
ከ 5 ሰአት በፊት
ለሳምንታት ከዘለቀ ከባድ የከተማ ውጊያ በኋላ የሱዳን መዲና ካርቱም ጸጥታ ወርሷታል።
ቢቢሲ ወደ ከተማዋ የገባው የሱዳን ጦር ካርቱምን ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) መልሶ ከተቆጣጠረ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
በአንድ ወቅት የሱዳን መንግሥት መቀመጫ እና የንግድ ማዕከል የነበረችው ካርቱም አሁን ባዶ ሆናለች።
በጦር ሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት ከሁለት ዓመት በፊት ከተነሳው የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ወደ ዋና ከተማዋን መመለስ ለጦሩ አዲስ ምዕራፍ ነበር።
ነዋሪዎቿ የጦርነቱን ማብቃቱን ቢመኙም ግጭቱ ወደ የትኛው አቅጣጫ እንደሚያመራ ግልጽ አይደለም ።
ቢቢሲ በመጀመሪያ ያቀናው ጦርነቱ እንደተጀመረ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ታጣቂዎች ስር ወደ ወደቀው የፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት።
ለአርኤስኤፍ ተዋጊዎች አስፈላጊ የጦር ማዕከል ነበር።
ወለሎቹ በቆሻሻ እና በተሰባበረ መስታዎት ተሸፍነዋል።
በአንድ ወቅት ለኦፊሴላዊ ተግባራት የሚያገለግሉ ወንበሮች በአቧራ ተሸፍነዋል። ጥቂት ሥዕሎች አሁንም በግድግዳዎች ላይ እንደተሰቀሉ ናቸው። የሚያማምሩ የመብራት ጌጦች ጣሪያው ላይ ተንጠልጥለዋል።
ሌላው ነገር በሙሉ ተዘርፏል። የኤሌክትሪክ ሽቦዎች ጭምር ከግድግዳው ውስጥ ተነቅለው ተወስደዋል።

በጣም የከፋ ጉዳት የደረሰው በሕንጻው የፊት ለፊት ክፍል ላይ ነው። ጦሩ ቤተ መንግሥቱን ከተቆጣጠረ በኋላ በአርኤስኤፍ ሰው አልባ አውሮፕላን በመመታቱ ነበር ተጎዳው።
ዋናው መግቢያው ተበላሽቷል፤ የደረቀ ደም አሁንም በደረጃው ላይ ይታያል፣ መስኮቶቹ ተሰባብረው በቀላሉ የአባይ ወንዝን ለመመልከት የተከፈቱ መስለዋል።
“በሪፐብሊካን ቤተ መንግሥት ውስጥ በመሆኔ በጣም ተደስቻለሁ” ሲል አንድ ሰው ነገረን።
“እዚህ ቦታ ስገባ የመጀመሪያዬ ነው። ይህንን ቦታ [እንደ ሱዳኖች ሁሉ] ጠብቄአለሁ። ነጻ እንዲሆን እፈልግ ነበር። ይህ ለእኛ የክብር ምልክት ነው።”
ለሠራዊቱ አስፈላጊ የሚባል የኃይል ምልክት ነው።

የኢድ በአልን በማስመለከትም ወታደሮቹ እየዘፈኑ እና እየጨፈሩ ደስታቸው ገለፁ።
በአካባቢው የሚገኝ ሬስቶራንት ምግብ ጋበዛቸው። በዋና ከተማው የሚገኙ ብዙ ነዋሪዎችም ጀግኖች ሲሉ አወደሷቸው።
ድላቸው ግን ከፍተኛ ዋጋ ተከፍሎበታል።
በማዕከላዊ ካርቱም ያለው የውድመት ደረጃ ከፍተኛ ነው። የመንግሥት ሚኒስቴሮች መስርያ ቤቶች፣ ባንኮች እና ከፍተኛ የቢሮ ሕንጻዎች ተቃጥለዋል።
በዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያው ያለው አስፋልት የተሰባበሩ አውሮፕላኖች መቃብር መስሏል። የፓስፖርት መቀበያ እና የመግቢያ ክፍሎቹ በአቧራ ተሸፍነዋል።

የቢቢሲ ባልደረቦች በከተማዋ ለመንቀሳቀስ ያልፈነዱ ፈንጂዎችን ላለመርገጥ በጥንቃቄ እና በዝግታ በመኪና ተንቀሳቅሰዋል።
በአንድ መስቀለኛ መንገድ ላይ የአስከሬን ክምር ይታያል። ሁለት የራስ ቅሎችም በግልጽ ይታያሉ። ከመንገዱ 100 ሜትር ርቀት ላይም አንድ አስከሬን ጥቃት ከደረሰበት መኪና ፊት ለፊት ይታያል።
እአአ በ1908 ዓ.ም በብሪታኒያ የተገነባው የቅዱስ ማቲዎስ ካቴድራል አነስተኛ ቁጥር ላላቸው የአገሬው ክርስቲያኖች የአምልኮ ቦታ በመሆን ያገለግላል።
በሚያምር ሁኔታ የተቀባው የጣሪያው ቀለም ምንም አልሆነም።
በአንደኛው ግድግዳ ላይ ያለው ቀዳዳ የደረሰበትን ጉዳት ያሳያል። አንድ መስቀልም ወድቆ ይታያል።
ከሌሎች በከተማዋ ካሉ ሕንጻዎች ጋር ሲነጻጸር ግን በጣም የተሻለ ይመስላል።

ወለሉ ላይ ያለውን ፍርስራሽ ሲያጸዳ የነበረ አንድ ወታደር አብዛኛው ጉዳት የደረሰው በቤተክርስቲያኑ አካባቢ በተተኮሰው ጥይት ነው ብሏል።
“የፈጣሪን ቤት” ማንም የሚያፈርሰው የለም፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች ግን ሕንጻው ውስጥ በመጸዳዳት ለማርከስ ሞክረዋል ሲል አክሏል።
ልጁ በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን እንደተወለደ ገልጾ የማያቋርጥ ጦርነት በመሆኑ ምክንያት ወደ ቤቱ ሄዶ ልጁን የማየት ዕድል አለማግኘቱን ገልጿል።
አርኤስኤፍ የዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች የሚገኙባቸውን ቦታዎችም ተቆጣጥሮ ነበር።
ጦርነቱ ሲጀመር የተለያዩ አገሮችና ኩባንያዎች ሠራተኞቻቸውንን ለማስወጣት በስፋት ተንቀሳቅሰዋል።
በብሪታንያ ኤምባሲ መግቢያ ላይ የአርኤስኤፍ መፈክር ተቀርጿል።
ለጥይት የማይበገር የሕንጻው መስታወት በብዛት እንዳለ ቢሆንም ለመስበር የተደረጉ ሙከራዎችን የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች አሉበት።

ከኋላ ባለው የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ተሽከርካሪዎች ወድመው ቆመዋል።
ከመንገዱ ማዶ በሚገኝ በተሰባበረ እና ቆሻሻ በለበሰ ሕንጻ ላይ የዩናይትድ ኪንግደም ባንዲራ ተሰቅሏል።
ይህ በ70 ዓመታት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ሱዳን ያስተናገደችው የእርስ በርስ ጦርነት ነው።
ከሁሉም የከፋውም ይኼኛው ነው። ቀደም ሲል የነበሩት ጦርነቶች በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የተካሄዱ ነበሩ።
ይህኛው ግን የሱዳንን እምብርት ሰንጥቆ፣ መለያየትን እያፋፋመ አገሪቱ እንዳትከፋፈል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
ከጦርነቱ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ለኢድ በዓል ጥቂት ሰዎች ወደ ጎዳና ወጥተዋል።
ምንም እንኳን በሌላ ቦታ ጦርነቱ ቢቀጥልም፤ በካርቱም ላሉ ሰዎች ግን ከወዲሁ አብቅቷል።

Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ሠራዊቱ ጥቃት በመፈጸም የተከሰሰ ሲሆን ባለፉት ቀናት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጦርነቱን ሸሽተው እንደነበር ዘገባዎች ጠቁመዋል።
በካርቱም ግን የጨካኙን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን አገዛዝ በማብቃቱ ነዋሪዎች ደስታቸውን ገልጸዋል።
ስሜቱ አል-ጀራይፍ በሚባለው ሠፈርም ተስተጋብቷል።
እንግሊዘኛን ከቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ እንደተማረ የሚናገረው ኡስማን አልበሽር የተባለ ነዋሪ “እንደገና የተፈጠርኩ ሆኖ ይሰማኛል” ሲል ዓይኑ በደስታ እንባ ተሞልቶ የጦርነቱን አስቸጋሪነት በዝርዝር ጠቀሶ ተናግሯል።
ዱአ ታሪቅ የዲሞክራሲ አቀንቃኝ ስትሆን ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የዘለቀው እና እአአ በ2019 ወታደራዊ መሪ ኦማር አልበሽርን አምባገነናዊ አገዛዝ ያስወገደው እንቅስቃሴ አካል ነበረች።
አሁን ጎረቤቶቿ ከጦርነቱ እንዲያገግሙ በመርዳት ላይ ትኩረት አድርጋለች።
“በሁለት ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢድን እያከበርን ነው” ስትል ተናግራለች።
“እኔን ጨምሮ ሁሉም ሰው እየለበሰ ነው! እንደገና እንዴት መኖር እንዳለብኝ ለመማር በማሰብ በብዙ ስሜቶች ተጨናንቄአለሁ። ነጻነት ይሰማናል፤ ብርሃን ይሰማናል፤ አየሩም የተለየ ሽታ አለው።”
ታሪቅ በጦርነቱ ወቅት ምግብ በማለቁ ተቸግራ ነበር። በአማፂያኑ የተዘረፈችው ከተማ፣ በጦር ሠራዊቱ ምንም እንዳይገባ እና እንዳይወጣ ከመከበቧም በላይ እና የአሜሪካ ዕርዳታ በመቋረጡ ምግብ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር።
የምግብ እጥረት አሁንም ቢኖርም ግን ቢያንስ ተስፋ አለ።
ቃሲም አግራ የተባሉ አዛውንት ደግሞ “አስደናቂ ስሜት እየተሰማኝ ነው። ደህንነት ይሰማኛል። ቢርበኝም እንኳን ጥሩ ስሜት ይሰማኛል” ብለዋል።
“ታውቃለህ ሌላው ነገር አይረባም፤ ዋናው ነገር ነጻነት ነው።”
“እንደምታየው ሞባይል ይዤያለሁ” ሲሉ ኪሳቸው ወዳለው ስልክ አመለከቱ።
“ከሁለት ሳምንት በፊት ሞባይል መያዝ አይቻልም ነበር።”
በካርቱም የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ለቢቢሲ የሚናገሩት ይህንኑ ነው። ለተቀረው ዓለም ተንቀሳቃሽ ስልኮች የሕይወት አካል ሲሆኑ ለአርኤስኤፍ ተዋጊዎች ደግሞ ዋነኛ የስርቆት ዒላማ ነው።

ካርቱም እና ቀሪው የአገሪቷ ክፍል ማገገም ይችላሉ የሚል ተስፋ አግራ አላቸው።
“መንግሥት ባለሀብቶችን ያመጣል ብዬ አስባለሁ፤ አሜሪካውያን፣ ሳዑዲዎችን፣ ካናዳውያን፣ ቻይናውያን በማምጣት ይህችን አገር እንደገና እንደሚገነቡ አምናለሁ።”
ምንም እንኳን እንደዚህ አይነት ግዙፍ መልሶ ማልማት ቢቻልም፣ ካርቱም ባሕላዊ እና ሥነ-ሕንፃዊ ቅርጿን እንደጠበቀች መቀጠሏን መገመት ይከብዳል።
ብዙ ሴቶች አርኤስኤፍ ይዘርፈናል የሚል ስጋት ስለሌለባቸው ያለ ስጋት መተኛት እንደሚችሉ ያምናሉ።

ናጃዋ ኢብራሂም ደግሞ “ልጆቻችን ተሳቀዋል” ትላለች።
“እነሱን ለመርዳት የሥነ-አእምሮ ሐኪሞች ያስፈልጋቸዋል። እህቴ አስተማሪ ስለሆነች ከልጆች ጋር ለመሥራት ሞክራ ነበር። ግን በቂ አይደለም።”
ታሪቅ ስለጦርነቱ ተጽእኖ ጥያቄዎች አሏት። “ከተማዋ እንደገና ተደራሽ የምትሆነው፣ እንደገና የምትከፈተው መቼ ነው?” የሚል ጥያቄ።
“በተጨማሪም እንደ አክቲቪስት ያለኝ ጥያቄ ደግሞ ባለፉት አምስት ዓመታት ያገኘናቸው ነጻነቶች እና መብቶች ምን ይሆናሉ?” በማለት በሽር ከስልጣን ከተባረሩ በኋላ የነበረውን የሲቪል እና ወታደራዊ መንግሥት ወደ ሲቪል አገዛዝ ለመመለስ ሲሠራ የነበረውን ዓመታት በማጣቀስ ትጠይቃለች።
“ሲቪል ማኅበረሰብ፣ አክቲቪስቶች፣ የነጻነት ታጋዮች እንዴት ይሆናሉ? አሁን ስለወደፊታችን እርግጠኛ አይደለሁም።”
ስለሱዳን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ማንም እርግጠኛ አይደለም።
የ16 ዓመቷ ሃዋ አብዱልሻፊያ “ለዳርፉር ሕዝብ እንጸልያለን” ስትል የአርኤስኤፍ ጠንካራ ይዞታ ስለሆነው እና የሰብዓዊ ቀውሱ ስለከፋበት አካባቢ ትገልጻለች።
“ፈጣሪ ይጠብቃቸው!!”