የኢራን ወታደራዊ መቀመጫ

ከ 56 ደቂቃዎች በፊት

ኢራን ሚሳኤል ለማስቀመጥ ከምድር በታች የገነባቻቸውን ምሥጢራዊ ማቆያዎች በቅርቡ ይፋ አድርጋለች።

ከእስራኤልና አሜሪካ የሚቃጣ ጥቃትን ለመመከት እንደምትጠቀምባቸውም አስታውቃለች።

“ከዛሬ ጀምሮ በየሳምንቱ የሮኬት ምሥጢራዊ ማስቀመጫዎችን ይፋ ብናደርግ ከሁለት ዓመት በኋላ ነው የምንጨርሰው። ማቆያዎቹ ያን ያህል ብዙ ናቸው” ብላለች ኢራን።

አሜሪካ ባለፈው ሳምንት ቦምብ የጫኑ ስድስት ተጨማሪ የጦር አውሮፕላኖችን በኢራንና የመን አቅራቢያ ወደሚገኙ ወታደራዊ መቀመጫዎች ማስጠጋቷን አንድ የአገሪቱ ባለሥልጣን ለሮይተርስ ጠቁመዋል።

ኢራን ለዚህ በምላሹ “አሜሪካ በቀጠናው ያላት ወታደራዊ እንቅስቃሴ የመስታወት ቤት ውስጥ ተቀምጦ ሌሎች ላይ ድንጋይ የመወርወር ያህል ነው” ብላለች።

ኢራን ይህንን ወታደራዊ መቀመጫ በቦምብ ለማጋየት ዝታለች። ወታደራዊ መቀመጫው የሚገኘው በሕንድ ውቅያኖስ ዲዬጎ ጋርሲያ በሚባል አካባቢ ነው። ቦታውን ለሞሪሸስ መልሶ ለመስጠት ሒደት ተጀምሯል።

‘የሚሳኤል ከተሞች’ ምንድን ናቸው?

ኢራን እንዳለችው እነዚህ ‘የሚሳኤል ከተሞች’ ሚሳኤል የሚዘጋጅባቸው ናቸው።

‘የሚሳኤል ከተሞች’ የሚለውን ቃል የተጠቀመው የኢራን ወታደራዊ ኃይል የሆነው የኢስላሚክ ሪፐብሊክ ዘብ ነው።

ከምድር በታች የተገነቡ ትልልቅ የሚሳኤል ማቆያ እንደሆኑ ተገልጿል። መጠነ ሰፊና በአገሪቱ ተራራማ አካባቢዎች በሚገኙ ሸለቆዎች መካከል የተገነቡ ናቸው።

ባለስቲክና ክሩዝ ሚሳኤል ለማከማቸትና ለመተኮስ ይውላሉ። ሰው አልባ አውሮፕላንና የአየር መቃወሚያ መሣሪያም ይገኝባቸዋል።

የኢራን ኮማንደሮች እንዳሉት እነዚህ ‘የሚሳኤል ከተሞች’ ስትራቴጂክ ናቸው።

“ሚሳኤል ለማምረትና ለማከማቸት ጥቅም ላይ ይውላሉ” ተብሏል።

እነዚህ ሚሳኤል የሚገኝባቸው ቦታዎች በግልጽ አይታወቁም። በይፍ ስለእነዚህ ቦታዎች ተነግሮም አያውቅም።

የኢራን ወታደራዊ ዘብ አየር ኃይል ኮማንደር የሆኑት ብርጋዴር ጀነራል አሚር አሊ ሀጂዝዳህ ከአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ አይአርአይቢ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ባለስቲክ ሚሳኤልና አጥፍቶ ጠፊ ሰው አልባ አውሮፕላን ክምችት ያለበትን ‘የሚሳኤል ከተማ’ በቪድዮ አሳይተዋል።

ቢቢሲ ይህ ቪድዮ ትክክለኛ መሆኑን በገለልተኛ ወገን አላጣራም።

ኢራን ለምን ስለ ‘ሚሳኤል ከተሞች’ አሁን መረጃ መስጠት ፈለገች? የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው።

ኢራን እንዳለችው እነዚህን መሣሪያዎች የምትጠቀመው “ኢራን ላይ ለሚቃጡ ጥቃቶች አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት” ነው።

“ኢራን በቀጠናው ካለ ወታደራዊ መቀመጫ ወይም ሌላ ኢራን ላይ በሚደርስ ሚሳኤል ጥቃት ከተፈጸመባት፣ የአሜሪካን ወታደሮችና የእንግሊዝን ወታደሮች ዒላማ በማድረግ መካከል ልዩነት የለም” ብላለች ኢራን።

ባለፉት 10 ዓመታት የኢራን ወታደራዊ ዘብ ከምድር በታች የተገነቡ ማቆያዎች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሚሳኤሎች፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖችና መከላከያ መሣሪያዎች አልፎ አልፎ ያሳይ ነበር።

ለአሜሪካ እና እስራኤል ምን ይጠቅማል?

ኢራን ምን ማድረግ እንደምትችል በማሳየት አሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት እንዳይሰነዝሩ ማድረግ ነው ዓላማዋ።

ከኢራን የተለቀቁት ምሥሎች ከህባር ሸካን፣ ሀጅ ቃሲም፣ ኢማድ፣ ሰጂል፣ ቃዳር ኤች እና ፓቬህ የተባሉ ሚሳኤሎችን ያሳያሉ።

ኢራን እስከ 2,000 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ አገሮችን ዒላማ ማድረግ እንደምትችል አስታውቃለች።

ኢማድ ባለስቲክ ሚሳኤል ኢራን በ2024 በእስራኤል ላይ ጥቃት ስትሰነዝር ከተጠቀመችባቸው መሣሪያዎች አንዱ ነው።

በማዕከላዊ እስራኤል ናቫቲም የአየር ኃይል መቀመጫ ላይ ጉዳት አድርሷል።

ከኢራን እስከ እስራኤል ያለው ርቀት 1,000 ኪሎሜትር ይደርሳል። ይህም ኢራቅ፣ ሶርያ እና ጆርዳንን አሻግሮ ነው።

እስራኤል በኢራን ከተቃጣው ጥቃት 99% መክሸፉን ገልጻለች።

ኢራን ለሁለተኛ ጊዜ ያደረሰችው ጥቃት እምብዛም ጉዳት አላደረሰም።

የኢራን ሚሳኤሎች የሚጓዙበትን ርቀትና ውጤታማነታቸውን በተመለከተ ጥርጣሬዎች አሉ።

ዲዬጎ ጋርሲያ የተባለውን የአሜሪካ ወታደራዊ መቀመጫ ኢራን ለመምታት መዛቷን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባም ነው።

የአሜሪካና ዩኬ የጋራ ወታደራዊ መቀመጫ የተገነባው በ1970ዎቹ ነበር። ከኢራን 3,800 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

ኢራን ሻሒድ 136ቢ ሰው አልባ አውሮፕላኖቿ 4,000 ኪሎሜትር እንደሚጓዙ ገልጻለች። ይሄ ግን አልተረጋገጠም።

ኢራን ከ2,000 ኪሎሜትር በላይ የሚምዘገዘግ ሚሳኤል አሁን ላይ ያላት አይመስልም።

አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ መሣሪያ መከላከያዎች አሏት። በቅርቡ በቀጣናው ሁለት የጦር አውሮፕላን ተሸካሚዎችም ታሰማራለች።

በዲዬጎ ጋርሲያ ቢ-2 ቦምብ ጣይ መሣሪያ ይገኛል። አሜሪካ በየመን የሁቲ አማጺያን ላይ ጥቃት ለመፈጸም ተጠቅማበታለች።

የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሻን ፓርናል “ኢራን ወይም አጋሮቿ አሜሪካ በቀጣናው ያላትን ፍላጎት የሚገዳደሩ ከሆነ ሕዝባችንን ለመከላከል እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል።

ኢራን ለምን ‘የሚሳኤል ከተሞችን’ ይፋ አደረገች?

በኢራን፣በአሜሪካ እና በእስራኤል መካከል ያለው ውጥረት ከፍተኛ በሆነበት ወቅት ነው ኢራን ‘የሚሳኤል ከተሞች’ ምሥጢርን ይፋ ያደረገችው።

ሦስቱ አገራት በተለይም ደግሞ ኢራን ከምትደግፋቸው የሁቲ አማጺያን ጋር በተያያዘ ውጥረታቸው አይሏል።

የኢራን የኒውክሌር ግንባታ ድርድር እንዳለ ሆኖ፣ እስራኤል በኢራን የሚደገፈውንና በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰውን ሔዝቦ ላይ ለማዳከም ጥቃት እየሰነዘረች ነው።

ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝሩ ከመዛታቸው ባሻገር፣ ኢራን በኒውክሌር ግንባታ ዙርያ ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ካልደረሰች የእጅ አዙር ቀረጥ እንደሚጥሉም አስታውቀዋል።

የኢራን ወታደራዊ መቀመጫ

ኢራን እና እስራኤል አምና ወታደራዊ ትንኮሳ ውስጥ መግባታቸው አይዘነጋም።

ኢራን አዲስ የሚሳኤል ማቆያ ቦታዎችን በይፋ ማሳየቷ ልትወስድ የምትችለውን የአጸፋ እርምጃ የሚጠቁም ይመስላል።

ኢራን ሦስተኛ ዙር ጥቃት በእስራኤል ላይ እንደምታደርስ አስጠንቅቃለች። ሆኖም ግን ጥቃት እንዳታደርስ ሕዝቡ ጫና እያሳደረ ነው።

ኢራን ምን ያህል በጥቃቱ ትቀጥላለች የሚለው ጥያቄ ውስጥ ስለሆነ ሌላ ጥቃት ባይሰነዘር ሲሉ ያሳስባሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ የእስራኤል ጥቃት የኢራንን የሚሳኤል አቅም ማዳከሙም ይጠቀሳል።

የኢራን መንግሥት የሚሳኤል ማቆያዎቹን በማሳየት ሕዝቡ እንዲተማመንበት ማድረግ ይፈልጋል።

ጠንካራ መንግሥት እንደሆነና አሜሪካን እንደሚቋቋም ለማሳየትም ይሻል።

‘የሚሳኤል ከተሞች’ ከምድር በታች የሚገነቡት ከስለላ መረብ ለመራቅ ነው። የአየር ጥቃት ቢሰነዘር በቀላሉ ጉዳትም አይደርስባቸውም።

ኢራን፣ ለአሜሪካ እና ለእስራኤል ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ምንም እንኳን በወታደራዊ መቀመጫዎች ጥቃት ቢሰነዘርባትም የአጸፋ ምላሽ መስጠት ትፈልጋለች።

እነዚህ ከምድር በታች የተገነቡ ወታደራዊ መቀመጫዎች ሚሳኤል ከማይታወቅ ቦታ እንዲወነጨፍ ያስችላሉ። ጠላት የኢራንን አቅም ለመገመት የሚያደርገውን ጥረትም ውዥንብር ውስጥ ይከታሉ።