
3 ሚያዚያ 2025
የሃንጋሪ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ለመውጣት መወሰኑን አስታወቀ።
በሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ገርግሊ ጉልያስ፤ ይህንን ውሳኔ ይፋ ያደረጉት በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ የወጣባቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለመንግሥታዊ ጉብኝት ወደ አገሪቱ ከገቡ ከሰዓታት በኋላ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ገርግሊ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት አጭር ጽሑፍ፤ “ሃንጋሪ ከዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ትወጣለች” ብለዋል።
“መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ እና ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎችን በመከተል ሐሙስ ዕለት [ከፍርድ ቤቱ አባልነት] የመውጣት ሂደቱን ይጀምራል” ሲሉ የአገሪቱ መንግሥትን ውሳኔ አስታውቀዋል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦርባን፤ለኔታንያሁ የጉብኝት ግብዣ ያቀረቡት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሕዳር ወር ላይ ማዘዣ እንደወጣባቸው ነበር።
ኦርባን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በአገሪቱ ውስጥ “ምንም ተፈጻሚነት” እንደማይኖረው ተናግረው ነበር።
የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ዳኞች ሕዳር ላይ የእስር ማዘዣ ያወጡት ኔታንያሁ በጋዛ ጦርነት ተፈጽመዋል ለተባሉ የጦርነት ወንጀሎች እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች “የወንጀል ኃላፊነት” እንዳለባቸው ለማመን የሚያስችሉ “ምክንያታዊ መሠረቶች” መኖራቸውን በመግለጽ ነው።
ኔታንያሁ፤ ይህንን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ “ፀረ-ሴማዊነት” ሲሉ ተቃውመውታል።
ሃንጋሪ ከ125ቱ የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት መስራች አባል አገራት አንዷ ነች።
አሜሪካ፣ሩስያ፣ ቻይና እና እስራኤል እንዲሁም ሌሎች አገራት ፍርድ ቤቱ በግዛታቸው ውስጥ ስልጣን እንዲኖረው እውቅና አልሰጡም።
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የተመሰረተበት የሮም ስምምነት አባል በሆኑ ግዛቶች ውስጥ በሚፈጸሙ የዘር ማጥፋት፣ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች እንዲሁም የጦርነት ወንጀሎች የተወነጀሉ አካላትን የመክሰስ ስልጣን አለው።
እስራኤል ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በግዛቷ ውስጥ ስልጣን አትቀበልም።
ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ እ.አ.አ በ2021 ባሳለፈው ውሳኔ በወረራ ስር ባለው ዌስት ባንክ፣ ምሥራቅ እየሩሳሌም እና ጋዛ ስልጣን እንዳለው ገልጿል።
ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ ፍልስጤማውያን በአባልነት በመቀበላቸው ነው።
- የተዘጉ ዳቦ ቤቶች እና በፈረቃ የሚከፋፈሉ የሕመም ማስታገሻዎች – የእስራኤል እርዳታ እገዳ በጋዛ3 ሚያዚያ 2025
- ፀረ – ሴማዊነት ምንድን ነው? ፀረ – ጽዮናዊነትስ?23 ጥቅምት 2023
- ከኳታር ገንዘብ ተቀብለዋል የተባሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ረዳቶች ታሰሩ2 ሚያዚያ 2025
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ሃንጋሪ ከፍርድ ቤቱ የአባልት ስምምነት ለመውጣት መወሰኗን በጽሑፍ ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ ማሳወቅ ይጠበቅባታል።
ፍርድ ቤቱን ባቋቋመው የሮም ስምምነት አንቀጽ 127 መሰረት ከአባልነት የመውጣት ጥያቄ ተፈጻሚ የሚሆነው ከአንድ ዓመት በኋላ ነው።
በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ማዘዣው የወጣ በመሆኑ በተለመደው አሰራር መሰረት የሃንጋሪ ባለስልጣናት ኔታንያሁን አስረው በሄግ ለሚገኘው ፍርድ ቤት መስጠት ነበረባቸው።
ይኹን እንጂ አባል አገራት ሁልጊዜም ፍርድ ቤቱ የሚያስተላልፋቸውን ትዕዛዞች ላይፈጽሙ ይችላሉ።
የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔውን እንደማይቀበለው ያስታወቀ ሲሆን ኔትያናሁም ከሕዳሩ እስር ማዘዣ በኋላ አገሪቱን ጎብኝተዋል።
ኔታንያሁ ዛሬ በሃንጋሪ ያደረጉት ጉብኝት ከዚህ ትዕዛዝ ወዲህ ወደ አውሮፓ ያደረጉት የመጀመሪያው ጉዞ ነው።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃንጋሪ ሲደርሱ የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ክሪስቶፍ ሳላይ ቦብሮቭኔትስኪ በቡዳፔስት አየር ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአውሮፕላኑ ሲወርዱ ወታደሮች በቀይ ምንጣፍ ዙሪያ ተደርድረው ነበር።
ኔታንያሁ፤ከወታደራዊው አቀባበል በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦርኣብንን ለማግኘት ወደ ወታደራዊው ቤተ መንግሥት አምርተዋል።
የዓለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት ኔታንያሁን እና የቀድሞውን መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንትን ለማሰር ያወጣውን ትዕዛዝ እና ክሱን በጽኑ የተቃወመችው እስራኤል፤ አቤቱታዋን አቅርባለች።
ሁለቱ ባለስልጣናት ፍርድ ቤቱ ያለውን ስልጣን እና የትዕዛዙን ቅቡልነት ተቃውመዋል።
የፍርድ ቤቱ ዳኞች ይህንን ውሳኔ ሲያሳልፉ እስራኤል እንደሞተ በምትገልጸው የሀማስ ወታደራዊ አዛዥ መሀመድ ዴኢፍ ላይ የእስር ትዕዛዝ አውጥተዋል።
ኔታንያሁ በሃንጋሪ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት እስራኤል ሀማስ ላይ ጫና ለማሳደር በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት ባጠናከረችበት እና አዲስ ወታደራዊ ኮሪደር እየመሰረተች ባለበት ወቅት ነው።
እስራኤል በፍልስጤም ግዛት ላይ በምትፈጽማቸው ጥቃቶች በርካቶች መገደላቸውም እየተዘገበ ነው።