ሲሙሌተር

ከ 9 ሰአት በፊት

ዛሬ፣መጋቢት 24 የኦቲዝም ግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን ነው።

ይህ ዕለት በዓለም ደረጃ ታስቦ እንዲውል ለተባበሩት መንግሥታት ሐሳብ ያቀረበችው ኳታር ናት።

ወደዚያው ብናቀና ዶክተር ወንድወሰን ግርማን እናገኛለን።

በኦቲዝም ኅብር (Autism spectrum) ውስጥ ያሉ ሰዎች መኪና እንዲያሽከረክሩ የሚያስችል ከፍተኛ ምርምር ያደረጉ ኢትዮጵያዊ ናቸው።

ብዙ ጊዜ ‘ኦቲዝም’ የአእምሮ ውስንነት ተብሎ በግርድፉ በስንፍና ይተረጎማል። ዶ/ር ወንድወሰን ይህ ትርጓሜ ይጎረብጣቸዋል።

”የአእምሮ አሠራር ልዩነት” በሚል ቢገለጽ ይመርጣሉ።

ለምን ሲባሉ፣ ‘ኦቲዝም’ ውስንነት ሳይሆን ‘የአእምሮ የአሠራር ልዩነት’ ስለሆነ ነው ይላሉ። እንዲህ ያብራሩታል።

“እኔ ለምሳሌ ስሜቴን መግራት ችግር ሊኖርብኝ ይችላል። አንተ ደግሞ ቁጥር ስሌት ጊዜ ሊወስድብህ ይችላል። ሌላ ሰው ተግባቦት ላይ ደከም ይላል። የዕድገት ውስንነት ነው ከተባለ ከእኛ ውስጥ ማን ‘ውስንነት’ የሌለበት አለ? “

ለዚህ ጽሑፍ የዶ/ር ዮናስ ባሕረ ጥበብን አገላለጽ ተውሰን ብንቀጥልስ?

ዶ/ር ዮናስ የአእምሮ ሕክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው። በጉዳዩ ላይ “ዓይኔን ተመልከተኝ” የሚል ግሩም መጽሐፍ ጽፈዋል። ይህን ‘ኦቲዝም’ የሚለውን እክል ”የአእምሮ ዕድገት ሥርዓት መዛባት” በሚል ይገልጹታል።

ይህ ነገር በዓለም እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልሄደም። ለምን ለሚለው ማንም ምላሽ የለውም።

በአሜሪካ በአሁኑ ጊዜ ከ36 ሕጻናት አንዱ የአዕምሮ ዕድገት መዛባት አለበት።

ከ20 ዓመት በፊት ከ500 ልጆች አንዱ ብቻ ነበር ይህ የዕድገት መዛባት የሚገጥመው። ከ80 ዓመት በፊት ግን ከ10ሺህ ልጆች አንዱ ብቻ።

ፍጥነቱ ያስደነግጣል።

በዓለም 75 ሚሊዮን፣ በአገራችን 5 ሚሊዮን ሰዎች ይህ ‘ ”የአእምሮ ዕድገት ሥርዓት መዛባት”’ አለባቸው ይላሉ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚወጡ ሰነዶች።

ለምንድነው እየጨመረ የመጣው የሚለው ትልቅ ጥያቄ ይቆየን።

‘የኦቲዝም ኅብር’ ውስጥ ያሉ ኑሯቸው እንዴት ይሻሻል የሚለው አጀንዳ ላይ ይበልጥ እናተኩር።

መሪ ሲጨብጡ ማየት

ሲሙሌተር ቤተ ሙከራ

ብዙዎቹ በዚህ የአእምሮ ዕድገት መዛባት ኅብር ጥላ ሥር ያሉ ሰዎች በሌሎች ላይ ጥገኛ ናቸው። ይሄ እንዲያበቃ ሳይንስ ብዙ ርቀት እየሄደ ነው።

በኳታር ዩኒቨርስቲ የሚመራመሩት ዶክተር ወንድወሰን፣ ‘የአእምሮ ዕድገት መዛባቱ ያለባቸው’ መኪና እንዲያሽከረክሩ የሚያስችል ምርምር የጀመሩት ከአራት ዓመት በፊት ነበር።

የኳታሩ ዩኒቨርስቲ ከቤልጂየሙ ሐሰልት ዩኒቨርስቲ ጋር በቅንጅት ይሠራል።

እርሳቸው የዚያ ፕሮጀክት አካል ሆነው ነው ከስምንት ባልደረቦቻቸው ጋር ጥናት የጀመሩት።

አሁን በኳታር መንግሥት ተቀባይነት ያገኘ በ’ኦቲዝም ኅብር ሥር’ ለሚኖሩ ሰዎች’ የሚሆን የአሽከርካሪዎች ማሠልጠኛ ማንዋል አቅርበዋል።

በአረብኛ እና በእንግሊዝኛ ተዘጋጅቶ በኳታር የአሽከርካሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለአገልግሎት ተሰናድቷል።

ምርምሩ ግብ አድርጎ የተነሳው በዕድገት መዛባት ኅብር ሥር ያሉ ሰዎችን በከፊልም ቢሆን ከጥገኝነት ለማላቀቅ ነው።

”እነሱ መሪ ሲጨብጡ እና ራሳቸውን ሲችሉ ማየት ትልቅ እርካታ የሚሰጥ ነው” ይላሉ፣ ዶ/ር ወንድወሰን።

ጥናታቸው ሰው ሠራሽ አስተውሎት በተገጠመላቸው መኪናዎች ላይ ያተኮረ አይደለም።በዚያ ረገድ ሳይንስ ብዙ ርቀት ሄዷል።

የርሳቸው ጥናት በተለምዶ ‘ማንዋል እና አውቶማቲክ’ በሚባሉት መደበኛ ተሽከርካሪዎች ላይ ያተኮረ ነው። የዕድገት መዛባቱ ያለባቸው በራሳቸው እነዚህን መኪናዎች እንንዲያሽከርክሩ ማስቻል ነው፣ የጥናቱ ዋና ግብ።

ሐሳቡ እንዴት ተጠነሰሰ?

የዕድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች በባሕረ ሰላጤው አገራት ቁጥራቸው ትንሽ ከፍ ይላል።

ለዚህ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ግርድፍ ጥናቶች ነገሩ ከቅርብ ዘመድ ጋብቻ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ይጠቁማሉ። ምርምሩ ግን እንደቀጠለ ነው።

በኳታር ዕድሜያቸው ከ6 እስከ 11 ባሉ አዳጊዎች ከ87ቱ አንዱ ‘በኦቲዝም ኅብር (Autism Spectrum) ጥላ ሥር ነው።

በዚህም የተነሳ የኳታር መንግሥት ከፍተኛ በጀት መድቦ ከሚሠራባቸው ዘርፎች አንዱ እነዚህን ዜጎች ማገዝ ላይ ነው።

ኑሯቸውን ምቹና ቀላል ለማድረግ ይተጋል።

ኳታር ፋውንዴሽን በዚህ ረገድ ስሙ በበጎ ይነሳል። በኦቲዝም ጉዳይ ለሚደረግ ጥናት እና ምርምር ሳይሰስት በጀት ይመድባል።

እንዳለመታደል በኦቲዝም ኅብር (Autism Spectrum) ጥላ ሥር የሚኖሩ ሰዎች ብዙዎቹ በዕለታዊ ኑሮ አድራሽ-መላሽ- አጉራሽ ያስፈልጋቸዋል።

ለምን ግን መኪና በራሳቸው እንዲያሽከረክሩ አይሞከርም? የሚለው በአንድ ዘመን ለብዙዎች ‘የእብድ ሐሳብ’ ነበር የሚመስለው።

በኳታር ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ የትራንስፖር ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ወንድወሰን ከዚህ ‘ያልተለመደ’ ጥያቄ ነው የተነሱት።

ዶ/ር ወንድወሰን ይህን ኮስተር ብለው እንዲያስቡ ያደረጋቸው ምናልባት በቀደመ ሙያቸው የሥነ ልቦና አጥኚ መሆናቸው ሊሆን ይችላል።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እና ከዚያ በኋላ በተለያዩ የአውሮፓ ዩኒቨርስቲዎች የሠሯቸው ሁለት ተከታታይ የማስተርስ ዲግሪዎች በልጆች ዕድገት እና ሥነ ልቡና ላይ ያተኮሩ ነበሩ።

ሦስተኛው ማስተርሳቸው ደግሞ የትራንስፖርት ሳይንስ ነው።

ይህ ጥምዝምዝ የትምህርት ጉዞ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በኦቲዝም ኅብር ጥላ ሥር በሚኖሩ ሰዎች የመኪና ማሽከርከር ጉዳይ ላይ እንዲያተኩር አደረገው።

ዶ/ር ወንድወሰን በቤልጂየም ሐሰልት ዩኒቨርስቲ በትራንስፖርት ዘርፍ በከፍተኛ ማዕረግ ከተመረቁ በኋላ ነው ወደ ኳታር ያቀኑት።

በታዋቂው ሐሰልት ዩኒቨርሰቲ ያቀረቡት የጥናት ወረቀትም ‘የዓመቱ ምርጥ የምርምር ሥራ’ በሚል ሽልማት ተበርክቶለታል።

ከዚያ በኋላ የዶክትሬት ጥናቱን ገፉበት።

ዶ/ር ወንድወሰን፣ በኳታር ካርዋ የመንጃ ፈቃድ ትምህርት ቤት ሠልጣኞች ጋር
የምስሉ መግለጫ,ዶ/ር ወንድወሰን፣ በኳታር ካርዋ የመንጃ ፈቃድ ትምህርት ቤት ሠልጣኞች ጋር

ጥናቱ እንዴት ተሠራ?

እርሳቸው በመሩት እና ኳታር ፋውንዴሽን ባገዘው በዚህ ምርምር የአሽከርካሪ ትምህርት ቤት መምህራን እና በኦቲዝም ኅብር ጥላ ሥር የሚኖሩ ዜጎች ተሳትፈውበታል።

የአእምሮ ዕድገት መዛባት ያለባቸው ወጣቶች እንዴት መኪና ሊያሽከረክሩ ይችላሉ የሚለው የምርመሩ ዋና ማጠንጠኛ ሆነ።

“መጀመሪያ ያደረግነው የመኪና መለማመጃ ትምህርት ቤቶችን መገምገም ነበር” ይላሉ፣ ዶ/ር ወንድወሰን።

ከዚያ በኋላ ነው ‘በኦቲዝም ኅብር ጥላ ሥር’ ያሉ ሰዎች በትምህርት ቤቶቹ የሚገጥማቸውን ፈተና ወደመመርመር የገቡት።

“ኦቲዝም ሲባል ሁሉም አንድ አይደሉም፤ በአንድ አይጨፈለቁም፤ እንደ ቀስተ ደመና ኅብረ ቀለም (ስፔክትረም) ያለ ነው” የሚሉት ዶ/ር ወንድወሰን እርሳቸው የመሩት ጥናት በተወሰኑት ላይ ብቻ እንዳተኮረ ያብራራሉ።

“እኛ የወስድነው የአእምሮ ልኬታቸው [IQ] አማካይና ከዚያ በላይ የሆኑትን ብቻ ነው” ይላሉ።

የሚያሳዩት መገለጫ የተለያየ ነው፤ የተጣባቸው ባሕሪና ልማድ፣ የተግባቦት ተግዳሮት ደረጃ፣ የሚፈጽሙት የድግግሞሽ ድርጊት ዓይነት ወዘተ. . . ለየቅል ነው፤ ጥናቱን ከባድ የሚያደርገውም ይህ በመሆኑ ነው።

ከሚያመሳስሏቸው ባህሪያት መካከል ደግሞ ብዙዎቹ ድምጽ ይረብሻቸዋል። በተለይ የመኪና ጡሩንባ ያውካቸዋል።

ከመኪና የሚረጭ ብርሃን መቋቋም ያቅታቸዋል፣ አንዳንዶች ደግሞ ለረዥም ሰዓት በትንሽዬ ነገር ላይ አተኩሮ የመቆዘም አዝማሚያ ያሳያሉ።

ከለመዱት ነገር ውልፍት አይሉም። አዲስ ከባቢ ያስጨንቃቸዋል።

መንገዱ ላይ ባለች ጠጠር ወይ የመኪና መስታወት ላይ ባረፈች አንዲት ዝንብ ላይ ብቻ ፈዘው ሊቀሩ ይችላሉ።

መኪና ማሽከርከር ደግሞ አካባቢን በንቃት መቃኘት እና ከባባዊ ሁኔታን ፈጥኖ መረዳት ይሻል።

ይህ በመሆኑ ለነርሱ በተለየ የሚዘጋጅ የማሽከርከር ክኅሎት ሥልጠና እንደሚያስፈልጋቸው እሙን ነው።

የጥናቱ አንድ ግብ የነበረው ለእነርሱ የሚመች የአሽከርካሪ ሥልጠና ማሰናዳት ነበር።

በአንጻሩ በኳታር የአሽከርካሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መምህራኑ ስለ ‘ኦቲዝም’ ያላቸው ግንዛቤ በጣም አናሳ ሆኖ ተገኘ።

አንዳንዶቹ መምህራን በኦቲዝም ኅብር ጥላ ሥር ያሉ መኪና ተለማማጆችን ቀሰስ ሲሉባቸው ይጮኹባቸዋል።

”ያላ! ያላ!’ (ዳይ ዳይ!) እያሉ ያዋክቧቸዋል። ይሄ ደግሞ ለአንድ ‘በኦቲዝም ኅብር ጥላ ሥር ላለ እጅግ የሚያውክ ነው።”

ይህን ክፍተት ለመሙላት ምን ይደረግ?

የአሠልጣኞች ሥልጠና ተሰናዳ። አሰልጣኖች ሰልጣኞቹን እንዴት ማስተማር እንዳለባቸው ተማሩ።

ይህ ሥልጠና በዓይነቱ አዲስ ስለነበረ በኳታር ሚዲያ ሰፊ ሽፋን ያገኘ ነበር።

እንደ ‘መርሃባ’፣ ‘ገልፍ ታይምስ’ እና ኳታር ትሪቢዩን ሳይቀሩ ብዙ የአገሬው ጋዜጦች ሰፊ ሽፋን ሰጥተውታል።

ጋዜጦች
የምስሉ መግለጫ,ዶክተር ወንድወሰን ይሠሩት የነበረው ጥናት በኳታር ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ያገኘ ነበር

ለዚህ ጥናት የተመረጠው የኳታሩ ”ካርዋ የአሽከርካሪዎች ማሠልጠኛ” ነበር።

84 መምህራን እና ጥቂት በኦቲዝም ኅብር ጥላ ሥር የሚኖሩ ልጆች ለጥናቱ ተመረጡ።

መምህራኑ በሁለት ተከፈሉ።

ለግማሾቹ በኦቲዝም ዙሪያ ከፍተኛ ሥልጠና ተሰጣቸው።

ለምሳሌ የአእምሮ ዕድገት መዛባት ያለባቸው እንዴት በሰከነ መንገድ ማስተማር እንዳለባቸው፣ ልዩ ፍላጎታቸውን እንዴት መለየት እንደሚችሉ፣ የታመቀ አቅማቸውን በተመለከተ በጥሩ ሁኔታ እንዲረዱ ተደረጉ።

ሌሎቹ መመህራን ደግሞ ድሮ በሚያስተምሩበት ሁኔታ ማስተማር እንዲቀጥሉ ተደረገ።

ከረዥም ጊዜ በኋላ ውጤቱ ተለካ።

ለ28 ቀናት ሥልጠና በወሰዱ መምህራን የተማሩት የመንጃ ፈቃድ ፈተናን ሁሉም ባይሆን ብዙዎቹ አለፉ።

ባልሠለጠኑ መምህራን የተማሩት ደግሞ ሁሉም ወደቁ።

በኳታር የመንጃ ፈቃድ ፈተና የሚሰጠው በትራፊክ ፖሊስ መሥሪያ ቤት አማካኝነት ነው። ይህም የጥናቱን ገለልተኝነት የሚያጎላ ሆኖ ተወስዷል።

“ብዙዎቹ በኦቲዝም ኅብር ጥላ ሥር የሚኖሩ ተማሪዎች የጽሑፍ ፈተናውን 40 ጥያቄ ለመመለስ 10 ደቂቃም አልፈጀባቸውም። ውጤቱ አስደናቂ ነበር” ይላሉ ዶክተር ወንድወሰን።

ዶ/ር ወንድወሰን ግርማ በሐሰልት ዩኒቨርስቲ ጥናታቸውን ካቀረቡ በኋላ ከዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰሮች ጋር
የምስሉ መግለጫ,ዶ/ር ወንድወሰን ግርማ (ከመሀል) በሐሰልት ዩኒቨርስቲ ጥናታቸውን ካቀረቡ በኋላ ከዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰሮች ጋር

በኦቲዝም ጥላ የሚኖሩ መኪና ማሽከርከር የሚፈሩት ለምንድነው?

ይህን ለመረዳት ዶ/ር ወንድወሰንና የጥናት ቡድናቸው ምናባዊ የሬንጅ ሮቨር መኪና (Simulator) ተጠቅመዋል።

ይህ ‘ሲሙሌተር’ እውናዊውን ዓለም የሚያካትት ዘመናዊ መሣሪያ ነው።

”ንፋሱን፣ የሞተር ድምጽን፣ የተሽከርካሪ ትርምሱን፣ የእግረኛ ግርግሩን ሁሉ የሚወክሉ ነገሮች ተገጥመውለታል።”

ይሄ መሣሪያ ታዲያ ፍጥነትን፣ መንቀርፈፍን (deceleration)፣ የብርሃን ፍልቅታን፣ ርቀትን አደጋን ወዘተ መለካት ይችላል።

ሌላው ለምርምር የተጠቀሙት መሣሪያ የዓይን ብሌን ተቆጣጣሪ መሣሪያ (Eye tracker) ነበር።

የዚህ ዘመናዊ መሣሪያ ጥቅም በተገጠሙለት ካሜራ አማካኝነት የዓይን እርግብግቢት እና ውልውልን መለካት ነው።

“እየነዳህ የሆነች ነገርን ለስንት ሚሊ ሰከንድ ተመልክተህ በምን ፍጥነት እርምጃ ወሰድክ የሚለውን ጭምር ይለካል” ይላሉ ዶ/ር ወንድወሰን።

ለምሳሌ አንድ ሰው በዚህ ጋር ትንኝ እልፍ ስትል አይተሃል ተብሎ ቢጠየቅ “እረ በጭራሽ” ሊል ይችላል። ነገር ግን ብሌን ተቆጣጣሪው መሣሪያ ማየቱን ብቻ ሳይሆን ለስንት ማይክሮ ሰከንድ እንዳያት ይመዘግባል።

በጥናቱ እንደተመላከተው ተለማማጆቹ ከሌሎች በተለየ “መሪ ስጨብጥ የልብ ምቴ ይጨምራል፣ አደጋ አደርሳለሁ ብዬ እሰጋለሁ፣ ሰዎች ጎበዝ መኪና አሽከርካሪ እንዳልሆንኩ ያስባሉ ብዬ እጨነቃለሁ” ይሉ ነበር።

በዚህ ጥናት የተሳተፉት ሌላው የዶ/ር ወንድወሰን ባልደረባ የኳታር ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር፣ ዶ/ር ዋኢል አልሐጂያሲን “በተሻለ ደረጃ ያሉ ኦቲስቶች ሳይቀር መኪና ማሽከርከርን እንደቀላል አያዩትም፣ ለዚህም ምክንያት አለው” ሲሉ ‘መርሃባ’ ለተሰኘው የኳታር ጋዜጣ አስተያየት ሰጥተው ነበር።

እነዚህ ተማሪዎች ችግራቸው እና ስጋታቸው ከተለየ በኋላ በሠለጠኑ መምህራን አዲስ ሥልጠና ሲሰጣቸው የሚያሳይዋቸው ያለመረጋጋት ስሜቶች ረገብ ብለው መታየታቸው በጥናቱ ተፈትሿል።

ይህ በዶክተር ወንድወሰን እና በረዳት ፕሮፌሰሩ የተመራው ጥናት ያረጋገጠው አንድ አቅም ይኸው ነው። በኦቲዝም ኅብር ጥላ ሥር ያሉ የተለየ የሥልጠና ከባቢን ይሻሉ።

ከዚያ ሌላ ግን ይህ ጥናት እነሱ የችሎታ ማነስ አለባቸው የሚለውን ጥናቱ ውድቅ አድርጎታል። ነገሮችን የሚረዱበት መንገድ የተለየ ሊሆን ይችላል እንጂ የችሎታ ማነስ አልነበረም በአመዛኙ የተስተዋለው።

እሱን ከግምት ያስገባ ሥልጠና ከተሰጣቸው ከዕለታዊ ድጋፎች መላቀቅ እንደሚችሉ፣ በራሳቸው መቆም እንደሚችሉ ጥናቱ አረጋግጧል።

የምርምሩ አንድ ምዕራፍ የመኪና መለማመጃ ትምህርት ቤቶችን መፈተሽ ነበር
የምስሉ መግለጫ,በኳታር የመኪና መለማመጃ ትምህርት ቤት ጥናት ሲደረግ

ለአደጋ ቢጋለጡስ?

ለአደጋ ቢጋለጡስ? የሚለው ጥያቄ የአእምሮ ዕድገት መዛባት ያለባቸውን ብቻ የሚመለከት መሆን የለበትም ይላሉ ዶክተር ወንድወሰን።

ማንም አሽከርካሪ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል።

ጥያቄው መሆን ያለበት አደጋው የደረሰው መኪናው የተዘወረው ‘በኦቲዝም ጥላ ሥር ባለ ሰው ስለሆነ ነው ወይ? የሚለው ነው።

በዚህ ዓመታትን በወሰደው የነ ዶ/ር ወንድወሰን ጥናት መሠረት አደጋ የመከሰት ዕድሉን ለመቀነስ መደረግ ያለባቸውን ምክረ ሐሳቦች አቅርበዋል።

ለምሳሌ ለአንድ ድንገተኛ ክስተት ፈጣን ምላሽ የመስጠት ችግር (Reaction Limitation) ያለባቸው ለማጅ አሽከርካሪዎች የመጀመሪያውን ሦስት ወር መሀል መንገድ እንዳይነዱ ይደረጋል።

በዚህ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሰው የማይኖርበት ሰፈር ከአስተማሪ ጋር እንዲያሽከረክሩ ይደረጋል።

ሆን ተብሎ ድንገተኛ አደጋዎች (ሐዛርድ) እንዲያጋጥማቸው እየተደረገ ምላሻቸው ይታያል።

ሌላ ሦስት ወራት ደግሞ የጎዳና መሀል መስመርን (Middle Lane) ይዘው ያሽከረክራሉ። ይህም ከአስተማሪ ጋር የሚሆን ነው።

ዝርዝር ማኑዋሉ እንዲህ እንዲያ እያለ ችግሮቻቸው ላይ መሠረት ያደረገ ሥልጠና እንዲሰጣቸው ያስችላል።

መኪና ማሽከርከር በጊዜ ርዝማኔ ‘ልማዳዊ ተግባር’ (Habit) የሚሆን ክኅሎት ነው።

”አንዳንዴ እየነዳህ እንደሆነ ሳታስብ ብዙ ርቀት ትነዳና እንዴት እዚህ ድረስ ነዳሁ ብለህ ለራስህ ትደነግጣለህ”

ይህ ነገር በኦቲዝም ጥላ ላሉ ተለማማጆችም ይሠራል። ”ብዙዎቹ በ7 ወር ውስጥ እዚያ ደረጃ ይደርሳሉ” ይላሉ ዶ/ር ወንድወሰን።

የሚገርመው ብዙዎቹ በኦቲዝም ኅብር ሥር ያሉ በባህሪያቸው ሕግ አክባሪ (Rule Bound) ናቸው።

ለምሳሌ ርቀት ጠብቀው ያሽከረክራሉ። ለምሳሌ ከተነገራቸው የትራፊክ ሕግ ወልፈት አይሉም። በእርግጥ ይህ ጥቅምም ጉዳትም ሊኖረው ይችላል።

ጉዳቱ እንዳያመዝን ግን በሥልጠና የሚገራ ይሆናል።

‘ልደቴ የዛሬ 10 ዓመት በምን ቀን እንደዋለ ነገረኝ’

simulator

”ዓይኔን ተመልከተኝ” የሚል መጽሐፍ የጻፉት ዶክተር ዮናስ ባሕረ ጥበብ በመጽሐፋቸው ይህ ውስነነት ‘ኅብረቀለም’ እንደሆነ በስፋት አመላክተዋል።

እክል ያለባቸውን ልጆች ጨፍልቆ በአንድ ማየት እንደማይገባም ያወሳሉ።

ለምሳሌ አንዳንዶች ጽኑ የአእምሮ ብስለት ችግር አለባቸው። ሌሎች ደግሞ በሆነ አንድ ጉዳይ ላይ እጅግ የላቀ እና የረቀቀ ዕውቀት ይኖራቸዋል።

የእድገት እክሉን በአንድ መፈረጅ እንደማይገባም ይመክራሉ።

ይህን ሐሳብ የሚጋሩት ዶ/ር ወንድወሰን ምርምር ካደረጉባቸው ወጣቶች መካከል አንድ የኳታር ዜጋ እንዴት እንዳስደመማቸው ያስታውሳሉ።

“ወጣት ነው፤ እናቱ አስተዋወቁን። ልጃቸው ልዩ የስሌት ችሎታ እንዳለው ጠቆሙኝ። የልደቴን ቀን ጠየቀኝ፤ ነገርኩት። ከዚያ የዛሬ 10 ዓመት በምን ቀን እንደዋለ አስልቶ ነገረኝ። ይህን ሊነግረኝ ሰከንድ አልወሰደበትም” ይላሉ።

እሳቸው ግን ልጁ የነገራቸው ነገር ልክ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ ኮምፒውተር ውስጥ ገብተው ስሌት መስላት ነበረባቸው።

“የልጁን መልስ ትክክል ሰለመሆኑ ለመረዳት ዘለግ ያለ ጊዜ ወስዶብኛል።”

ሌላ የምርምሩ አካል የነበረና በኦቲዝም ኅብር ጥላ ሥር የሚኖር ልጅ ሲናገር ይርበተበታል፣ ዐረፍተ ነገሩ ይቆራረጣል። ነገር ግን አእምሮው ስል ሆኖ አግኝተነዋል ይላሉ።

“የብስለት ምጣኔውን (IQ) ለክተነው 109 ነበር። እኛ ፕሮፌሰሮቹ እንኳ ይህን ያህል የለንም።”

ዶ/ር ወንድወሰን የጥናቱ ትሩፋት ወደ ኢትዮጵያም እንዲዘልቅ ይመኛሉ።

“ዋናው ነገር ልጆቹ የአንድ ልዩ ክኅሎት ባለቤት መሆናቸውን መረዳት ነው። አሪፍ ከባቢ ከተመቻቸላቸው ታላቅ ፈጣሪዎች ናቸው።”

ምቹ ሁኔታ ካልተፈጠረላቸው ግን ለዓለም አዲስ ነገር ማበርከት ቀርቶ መንጃ ፈቃድ ለማውጣትም ይቸገራሉ።

“በእነርሱ አቅም የትየሌለነት ማመን ማቆም አይገባንም።ልዩነት ነው እንጂ ውስንነት አይደለም የምለውም ለዚሁ ነው።”