የተቃጠለ ታንክ

ከ 8 ሰአት በፊት

የግዙፉ ማሕበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ወላጅ ኩባንያ ሜታ በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተዛመተው ጦርነት ተጫውቷል በተባለው ሚና ኬንያ ውስጥ መከሰስ እንደሚችል የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መወሰኑ ተገለጸ።

ለሁለት ዓመት በዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወደ ብሔር ብጥብጥ እና ግድያ የሚመሩ ይዘቶችን በማስተዋወቅ የተወነጀለው ሜታን ክስ የማየት የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን እንዳለው ብይን መሰጠቱን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ስትራቴጂክ ሊቲጌሽን ኃላፊ ማንዲ ሙዳሪክዋ ሐሙስ፣ መጋቢት 25/ 2017 ዓ.ም ገልጸዋል።

“የዛሬው ብያኔ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አስተዋጽኦ ያደረጉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል አዎንታዊ እርምጃ ነው። ለፍትህ መንገድ የሚከፍት እና ታላላቅ የቴክኖሎጂ መድረኮች ተጠያቂ የማይሆኑበት ጊዜ ያለፈበት መሆኑን የሚያሳይ ነው” ሲሉ መናገራቸው በዛሬው ዕለት አምነስቲ ባወጣው መግለጫ ሰፍሯል።

ፌስቡክ በትግራይ ጦርነት ወቅት በገጹ ጥላቻ የሚነዙ እና ግጭት የሚያነሳሱ መልዕክቶችን አሰራጭቷል በሚል የሁለት ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍል ክስ የተመሰረተበት ከሁለት ዓመታት በፊት ታህሳስ ወር ላይ ነበር።

የሜታ የህግ ባለሙያዎች ቡድን በበኩሉ ኩባንያው በአሜሪካ ውስጥ የተመዘገበ በመሆኑ በኬንያ ሊታይ አይገባም በሚል ከዚህ ቀደም ተከራክሮ ነበር።

በተጨማሪም ተፈጽመዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በኢትዮጵያ ስለተፈጸሙ በኬንያ ሊሰሙ አይገባም የሚል መከራከሪያ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፤ የኬንያው ፍርድ ቤት ክሱን ለማየትም ሆነ ለማጤን የዳኝነት ስልጣን አለኝ ብሏል።

ሜታን በኬንያ ከከሰሱት መካከል የትግራይ ተወላጅ የሆኑት አባቱ ፌስቡክ ላይ በተለጠፈ ጽሑፍ ምክንያት የተገደለበት አብርሃም ማዕረግ አንዱ ነው።

በባህርዳር ዩኒቨርስቲ መምህር የነበሩት አባቱ ፕሮፌሰር ማዕረግ አማረ በብሔራቸው ላይ ያነጣጠረ በፌስቡክ በወጣ ጽሁፍ ምክንያት በጥይት ተገድለዋል።

ይህ ጽሁፍ የፕሮፌሰር ማዕረግን ስም እና አድራሻ የያዘ እንዲሁም እንዲገደሉ ጥሪ ያደረገ ነበር።

አባትየው ከመገደላቸው በፊት አብርሃም እነዚህን ጽሁፎች እንዲነሱ ለፌስቡክ ሪፖርት ቢያደርግም የማህበራዊ ሚዲያው ልጥፉን ለማንሳት ፈቃደኛ እንዳልነበር ክሱ ያትታል።

ጥቃቱን የፈጸሙት ግለሰቦች በአካባቢው የሚተላለፉ ሰዎች ፕ/ር ማዕረግን እንዳይረዷቸው ስላስጠነቀቁ ማንም ሰው ሊያተርፋቸው አልሞከረም።ፕሮፌሰር ማዕረግ ከተተኮሰባቸው ከሰባት ሰዓታት በኋላጥቅምት 24/ 2014 ሕይወታቸው አልፏል።

ፌስቡክ ለአብርሃም ምላሽ የሰጠውሪፖርት ካደረገ ከሶስት ሳምንታት በኋላ፣ አባትየው ከተገደሉ ከስምንት ቀናት በኋላ ነበር።

“ፌስቡክ የጥላቻ ንግግሩን ቢያስቆም እና በገጹ የሚለጠፉ ጽሑፎችን በአግባቡ ቢያጣራ ኖሮ አባቴ አይሞትም ነበር” ሲል አብርሃም ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።

አብርሃም ለፍርድ ቤት በሰጠው ምስክርነት፣ የፌስቡክ አልጎሪዝም “ጥላቻ አዘልና ግጭት አነሳሽ” መልዕክቶች እንደሚያስተዋውቅ ተናግሯል። መሰል ይዘቶች የተጠቃሚዎችን ተሳትፎ ስለሚጨምሩ እንደማይወገዱም አክሏል።

ሌላኛው ከሳሽ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተመራማሪ የነበሩት አቶ ፍስሃ ተክሌ ናቸው። አቶ ፍስሃ በሁለት ዓመቱ ጦርነት ወቅት በኢትዮጵያ ይሰሩት በነበረው የሰብዓዊ መብት ስራዎች የበይነ መረብ ጥቃቶችን አስተናግደዋል።

አብርሃም ማዕረግ
የምስሉ መግለጫ,በፌስቡክ ጽሁፍ አባቱ የተገደለው አብርሃም ማዕረግ

በኬንያ ነዋሪነታቸውን ያደረጉት አቶ ፍስሃ በፌስቡክ በተሰራጩ ይዘቶች ምክንያት ለደህንነታቸው እንደፈሩ ገልጸው ነበር።

ከሁለቱ ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ካቲባ የተሰኘ የኬንያ የመብቶች ተሟጋች ተቋም ናቸው በሜታ ላይ ክሱን የመሰረቱት።

ከሳሾቹ በፌስቡክ ላይ ከተሰራጨው ጥላቻ ጋር በተያያዘ ለደረሰባቸው ጉዳት የሁለት ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላቸው እንዲሁም የፌስቡክ አልጎሪዝም ላይ ለውጥ እንዲደረግም ይሻሉ።

“በበርካታ አገራት ውስጥ በሚፈጸሙ የኩባንያዎች የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች የተጎዱ ማህበረሰቦች እና ግለሰቦች አብዛኛውን ፍትህን ለማግኘት ይቸገራሉ። በከፊል እንደ ሜታ ያሉ ኩባንያዎች የአገልግሎት ውላቸውን ተጠቅመው የፍርድ ቤቶችን የተደራሽነት ስልጣን በመገደብ በርካታ ተጎጂዎች እንዳይደርሷቸው ለማድረግ ስለሚሞክሩ ነው” ሲሉ ማንዲ ሙዳሪክዋ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሜታ በፌስቡክ ግጭት የሚያነሳሱ እና ጥላቻ የሚነዙ ጽሁፎች እንዲሰራጩ መድረክ በመሆን ደም አፋሳሹ ጦርነት እንዲቀጣጠል አስተዋጽኦ አድርጓል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

ክሱ፤ ፌስቡክ የመልዕክት ይዘትን በየመልኩ በሚፈርጀው አልጎሪዝሙ ግጭትን የሚያነሳሱ ልጥፎችን ተጠቃሚዎች እንዲያዩት ማስተዋቅን ጨምሮ የሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል ብሏል።

ከሳሾቹ ፌስቡክ እንዲወስዳቸው ከጠየቋቸው የማሻሻያ እርምጃዎች አንዱ፣ በጥላቻ ንግግርና በግጭት አነሳሽ ይዘቶች ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ካሳ የሚሆን 1.6 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እና ተጨማሪ 410 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ካሳ ደግሞ ፌስቡክ ስፖንሰር ባደረጋቸው ይዘቶች ለደረሱ ጉዳቶች የሚውል ነው።

ፌስቡክ አልጎሪዝሙ “ጥላቻ የሚነዙና አደገኛ ይዘቶችን” ከማሰራጨት እንዲቆጠብ እንዲደረግ እንዲሁም በአገር ውስጥ ቋንቋዎች የይዘት ቁጥጥር የሚያደርጉ ተጨማሪ ሠራተኞች እንዲቀጠሩም ክሱ ይጠይቃል።

ሜታ ከዚህ ቀደም የኬንያ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን እንደሌላቸው እና በተጨማሪም የኩባንያው የአገልግሎት ውል (ተርምስ ኦፍ ሰርቪስ) እንዲህ አይነት ጉዳዮችን የአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ብቻ እንዲያዩት የሚያደርግ ነው ብሏል።

ሊንዳ “ይህ ውሳኔ ማህበረሰቦች በዓለም ውስጥ የትም ቢሆኑ ፍትህን ማግኘት እንደሚችሉ ተስፋ ይሰጣል። ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ውጭ ያሉ ሃገራት ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ ትርፍ ማግኘት የሚቻልባቸው ገበያዎች አድርጎ ብቻ የመመልከት እሳቤ ሊቆም ይገባል” ብለዋል።

“እነዚህ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እና ከትርፍ ይልቅ ለሰብዓዊ መብቶች ቅድሚያ የሚሰጡበት ጊዜ ነው” ሲሉ አክለዋል።

አምነስቲ በሁለት አመቱ በነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሜታ ሚና እንደነበረው ‘Meta’s failures contributed to abuses against Tigrayan community during conflict in northern Ethiopia’ በሚል ርዕስ ጥቅምት 20/ 2016 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት አስነብቧል።

“የፌስቡክ አልጎሪዝም በትግራይ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ ትርክቶች እንዲዛመቱ ያስቻለ እንዲሁም ይዘቶችን የመቆጣጠሩ ስርዓት እንዲህ አይነት ጽሁፎችን ለመለየት እንዲሁም ምላሽ መስጠት እንደተሳነው” አምነስቲ ባደረገው ጥናት እንዳገኘው ገልጿል።

“እነዚህ ሁኔታዎች በመጨረሻም የትግራይ ተወላጅ የሆኑት የዩኒቨርስቲ መምህሩ ፕሮፌሰር ማዕረግ አማረ እንዲገደሉ አስተዋጽኦ አድርጓል” ሲል በሪፖርቱ አስፍሯል።