
ከ 4 ሰአት በፊት
በዛምቢያ ዋና መዲና ሉሳካ በቅርብ በተሰሙ ተደጋጋሚ የህፃናት መደፈር ሪፖርቶች ምክንያት የአደባባይ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል።
ባለፉት ሁለት ወራት ዛምቢያዊያን ሞትንም ባስከተሉ በበርካታ የህፃናት መደፈር ሪፖርቶች ደንግጠዋል።
በጣም ዘግናኝ ከሆኑ ሪፖርቶች መካከል ለካንሰር ሕክምና ሆስፒታል የተኛችውን የሰባት ዓመት ልጁን የደፈረ አባት ይገኝበታል።
የአምስት ዓመት ልጅ በአራት ወንዶች በቡድን መደፈርን ጨምሮ የስድስት ዓመት ልጁን በመድፈር የብልት ኪንታሮት እና የአባላዘር በሽታ ያስያዘ አባት ታስሯል።
የዛምቢያ ፍትሕ ሚኒስትር ፕሬንሰስ ካሱኑ-ዙሉ መድፈርን ለመከላከል እና ህፃናትን ከጥቃት ለመጠበቅ የደፋሪዎች ብልትን መቁረጥ የመሰለ ከመጠን በላይ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።
“እንደ አገር ከዚህ በታች መውረድ እንችላለን? እንደ ማኅበረሰብ ከዚህ በታች ምን ያህል ዝቅ እንላለን? እየሆነ ያላው ያሳምማል። አሁን ከሕግ በላይ ነው። ሞራላችን ለምን እንደዘቀጠ ዛምቢያዊያን መመርመር የእናንተ ፋንታ ነው” ብለዋል ለአገሪቱ እንደራሴዎች።
ሪፖርቶቹን ተከትሎ ሐሙስ ዕለት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ሙዚቀኞች እና ግለሰቦች የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ መንግሥት የህፃናት ደፋሪዎች ላይ ከባድ ቅጣትን የሚጥሉ ሕጎችን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
- ሜታ በተወነጀለበት በኢትዮጵያ ጦርነት ሚናው በኬንያ ሊከሰስ እንደሚችል ተወሰነከ 3 ሰአት በፊት
- የዓለማችን አምስት ግዙፍ ምጣኔ ኃብቶች የትራምፕን ታሪፍ እንዴት ተመለከቱት?ከ 5 ሰአት በፊት
- በሥራ ጫና ምክንያት የሚመጣ ሕመም ምን ማለት ነው? መንስዔውና ምልክቶቹ ምንድን ናቸው? እንዴትስ ማገገም ይቻላል?ከ 5 ሰአት በፊት
ለምክትል ፕሬዝዳንት ሙታላ ናሉማንጎ በደረሰ የፊርማ ስብስብ በህፃናት መድፈር የተጠረጠሩ ሰዎች ዋስትና እንዲከለከሉ የሕግ ለውጥ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጉዳዩ ሁሉንም የዛምቢያ ዜጋ የሚያሳስብ በመሆኑ አቋም መያዝ አለበት ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በተቃውሞ ሰልፉ የተሳተፈች ሙዚቀኛ “ለልጆቻችን ደኅንነት ያለው ከባቢ ልንፈጥር ይገባል” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ሲስታ ዲ በሚል ስም የምትታወቀው ሙዚቀኛ ህፃናት ደፋሪዎች ብልታቸው ሊቆረጥ ይገባል ያለችም ሲሆን፤ ይህም “ለህፃናት ደኅንነት ሲባል እና ከወንድነት ክብራቸው መግፈፍ ያስፈልጋል። ምክንያቱም አይገባቸውምና” ብላለች።
እ.አ.አ በ2024 ሦስት ወራት ብቻ በዛምቢያ ከህፃናት ፆታዊ ጥቃት ጋር የተያያዙ ከ10 ሺህ የሚበልጡ ሪፖርቶች ተመዝግበዋል።
የአገሪቱ ብሔራዊ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንደዘገበው አብዛኞቹ ሪፖርቶች በዋና ከተማው ሉሳካ ተመዝግበዋል።