
ከ 1 ሰአት በፊት
ባለፈው ዓመት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተሞክሮ በከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ላይ በመሳተፍ ተከስሰው የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሦስት አሜሪካውያን፣ ፍርዳቸው ወደ እድሜ ልክ እስራት እንዲቀየር መደረጉን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አስታወቁ።
ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ፕሬዚደንት ከሥልጣን ለማስወገድ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በመፈፀም ሦስት አሜሪካውያን፣ እንግሊዛዊ፣ ቤልጂየማዊ እና ካናዳዊን ጨምሮ 37 ግለሰቦች የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል።
ግለሰቦቹ ግንቦት ወር ላይ በፕሬዚደንቱ ቤተ መንግሥት እና የፕሬዚደንት ፊሊክስ ታሺኬዲ አጋር መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት እንዲፈፀም በመምራት ነበር ክስ የቀረበባቸው።
መፈንቅለ መንግሥቱ እንዲፈፀም በመምራት የተጠረጠረው ትውልደ ኮንጎያዊው የሆነው አሜሪካዊው ክርስቲያን ማላንጋ በጥቃቱ ወቅት ከሌሎች 5 ግለሰቦች ጋር ተገድሏል።
በአሜሪካውያኑ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መቀየሩ የተሰማው የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቦሎስ ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጉብኝት ከማድረጋቸው በፊት ነው።
የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሴት ልጅ፣ ቲፋኒ አማች የሆኑት ቦሎስ ነገ ሐሙስ ወደ ሩዋንዳ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ የሚያደርጉትን ጉዞ ወደ ኪንሻሳ በማቅናት ይጀምራሉ።
አሜሪካ ሦስቱ አሜሪካውያን በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ስለታሰሩበት ሁኔታ ምንም ባትልም፣ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ በአገሮቹ መካከል ውይይት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።
ሦስቱ አሜሪካውያን ወንጀል በማሴር፣ በሽብርተኝነት እና በሌሎች ክሶች የተከሰሱ ቢሆንም እነርሱ ግን ይህንን አስተባብለው ተከራክረዋል።
መፈንቅለ መንግሥቱ እንዲፈፀም በመምራት የተጠረጠረው ትውልደ ኮንጎያዊው የሆነው አሜሪካዊው ክርስቲያን ማላንጋ በጥቃቱ ወቅት ከሌሎች 5 ግለሰቦች ጋር ተገድሏል።
በአጠቃላይ 51 ሰዎች በወታደራዊ ፍርድ ቤት ክስ የቀረበባቸው ግለሰቦች የፍርድ ሂደቱ በብሔራዊ ቴሌቪዥን እና በራዲዮ በቀጥታ ተላልፏል።
ከተከሰሱት መካከል 14 ሰዎች ፍርድ ቤቱ ከጥቃቱ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው በማረጋገጡ በነጻ ተለቅቀዋል።
- በኮንጎው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ዜጎችን ጨምሮ 37 ግለሰቦች ሞት ተፈረደባቸው14 መስከረም 2024
- ትራምፕ በግጭት ከምትታመሰው ዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር የማዕድን ውል ለመግባት እያሰቡ ይሆን?13 መጋቢት 2025
- የዲሞክራቲክ ኮንጎ ማዕቀብ በሞባይል እና በመኪኖች ዋጋ ላይ ጭማሪ ያስከትላል ተባለ6 መጋቢት 2025
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል የሞት ፍርድ ተፈጽሞ የማያውቅ ሲሆን፣ ቅጣቱ የሚጣልባቸው ወንጀለኞች በእድሜ ልክ እስራት ይቀጣሉ።
መንግሥት ይህንን የሞት ፍርድ ተግባራዊ ለማድረግ ውሳኔ ያሳለፈው በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ ከአገሪቱ ሠራዊት ውስጥ “ከሃዲዎችን” ማስወገድ አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ነው።
ሆኖም ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሞት ቅጣት አልተፈጸመም።
ማክሰኞ ዕለት ፕሬዚደንት ቲሺሴኬዲ የአሜሪካውያንን የሞት ፍርድ ለመለወጥ የሚያስችል ውሳኔ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸውን ቃል አቀባያቸው ቲና ሳላማ ተናግረዋል።
ሦስቱ አሜሪካውያን ማርሴል ማላንጋ ማሉ፣ ታይሎር ቶምሰን እና ዛልማን ፖሉን ቤንጃሚን በፕሬዚዳንቱ “ይቅርታ” ተደርጎላቸዋል በማለት ሳላማ በመግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል።
ከማላጋ ጠበቆች አንዱ የሆኑት ክኪነስ ሲያምባ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት “የፕሬዝዳንት ይቅርታው ወደፊት ትልቅ ለውጥ እንደሚመጣ ተስፋ የሚሰጥ የመጀመሪያ እርምጃ ነው” ብለዋል።
የሞት ፍርድ የተፈረደበት የኮንጎ እና የቤልጂየም ዜግነት ያለው ዣን ዣክ ዎንዶ በጤና እክል ምክንያት በየካቲት ወር ወደ ቤልጂየም ተዛውሯል።
አሜሪካውያን የቅጣት ፍርዳቸውን ለመፈጸም ወደ አገራቸው ሊላኩ ይችሉ እንደሆነ ግልጽ የሆነ ነገር የለም።
የብሪታንያ፣ ቤልጂየም እና ካናዳ ዜግነት ያላቸው ሌሎች ተከሳሾችም ቅጣታቸው ይቀነስላቸው እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም።
የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የተፈፀመው በመዲናዋ ኪንሻሳ ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ነበር። የታጠቁ ሰዎች መጀመሪያ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ቪታል ካመርሄ ቤት ላይ ጥቃት የፈፀሙ ሲሆን ከዚያም ወደ ፕሬዚደንቱ መኖሪያ ቤት አቅንተዋል።
በወቅቱ የዓይን ምስክሮች እንደተናገሩት የጦሩን የደንብ ልብስ የለበሱ 20 ግለሰቦች ቤተመንግሥቱ ላይ ጥቃት ሲፈፅሙ እና የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ ነበር።
በኋላ ላይም የጦሩ ቃል አቀባይ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ሊፈፀም ታቅዶ የነበረውን መፈንቅለ መንግሥት ጦሩ ማክሸፉን አስታውቀዋል።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ጥቃት ፈፃሚዎቹ ከኮንጎያዊ ፖለቲከኛ ማላንጋ ጋር የሚገናኘው ኒው ዛየር እንቅስቃሴ አባላት ናቸው።
ማላንጋ እጁን ለመስጠት ፈቃደኛ ስላልነበር በተከፈተበት ተኩስ መገደሉንም በወቅቱ የጦሩ ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ጀነራል ስይላቪን ኢኬንጌ ተናግረዋል።
መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተካሄደባቸው ፕሬዚደንት ታሺኬዲም ታኅሳስ ወር ላይ በተካሄደው አወዛጋቢ ምርጫ 78 በመቶ ድምጽ በማግኘት ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠዋል።
ዲሞክራቲክ ኮንጎ በማዕድን የበለፀገችና በርካታ ሕዝብ ያላት አገር ብትሆንም በአገሪቷ ውስጥ ባለው ግጭት፣ ሙስና እና ደካማ አስተዳደር ለበርካቶች ሕይወት ፈተና ሆኖባቸዋል።
ምንም እንኳን ፕሬዚደንቱ ግጭቶችን ለመፍታት አስቸኳይ ጊዜ ቢያውጁም፣ ከታጣቂዎች ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ቢፈፅሙም፣ የጎረቤት አገራት ወታደሮችን ቢያሰማሩም አብዛኛው የአገሪቷ ተፈጥሯዊ ኃብት የሚገኝበት ምስራቃዊ የአገሪቷ ክፍል በግጭት ውስጥ ነው የሚገኘው።