Sintayehu Chekol  

የፖሊስ መለዮ ባያችሁ ቁጥር ስለኔ የምትሳቀቁ ልጆቼ …የመጨረሻውን ወሰንኩ!

በዘመናችሁ ሁሉ ስቃይ ያሸከምኳችሁ የፖሊስ መለዮ ባያችሁ ቁጥር ስለኔ የምትሳቀቁ ልጆቼ …አሁንስ ተስፋው ማነው? እንደምትሉ አውቃለሁ።

ግዴለም ተስፋዬ እግዚያብሔር ነው። ከብዙ ወጥቻለሁ ነገም ከኔ ጋር ነው! አታስቡ። በተኛችሁበት ጥያችሁ በመሄዴ ብታዝኑም ክፉ አባት ግን አይደለሁም ታውቃላችሁ።

በናተ እድሜ በአንድ የታሪክ ምዕራፍ የተፈጠረ አረመኔ ዘረፈጂ ሃይል የራሱን ልጅን አቅፎ እየኖረ የናተን አባት ግን በሚችለው ሁሉ ተበቀለው በመጨረሻም እናተን ጥዬ እንድወጣ አደረገ። ይኽ አልፋና ኦሜጋ አይደለም በህይወታችሁ ተስፋ እንዳትቆርጡ በፍጹም በችግር ውስጥ መልካም ነገር አለና። በርቱ!

ለወዳጆቼ በሙሉ በጥሩም በመጥፎ ጊዜዎች ስለሰጣችሁን ተስፋ አመሰግናለሁ።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ የወጣትነት እድሜ ከ25 አመታት የልጅነት ትግል ጀምሮ ቀላል አመታትን አላለፍንም።

ትግላችን ይዞት ከመጣው ከብዙ ውጣውረድ በኋላ በውጤት ነፃነት ሳይሆን ሀገር ጥሎ መሰደድ ብቸኛ ምርጫ ሆኖ ተሰድጃለሁ።

በረጅም የትግል ታሪክ ግለ ህይወቴ ወደፊት በጽሁፍ በቃል ለማስፈር እገደዳለሁ የሰው ልጅ መቀበል የሚችለውን መራር ዋጋ በመቀበል ተምሬበታለሁ።

እርግጥ ነው ቦታዬ መሰደድ ባይሆን እመርጥ ነበር ምርጫዬ ይኽ እንዳልሆነ ቢገባኝም እያዘንኩ የወሰንኩት የታሪክ ኩነት ሆኗል። ይኽ አዲስ ነገር ሌላ ምዕራፍ ነው።

ባሳለፍነው በመራራ ትግላችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ሁሉ ከጎኔ የቆማችሁ ወገኖቼ እህት ወንድሞቼ በፈጣሪ ስም አመሰግናለሁ።

የነገ ታሪካችን አካል ናችሁ። ክብር ይስጥልኝ።

ዛሬም በፈተና ውስጥ ብሆንም ከየትኛውም ጊዜ በላይ ትብብራችሁን እሻለሁ። ይኽ የድካሜ ውጤት ፍሬ ማሳያ ነውና። የትግላችን እዳ ነውና።

ከትላንቱ ስርዓት በከፋ ሁኔታ ባለፉት ሰባት አመታት ያሳለፍነው ከባድ ነው ምናልባት በወደፊቱ ትውልድ መማሪያ ቁጭት የሚፈጥር የጥላቻ ጥግ በቀል ከኔ ውጭ ይኽን ያህል ነውረኛ ድርጊት የተፈጸመበት አላውቅም። አንድ ሰውን በዚህ ደረጃ ማሳደድ ምክንያቱም አይገባኝም።

ለአብነት

1ኛ ይኽ አገዛዝ ወደስልጣን ከመጣ ወዲህ በአምስት ክልል ከተሞች ከ30 በላይ የእስር ቀጠናዎች… ሪከርድ ሆኗል።

2ኛ በትንሹ 21 የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ከፍቶብኛል።

3ኛ ዐቃቢ ህግ በ4 መደበኛ ክስ ፍርድ ቤት ገትሮኛል።

4ኛ ኮሽ ባለቁጥር የ3 አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀጥተኛ የእስር ትህዛዝ ተፈጻሚ ተደርጓል።

5ኛ ከ350 ሺህ በላይ የዋስት ገንዘብ ተከፍሏል።

6ኛ በተለምዶ የቅጣት ቦታ የሚባል 3 የጨለማ ክፍሎች ለወራት አቆይቶኛል።

በአጠቃላይ በሰባት አመት የስልጣን ዘመን ውስጥ አራት አመት(4) ለነጋሪ በማይመች ዋጋ አስከፈሎናል።

የሰኔ 16 እርግማን የመጨረሻ ውጤት ህወሓትን የሚናፍቅ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ሙሉ ቤተሰብ በትኜ ከሀገር እንድወጣ ምክንያት ሆኗል። እንደመሸ አይቀርም ነገን ተስፋ አደርጋለሁ።

ፈጣሪ የሚወደውን ይፈትናል ለወዳጆቼ በድጋሚ አመሰግናለሁ። ልጆቼን አደራ!

May be an image of 1 person, beard and eyeglasses