ሞውሪስ ሊሰን ያስረዳሉ።

በሰሜን አየርላንድ የጤና ኮሚቴ ጉባዔ ቀርበው አስተያየታቸውን የሰጡት ባለሥልጣኑ ፍላጎት እና አቅምን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እንዲሁም አገልግሎቶችን ለማሳደግ ትልቅ ማሻሻያ መደረጉን ተናግረዋል።

በጤና ሚኒስትሩ ከተመደበው 2 ሚሊዮን ፓውንድ ውስጥ 1.7 ሚሊዮኑ ጥቅም ላይ ውሏል ብለዋል።

የወላጆችን የእረፍት ጊዜዎችን ጨምሮ “ሊለኩ የሚችሉ ማሻሻያዎች መምጣታቸውን አስረድተዋል።

ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶችን ለማስፋት መታቀዱንም ባለሥልጣኑ አክለዋል።

ኦቲዝም ባለበት ልጇ ጥቃት የደረሰባት ክሌር ሚለር
የምስሉ መግለጫ,ኦቲዝም ባለበት ልጇ ጥቃት የደረሰባት ክሌር ሚለር

“ራሴን አምቡላንስ ውስጥ አገኘሁት “

እናቶቹ ያለድጋፍ ከልጆቻቸው የሚያደርጉትን የማያቋርጥ ትግል በፊልሙ እንዲታይ ፈቅደዋል።

በርካታ የሚያሳዝኑ ትዕይንቶች በካሜራ ተቀርጸዋል።

እነዚሁ እናቶች ለዚሁ የጤና ኮሚቴ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ቤተሰቦቹ ይህ የገንዘብ ድጋፍ ለአሳዳጊዎች ወይም ለወላጆች ከተንከባካቢነት ኃላፊነታቸው እረፍት እንዲወስዱ የሚያደርግ እንዲሆን ተስፋ አድርገው ነበር።

የሚንከቧከቧቸው ልጆች በዩናይትድ ኪንግደም የጤና አገልግሎት ቅርንጫፍ በሆኑ ማዕከላት ውስጥ ሌሊቶችን እንዲያሳልፉ በማድረግ እፎይታን ለማግኘት ሽተው ነበር።

የኮቪድ ወረርሽኝን ተከትሎ ወላጆቹም የሚያገኙት እረፍት እንደቆመ ነው።

ክሌር በበኩሏ ፈልሙ ከተለቀቀ በኋላ ኑሮዋ የበለጠ መክፋቱን ታስረዳለች።

ባለፈው የካቲት ላይ በልጇ ጥቃት እንደፈጸመባት በሐዘን ገልጻለች።

“ከሦስት ሳምንት በፊት ዳኒን ማለዳ እያዘገጃጀሁት ነበር። ሰዓቱን ስመለከት ከጥዋቱ 2፡15 ነበር” ትላለች።

“በመቀጠል የማስታውሰው ከቀኑ ስድስት ሰዓት አልፏል። በአምቡላንስ ውስጥ ራሴን አገኘሁት” ብላለች።

ክሌር በእነዚህ ሰዓታት የተከናወነውን ነገር ማስታወስ አትችልም። ራሷንም ስታ ለሁለት ቀናት ያህል በሆስፒታል አሳልፋለች።

በእነዚያ ሰዓታት የተከናወኑትን ክፍተት መሙላት የቻለችው በወቅቱ ሌላኛዋን ሴት ልጇን ሲንከባከቡ የነበሩት እናቷ በቤቷ በመገኘታቸው ነው።

“ከፍተኛ መጠን ያለው ፀጉሬን ነጨው። ከዚያም መሬት ላይ ክፉኛ ወደቅኩ” ትላለች።

ክሌር በዚህ አደጋ ምክንያት የማስታወስ ችግር ደርሶባታል፤ እንዲሁም ንግግሯም በሚታይ መልኩ ዘገምተኛ ሆኗል።

“በዚያን ቀን በፊልሙ ላይ ከተሳተፉት እናቶች ከአንዷ ጋር በመሆን ከዩኬ ጤና አገልግሎት ጋር ቀጠሮ ነበረን። ሆኖም በሚያሳዝን ሁኔታ መገኘት አልቻልኩም” ትላለች።

ኦቲዝም ባለበት ልጇ ጥቃት የደረሰባት ክሌር ሚለር
የምስሉ መግለጫ,ኦቲዝም ባለበት ልጇ ጥቃት የደረሰባት ክሌር ሚለር

“በዚህ አደጋ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ተሰባብሬያለሁ” ስትል ክሌር ታስረዳለች።

በፊልሙ ላይ የተሳተፈችው ሌላኛዋ እናት ካርሊ ብሬይደንም እንዲሁ የልጇ የሩዲ ባህርይ እየከፋ መምጣቱን አስተውላለች።

“አንዳንዴ ካልሆነ በስተቀር ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አይችልም። ለራሱ እና ለሌሎች አደገኛ እንደሆነም ተቆጥሯል” ብላለች።

“ነገር ግን በሕይወቱ መደበኛ ፕሮግራም ስለሌለው በቤትም ውስጥ የአእምሮ እና የአካል ጤንነቱን እየከፋ ነው።”

በዚህም ምክንያት በመኖሪያ ቤታቸው ችግር አንዳንዴም የከበደ ክስተት መፈጠሩ አልቀረም። በአንድ ወቅትም ፖሊስ ተጠርቷል።

“ከመኖሪያ ቤቴ ውጪ ፖሊስን ጨምሮ 14 ባለሙያዎች ተገኙ” ትላለች።

“የሚሄድበት ቦታ ስለሌለ ለታዳጊ ታራሚዎች መቆያ በሆነው ሃይዴባንክ እንዲሄድ ሃሳብ አቀረቡ።”

“ይህ በጣም አስገራሚ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ሻንጣ አውጥቼ የዳይፐር ፓንቱን ሳስገባ ያኔ ኦቲዝም ላለበት እና ለማይናገር ልጅ የማይሆን ስፍራ እንደሚሆን ተገነዘቡት።”

የላውራ ፍላኒጋን ልጅ ኤዎይን ቢቢሲ ፊልሙን መሥራት ከጀመረ አንድ ዓመትን ጨምሯል።

ሆኖም ምንም ዓይነት እርዳታ እንዳላገኘች እና የተለያዩ አማራጮች እየታዩ ስለሆኑ እንዲጠብቁ ተነግሯቸዋል። ነገር ግን “ምንም ዓይነት ለውጥ አልመጣም” ትላለች።

ኦቲዝም ባለበት ልጇ ጥቃት የደረሰባት ክሌር ሚለር
የምስሉ መግለጫ,ኦቲዘም ባለበት ልጇ ጥቃት የደረሰባት ክሌር ሚለር

‘አፍረናል’

ፊልሙ ለዕይታ ከበቃ በኋላ ወላጆች እረፍት እንዲያገኙ የሚደረገው እገዛ ለይስሙላ ብቻ መነሳቱን ሌላኛው የጤና ሚኒስቴር ባለሥልጣን ናይጀል ቻምበርስ ያምናሉ።

ሆኖም በሚቀጥለው የበጀት ዓመት ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚጀምሩ ቃል ገብተዋል።

ናይጀል ቻምበርስ ፊልሙ ከተለቀቀበት ጊዜ አንስቶ አብዛኞቹ ተግባራት የተሠሩት በፍጥነት ማሳደግ በሚቻል ሌሎች አገልግሎቶች ላይ አተኩሯል ብለዋል።

“እፍረት ይሰማናል” ሲሉም አስረድተዋል።

“ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ከአቅርቦቱ በላይ በሆነበት በዚህ ሥርዓት ውስጥ መሥራት አሳፋሪ ነው” ብለዋል።