በእስራኤል ጥቃት የተፈጸመባቸው ግለሰቦች

ከ 4 ሰአት በፊት

እስራኤል ከሰሜን ጋዛ ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች መጠለያ ሆኖ በማገልገል በሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 27 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ዳር አል አርቃም በተሰኘው ትምህርት ቤት በተፈጸመው ጥቃት ከተገደሉት በተጨማሪ በርካቶች መቁሰላቸውን በሐማስ የሚተዳደረው የጤና ሚኒስቴር የአካባቢውን ሆስፒታል ዋቢ አድርጎ ጠቅሷል።

የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ ትምህርት ቤቱን ሳይጠቅስ የሐማስ የትዕዛዝ እና የቁጥጥር ማዕከልን መምታቱን ገልጿል።

የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ቀደም ብሎ እስራኤል በ24 ሰዓታት ውስጥ ባደረሰችው ጥቃት 97 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን አስታውቆ ነበር።

ከአየር በተጨማሪ የምድር ላይ ጥቃት የጀመረችው እስራኤል በበኩሏ ሰፋ ያለ የፍልስጤምን ግዛት እንደምትወር ተናግራለች።

የጋዛ የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ማህሙድ ባሳል በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል ሴቶች እና ህጻናት ይገኙበታል ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አክለውም መንታ ልትወልድ የተቃረበች ነፍሰ ጡር ከሶስት ልጆቿ፣ ከባለቤቷ እና ከእህቷ ጋር እንደጠፋች ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ከሚገኘው አል አህሊ ሆስፒታል የተገኘ ቪዲዮ በከፋ የተጎዱ ህጻናት በመኪና ወደ ማዕከሉ ሲወሰዱ ያሳያል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ በጋዛ ከተማ ጥቃት ያደረሰበት ስፍራ የሐማስ ተዋጊዎች ጥቃቶቻውን የሚያቀነባብሩበት ስፍራ መሆኑን ነው።

በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርስን ጉዳት ለመከላከል በርካታ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም መግለጫው አክሏል።

የእስራኤል መከላከያ በተጨማሪ በጋዛ ምስራቃዊ ሸጃያ አካባቢ በፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 12 ሰዎች መገደላቸውን የሲቪል መከላከያው ገልጿል።

የሁለት ትንንሽ ህጻናት አስክሬን ከፈራረሰ ህንጻ ውስጥ በአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ሲወጣ የሚያሳይ ቪዲዮ ለቋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ የአረብኛ ፕሮግራም እንደተናገሩት “ድንገተኛ ኃይለኛ ፍንዳታ” ከእንቅልፋቸው እንደቀሰቀሳቸው ተናግረዋል።

ፍንዳታውም የተሰማው አያድ በተሰኙ ጎረቤታቸው ቤት ነው ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ከእስራኤል መከላከያ በኩል ወዲያውኑ ምላሽ ባይሰጥም ሐሙስ ጥዋት የሸጃያ እና አራት አጎራባች አካባቢ ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው በአስቸኳይ ወደ ምዕራባዊ ጋዛ ከተማ እንዲሄዱ አስገዳጅ መመሪያ አስተላልፏል።

“የአሸባሪዎችን መሰረተ ልማት ለማውደም፤ በከፍተኛ ኃይል እየሰራ ነው” የሚል ማስጠንቀቂያም የታከለበት ነው።

የእስራኤል ጦር በቅርቡ 15 የፍልስጤም የህክምና ባለሙያዎችን በራፋህ አካባቢ የገደለ ሲሆን ከሳምንት በኋላ አስከሬናቸው የተገኘውን የእነዚህን ግለሰቦች ቀብር፣ የተባበሩት መንግሥት “የጅምላ መቃብር” ሲል ገልጾታል።

ዘጠኝ ሰዎችን ጭኖ የነበረው አምቡላንስ አልሃሺን በተባለ ስፍራ ከሳምንት በፊት ከፍተኛ ተኩስ እንደተፈጸመበት ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ገልጿል።

ለሳምንት ያህል ወደ ስፍራው መድረስ በመከልከሉ አስከሬናቸው ከተገደሉ ከሳምንት በኋላ እሁድ፣ መጋቢት 21/ 2017 ዓ.ም መወሰዱ ተገልጿል።

የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማህበር ከሰራተኞቹ በተጨማሪ ስድስት የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ እንዲሁም አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኛ አስከሬኖችም ተገኝቷል ብለዋል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ50 ሺህ 399በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

የጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ባሉት 18 ወራት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) 18 ሺህ ህጻናት መገደላቸውን፣ ከ34 ሺህ በላይ መቁሰላቸውን እንዲሁም አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት በተደጋጋሚ መፈናቀላቸውን ገልጿል።

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ማንኛውም ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ ከአንድ ወር በፊት ክልከላ ማስቀመጧን ተከትሎ የሰብዓዊ ቀውሱ መክፋቱን የረድዔት ድርጅቶች እየገለጹ ነው።

እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሦስተኛው የጋዛ ሕንጻዎች መውደማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።