አርቴምስ ጋሰምዛዴህ
የምስሉ መግለጫ,አርቴምስ ጋሰምዛዴህ ከአሜሪካ ተባርራ ወደ ፓናማ ተልካለች

ከ 9 ሰአት በፊት

በርካታ የእስያ እና የአፍሪካ ስደተኞች በላቲን አሜሪካዋ አገር ፓናማ መዲና በሚገኝ ቅንጡ ሆቴል እንዳይወጡ ተዘግቶባቸው ቢገኝም በመስኮት በኩል እርዳታ ለማግኘት መማጸን ከጀመሩ አንድ ወር አልፏቸዋል።

ከአሜሪካ ወደ ፓናማ ርዕሰ መዲና ከተባረሩ በኋላ ስለቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

እንደ ኢራን፣ አፍጋኒስታን፣ ኔፓል፣ ፓኪስታን፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ካሜሮን፣ ኢትዮጵያ፣ ቻይና እና ሩሲያን ከመሳሰሉ አገራት የመጡ ናቸው ብሏል ፌይ አሌግሪያ የተባለ የኃይማኖት ተቋም።

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት 51 ስደተኞችን በአገሪቱ ዋና ከተማ እያስተናገደ ይገኛል።

የፓናማ መንግሥት በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሠረት ከአሜሪካ ወደ ፓናማ ሲቲ ከተባረሩት 299 ሰነድ አልባ ስደተኞች መካከል 192ቱ በፈቃዳቸው ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ተስማምተዋል።

ለመቆየት የወሰኑት ለ30 ቀናት ጊዜያዊ የሰብዓዊነት ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል።

ይህም በ60 ቀናት ሊራዘም ይችላል፤ ከዚያ በኋላ ግን ከፓናማ ሊባረሩ ይችላሉ።

ቢቢሲ ከተባረሩት መካከል ሦስቱን አነጋግሯል፤ ሁለቱ ኢራናዊያን ሲሆኑ እና አንዱ አፍጋኒስታናዊ ነው።

ሦስቱም ወደ አገራቸው መመለስን አይቀበሉትም።

“እአአ በ 2022 ኃይማኖቴን ቀይሬ ክርስቲያን ለመሆን ወሰንኩ። ኢራን ውስጥ ይህ የሞት ቅጣት ያስቀጣል” ስትል አርቴምስ ጋሰምዛዴህ ለቢቢሲ ተናግራለች።

የፓናማ መንግሥት በበኩሉ ወደ አገራቸው መመለስ የማይችሉ ስደተኞች ፈቃደኛ የሆነ ሦስተኛ አገር ማፈላላግ አለባቸው ብሏል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስደተኞች ግን የሚቀበላቸው አላገኙም።

በቅንጡው ድካፖሊስ ሆቴል ውስጥ የሚገኙ  ስደተኞች ተማጽኖ ሲያቀርቡ
የምስሉ መግለጫ,በቅንጡው ድካፖሊስ ሆቴል ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ተማጽኖ ሲያቀርቡ

ለመሆኑ እንዴት ፓናማ ደረሱ?

የኢራን መንግሥት በድብቅ የሚንቀሳቀስ ቤተእምነት አግኝቶ ሁለት ጓደኞቿን ካሰረ በኋላ አርቴምስ አገሯን ጥላ ሸሸች።

ሂጃብ በአግባቡ አለበሽም በሚል ምክንያት ተይዛ የተደበደበችው ወጣት ማህሳ አሚኒ ከተገደለች በኋላ “ኢራን ውስጥ የሂጃብ ጉዳይ አንገብጋቢ ሆኗል” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

አርቴምስ አሜሪካ ለመግባት መጀመሪያ ወደ ተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አቀናች። ከዚያም ወደ ደቡብ ኮሪያ እና ወደ ሜክሲኮ በመብረር አሜሪካ ደረሰች።

ጥገኝነት ለመጠየቅ በማሰብ ከታላቅ ወንድሟ ጋር በሕገ ወጥ መንገድ የአሜሪካ-ሜክሲኮን ድንበር አቋረጠች።

ካሊፎርኒያ ሳንዲያጎ ደርሳ በድንበር ጠባቂ ተያዘች።

ከጥቂት ቀናት በኋላ እሷ እና ሌሎች በርካታ የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ቴክሳስ እንደሚዛወሩ ቢነገራቸውም መዳረሻቸው ግን በፓናማ ሲቲ ሆነ።

ከትራምፕ አስተዳደር ጋር በተደረገው ስምምነት ፓናማ እንደ አርቴምስ ያሉ 299 ስደተኞችን ተቀብላለች።

ቢቢሲ ስለስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮችን ለማግኘት የፓናማና የአሜሪካ መንግሥታትን ቢያነጋግርም ምላሽ አላገኘም።

ስደተኞቹ መጀመሪያ ላይ በቅንጡው ዲካፖሊስ ሆቴል ለአንድ ሳምንት እንዲቆዩ ተደረገ።

የፓናማ የደህንነት ሚኒስትር ፍራንክ አብሪጎ በወቅቱ እንደተናገሩት ስደተኞቹ አልታሰሩም፤ ለደህንነታቸው ሲባል “በእኛ ጊዜያዊ ጥበቃ ላይ ሲሆኑ” በተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች ጥበቃ ይደረግላቸዋል።

የፓናማው ፕሬዝዳንት ሆዜ ራውል ሙሊኖ እና የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ
የምስሉ መግለጫ,የፓናማው ፕሬዝዳንት ሆዜ ራውል ሙሊኖ እና የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ

ቢቢሲ ያነጋገረው ሆህ* የተባለ አፍጋኒስታዊ ስደተኛ ግን “በሆቴሉ ውስጥ እንደ እስረኞች ነበርን” ብሏል።

“በክፍሉ በር ላይ የጥበቃ ዘቦች፣ፖሊስ እና የኢሚግሬሽን ባልደረቦች ነበሩ።”

በርካታ ስደተኞች በሆቴሉ መስኮት በኩል እርዳታ ለማግኘት ሲማጸኑ የሚያሳዩ ፎቶዎች ይፋ ሆነዋል።

ከውጭው ዓለም ጋር እና ከጠበቃዎች ጋር እንዳይገናኙ መከልከላቸው ተናግሯል።

“እነዚህ ሰዎች የዘፈቀደ አሠራር ሰለባ ሆነው ወደ ፓናማ ተዛውረዋል። ጥገኝነት የመጠየቅ ዕድል ሳይኖራቸው፣ ጠበቆችን ሳያገኙ ለሳምንታት ሙሉ በሙሉ መገለል የለባቸውም” ብለዋል የሂዩማን ራይትስ ዋች የአሜሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ጁዋኒታ ጎበርተስ።

171ቱ በፈቃዳቸው ወደ አገራቸው ለመመለስ መስማማታቸውን እና አሜሪካ የትራንስፖርት ወጪያቸውን እንደምትሸፍን የፓናማ መንግሥት ከሳምንት በኋላ አስታውቋል።

ለመመለስ ያልተስማሙት ደግሞ በዳሪየን ግዛት ወደሚገኘው ሳን ቪንሼንቴ ጣቢያ ይዘዋወራሉ።

ጣቢያው ወደ አሜሪካ ለመድረስ የሚሞክሩ ስደተኞች የሚቆዩበት ነው።

ጥቅጥቅ ካለ ደን አጠገብ የሚገኘው ጣቢያ ለመድረስ ከፓናማ ርዕሰ መዲና ለአራት ሰዓታት ያህል በመኪና መጓዝን ይጠይቃል።

ከጥበቃ ሠራተኞች የተሰጠውን መመሪያ ተከትሎ ሆህ ከደካፖሊስ ሆቴል ፊት ለፊት የቆመውን አውቶብስ ሲሳፈር ይህንን ውሳኔ አላወቀም ነበር።

“ሆቴላችንን እንደሚቀይሩ ነግረውን አውቶቡስ ውስጥ አስገቡን። ከስምንት ሰዓት በኋላ ዳሪየን ጫካ ውስጥ መሆናችንን ተረዳን።”

 ወደ ፓናማ ከባረሩት መካከል አንዱ የሆነው ኢራናዊው አርሰላን
የምስሉ መግለጫ,አርሳላን ለስኳር ህመሙ መድሃኒት ማግኘት አለመቻሉን ገልጿል

አስደንጋጭ ሁኔታዎች

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስቱም ስደተኞች በዳሪየን መጠለያ ያለው ሁኔታ በጣም አስፈሪ መሆኑን የገለፁ ሲሆን፣ በቂ ምግብ አለመኖሩንም ተናግረዋል።

“የስኳር በሽተኛ ብሆንም መድሃኒቶቼን አልሰጡኝም። በደሜ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን በጣም ከፍ ቢልም ማንም የረዳኝ አልነበረም። እንደ ወንጀለኛ፣ ነፍሰ ገዳይ ይቆጥሩኝ ነበር” ሲል ኢራናዊው አርሳላን ተናግሯል።

“የሰጡን ምግብ፣ ምግብ አይመስልም። ጣቢያው ከመቆሸሹ የተነሳ በየቦታው ሻጋታ እና ጀርሞች ነበሩ። በአጠቃላይ ሰብዓዊነታችንን በጠበቀ መልኩ አልያዙንም” ሲል አክሏል።

አንድ ጠባቂ መጸዳጃ ቤት ድረስ ያለማቋረጥ እንደሚከታታላቸው ሆህ ተናግሯል።

የፓናማ መንግሥት በበኩሉ በማዕከሉ የሚገኙትን ስደተኞችን የመንከባከብ ኃላፊነት ያለባቸው ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ናቸው።

የአይኦኤም ቃል አቀባይ ግን ድርጅቱ በስፍራው ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌለው የካቲት 20 ቀን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አርቴምስ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ከሆነ የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ወደ ሳን ቪሼንቴ ከቀናት በኋላም አልደረሱም።

የሂውማን ራይትስ ዎች የአሜሪካ ዳይሬክተር በበኩላቸው “ስደተኞቹ የተያዙት በቂ ባልሆነ ሁኔታ፣ መድረሻቸውን ሳያውቁ ወይም መሰረታዊ መብቶቻቸውን መጠቀም ሳይችሉ ነው።”

አርቴምስ እና ሌሎችም ወደ ፓናማ ሲቲ ተመልሰዋል
የምስሉ መግለጫ,ስደተኞቹን ፓናማ ሲቲ መናኃሪያ አድርሰው ለቀዋቸዋል

ዕቅድ መቀየር

የፓናማ መንግሥት በአገሪቱ ለ30 ቀናት የመቆየት ፍቃድ ሰጥቶ ለመልቀቅ ማቀዱን ይፋ ባደረገበት ወቅት ስደተኞቹ በመጠለያው ውስጥ ለሁለት ሳምንታት ቆይተዋል።

የፓናማ ኢሚግሬሽን አውቶቡሶች ፓናማ ሲቲ ወደሚገኘው አልብሩክ አውቶቡስ መናኸሪያ አጓጉዘዋቸው እንዲለቀቁ ተደረገ።

አርቴምስ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ፓናማ ሲቲ ከደረሱ በኋላ በመፈታታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ነገር ግን ምን እንደሚደርስባቸው ስለማያውቁ መጨነቃቸውን ገልጸዋል።

“ወደ አገራችን መመለስ አንችልም። ሌላ አገር ማግኘት አንችልም። ምን እንደሚፈጠር አናውቅም” ሲል ሆህም ተስማምቷል።

ገንዘብ እና የሚያውቁት ሰው ስለሌላቸው እና ስፓኒሽ መናገር ባለመቻላቸው ሁኔታው ይበልጥ ውስብስብ ሆኗል።

ቢቢሲ ባነጋገራቸው ወቅት ስደተኞቹ በፓናማ ሲቲ ሆቴል ውስጥ ነበሩ።

“ማን እንደከፈለልን አላውቅም። ዛሬ ማታ እዚህ ሆቴል እንደምናርፍ ነግረውናል። ነገ የት እንደምንወድቅ አናውቅም” ሲል ሆህ ተናግሯል።

“በፓናማ ሲቲ በአውቶቡስ መናሀሪያ አድርሰው እንደተተዉ ደርሰንበታል” ሲሉ ጎበርተስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስደተኞቹ ወደ ፓናማ ሲቲ ሲመለሱ
የምስሉ መግለጫ,ስደተኞቹ ወደ ፓናማ ሲቲ ሲመለሱ

የፓናማ ፕሬዝዳንት ሆሴ ራውል ሙሊኖ ከአሜሪካ ጋር በነበራቸው ስምምነት ፓናማ የስደተኞች “መሸጋገሪያ” አገር እንደምትሆን ቢስማሙም ለማስተናገድ ግን አሰልተስማሙም ነበር።

አሁን ዕቅዶቹ ተቀይረዋል። ቀጥሎ የሚሆነውን ነገር የሚወስኑት የፓናማ ባለስልጣናት ናቸው።

ጎበርተስ እንዳሉት ከሆነ “ምንም ያህል ከአሜሪካ መባረራቸው ሕገወጥ ሊሆን ቢችልም” የፓናማ መንግሥት ወደዚያ ለተላኩት የሦስተኛ አገር ዜጎች አሁን ኃላፊነት አለበት።

ቢቢሲ ሙንዶ የስደተኞቹን መብት ለመጠበቅ ምን አይነት እርምጃ እንደተወሰደ ለመጠየቅ የፓናማ የደህንነት ሚኒስቴር እና የብሔራዊ የስደተኞች አገልግሎትን ጠይቆ ምላሽ አላገኘም።

 የፌይ አልጌሪያ ጂም
የምስሉ መግለጫ,ጂሙ ለስደተኞች እንደመጠለያ ጣቢያ በማልገል ላይ ይገኛል

በጂም ውስጥ ማደር

ስደተኞቹ ወደ ፓናማ ሲቲ ከተመለሱ ጀምሮ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ እያገኙ ነበር።

አብዛኛዎቹ የሚኖሩት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ባቋቋመችው ፌይ አልጌሪያ ስር በሚተዳደር ጂም ውስጥ ነው። ሌሎች ደግሞ በእንክብካቤ መስጫ ቤቶች ውስጥ ናቸው።

ኤልያስ ኮርኔዮ በተቋሙ የስደተኞች እርዳታ አስተባባሪ ነው።

16 ወንዶች እና 35 ሴቶች አሁንም እነሱ ዘንድ እንዳሉ ተናግሯል። ሌሎች ደግሞ በራሳቸው ለመኖር ወጥተዋል።

አንዳንዶች በፓናማ ለመቆየት ወስነዋል። የተቀሩት ቀጥሎ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እየወሰኑ ነው።

መጠለያውን ለቅቆ የወጣ አንድ የአፍሪካዊ ቤተሰብ አባላት ወደ አሜሪካ ለመመለስ እንደሚሞክሩ እንደነገራቸው ኮርኔዮ ገልጿል።

ስደተኞቹ እንዲቆዩ የተፈቀደላቸው 30 ቀናት ሲጠናቀቅ ምን እንደሚገጥማቸው ወይም ፈቃዳቸውን ለማራዘም ምን ማድረግ እንዳለባቸው እስካሁን ግልጽ አይደለም።

ከአሜሪካ የተባረሩ አዲስ ስደተኞች ወደ አገሪቱ ይገቡ አይግቡ የታወቀ ነገር የለም።

በየካቲት ወር ሁለት መቶ ስደተኞች ከአሜሪካ ወደ ኮስታሪካ (የፓናማ ጎረቤት አገር) ተባርረዋል። አብዛኛዎቹም ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ነው የገጠማቸው።

ፓናማ ውስጥ ከአንድ ወር ተኩል በላይ ከቆዩ በኋላ አርቴምስ፣ አርሳላን እና ሆህ ተመሳሳይ ጥያቄ ያነሳሉ”ነጻነት እና የመኖሪያ ቦታ። ይህ ለእኛ በቂ ነው” ይላሉ።

*ለደህንቱ ሲል ስሙ እንዲቀየር ተደርጓል