
2 ሚያዚያ 2025
በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ “አተት በሚመስል በሽታ” የተያዙ ሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ተወካይ ለቢቢሲ ተናገሩ።
በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጃዊ ወረዳ ከሰኞ መጋቢት 22/2017 ዓ.ም. ጀምሮ በተከሰተ “አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት” የሁለት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ 52 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ተይዘው ወደ ሆስፒታል መምጣታቸውን የጃዊ መጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የጃዊ መጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል ባልደረባ በበሽታው ተይዘው ወደ ሆስፒታላቸው ከመጡ ሰዎች መካከል “በአሳሳቢ ሁኔታ የሚገኙ አሉ” ያሉ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ “በኦአርኤስ ማገገም ችለዋል” ብለዋል።
የጃዊ ወረዳ የጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ተወካይ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ወሰን ትዕዛዙ በበኩላቸው መጋቢት 22 2017 ዓ.ም. ሰኞ ዕለት፣ ብሔራዊ ፀበል ከሚባል አካባቢ 20 የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው ተይዘው ወደ ጤና ጣብያ መምጣታቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ጃዊ ወረዳ ኮሙኑኬሽን በፌስቡክ ገጹ ላይ “ወረርሽኙ በወረዳው የተከሰተው ከባህዳር አንዳሳ ፀበል ወደ ወረዳው በመጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች” ነው ሲል ገልጿል።
ሰኞ ዕለት ጃዊ ሆስፒታል እንደደረሱ የሞቱ ሁለት ሰዎች መኖራቸውንም አቶ ወሰን አረጋግጠዋል።
የሞቱትን ሰዎች በተመለከተ ቢቢሲ የጠየቃቸው የሆስፒታል ምንጭ ሲያስረዱ ሰዎቹ በባጃጅ ከመጡ በኋላ ምን እንደገጠማቸው ቤተሰቦቻቸው ሲጠየቁ የሚያሳዩት ምልክት “የአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት እንደነበር” ተናግረዋል።
“በባጃጅ ነው የመጡት። ከባጀጅ ወርደው ሲታዩ ሕይወታቸው አልፏል” ሲሉም አክለዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጃዊ ወረዳ ኮሙኑኬሽን በበኩሉ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ “የሕክምና ቡድኑ 8 ሰዎችን እዛው ፀበል ቦታ ላይ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ” እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ወረርሽኙ በተከሰተበት ብሔራዊ ጸበል አካባቢ የጸጥታ ችግር መኖሩን የተናገሩት አቶ ወሰን፣ እስካሁን ድረስ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ኃላፊው አክለውም ከወረዳው ቤተ ክህነት ጋር በመሆን አገልግሎት መስጠት እንዲያቆም ደብዳቤ መጻፋቸውን ገልጸዋል።
የወረዳው ጤና ጽሕፈት ቤት ተወካይም ሆኑ የጃዊ መጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል ባልደረባ የሕሙማኑ ቁጥር ከዚህ ይጨምራል የሚል ስጋት እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
- አተት እና ኮሌራ ምን እና ምን ናቸው?5 መስከረም 2018
- ኮሌራን የሚቆጣጠር ኮምፕዩተር ተሰራ28 ነሐሴ 2018
- የአእምሮ ዕድገት መዛባት (ኦቲዝም) ያለባቸው መኪና እንዲያሽከረክሩ የሚረዳ ጥናት ለኳታር ያቀረቡት ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ2 ሚያዚያ 2025
በበሽታው የተያዙት ሰዎች የሚያሳዩት ምልክት “የአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት ነው” ያሉት አቶ ወሰን፣ “ናሙና ተወስዶ አልተረጋገጠም እንጂ የሚመጡት ሕሙማን በሙሉ የሚያሳዩት ምልክት ተመሳሳይ ነው” ብለዋል።
የአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን ቦታው ድረስ በመገኘት የሕክምና አገልግሎት እና ለኅብረተሰቡ ትምህርት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ኃላፊው አክለውም የፈንድቃ ከተማ እና የጃዊ ከተማ አስተዳደር በጋራ በመሆን ማቆያ ለሕሙማን በመሰራት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
አቶ ወሰን ተጨማሪ ለሕክምና አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ከዞኑ መጠየቃቸውን ገልጸው፣ በትናንትናው ዕለት “የተከሰተው ኮሌራ መሆን አለመሆኑን ለመለየት ናሙና ወደ ክልል ተልኳል” ብለዋል።
“ምልክቱ ኮሌራ ነው” ያሉት አቶ ወሰን በትክክል የበሽታውን ምንነት ለመለየት የናሙናውን ውጤት እየተጠባበቁ መሆን ተናግረዋል።
በአካባቢው የተከሰተው ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል የሚል ስጋት መኖሩን አቶ ወሰን ጨምረው ተናግረዋል።
የጃዊ መጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል ባልደረባ በአቶ ወሰን ሃሳብ የሚስማሙ ሲሆን፣ “ቶሎ ይቆማል” የሚል ግምት የለንም ብለዋል።
የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ በተለያዩ በጥቃቅን በዓይን በማይታዩ ተዋህሲያን አማካኝነት የሚከሰት በሽታ ሲሆን ከንጽህና መጓደል በተለይም በተህዋሲያን በተበከሉ ምግቦች፣ የመጠጥ ውሃ እና በሌሎች መተላለፊያ መንገዶች ከሰው ወደ ሰው በከፍተኛ ፍጥነት የሚተላለፍ ነው።
በአተት በሽታ የተያዘ ሰው በተደጋጋሚ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት የሚኖረው ሲሆን በዚህም የተነሳ የሰውነት ፈሳሽና ጠቃሚ የሆኑትን ንጥረ ነገሮች መጠን ይዛባል።
