
4 ሚያዚያ 2025, 11:55 EAT
ተሻሽሏል ከ 31 ደቂቃዎች በፊት
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ የንግድ አጋሮች ላይ ታሪፍ ቢጥሉም ሩሲያ በዚህ ዝርዝር ውስጥ አልተካተተችም።
ለዚህም ምክንያቱ አሜሪካ በሩሲያ ላይ የጣለችው የቀደመ ማዕቀብ “ትርጉም ያለው የንግድ ልውውጥን ስለሚከለክል ነው” በማለት የዋይት ሃውስ የፕሬስ ጸሐፊ ካሮላይን ሌቪት መናገራቸውን የአሜሪካው ሚዲያ አክሲዮስ ዘግቧል።
ሆኖም ከአሜሪካ ጋር ያነሰ የንግድ ልውውጥ ያላቸው እንደ ሶሪያ ያሉ አገራት የትራምፕ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።
ሶሪያ በባለፈው ዓመት ወደ አሜሪካ 11 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን መላኳን የተባበሩት መንግሥታት ደርጅትን መረጃ ዋቢ አድርጎ ትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ የተሰኘው ተቋም አስፍሯል።
ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2022 በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ አሜሪካ መጠነ ሰፊ ማዕቀብ ጥላለች።
ትራምፕ ወደ ዋይት ሃውስ ከተመለሱ በኋላ በሩሲያ ላይ እየተከተሉት ፖሊሲ መሻሻል አሳይቷል።
ትራምፕ የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም ቅድሚያ ሰጥተዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ድርድር በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት አንድ ከፍተኛ የሩሲያ ባለስልጣን ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ለመወያየት ዋሽንግተን ይገኛሉ።
- በፕሬዝዳንት ትራምፕ ታሪፍ ምክንያት የአሜሪካ አክሲዮን ገበያ ከ2020 ወዲህ አሽቆለቆለከ 2 ሰአት በፊት
- የዓለማችን አምስት ግዙፍ ምጣኔ ኃብቶች የትራምፕን ታሪፍ እንዴት ተመለከቱት?ከ 5 ሰአት በፊት
- ትራምፕ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ100 አገራት ላይ ታሪፍ ጣሉ3 ሚያዚያ 2025
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ባለፈው ወር ትራምፕ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተኩስ አቁም ስምምነት ካልተስማሙ የሩስያን ዘይት በሚገዙ አገራት ላይ 50 በመቶ ታሪፍ ይጠብቃቸዋል በሚል አስጠንቅቀው ነበር።
ሩሲያ በትራምፕ ታሪፍ ዝርዝር ውስጥ ያልገባችው በተጣለባት ማዕቀቦች ምክንያት መሆኑን የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ሐሙስ ዕለት አጽንኦት ሰጥተው ዘግበዋል።
“በሩሲያ ላይ ታሪፍ አልተጣለም፤ ይህ ለየት ያለ ስፍራ ስለተሰጠን አይደለም። ምዕራቡ ዓለም ማዕቀብ በአገራችን ላይ ቀድሞውኑ ስለጣሉ ብቻ ነው” ሲል መንግሥታዊው ሮሳያ 24 ቴሌቪዥን ዘግቧል።
ሩሲያ በታሪፍ ዝርዝር ውስጥ አለመካተቷ “አብዛኛው ምዕራባውያኑን ያናደደ ነው” ሲልም ነው ሌላኛው መንግሥታዊ ሚዲያ የዘገበው።
በርካታ በክሬምሊን ቁጥጥር ስር ያሉ መገናኛ ብዙኃን “ሩሲያ እና ቤላሩስ ጋር የንግድ ልውውጥ የለንም። ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል” በማለት የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት ለፎክስ የዜና ወኪል የተናገሩትን ጠቅሰዋል።
አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2024 3.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ከሩሲያ ማስገባቷን የአሜሪካ የንግድ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
አሜሪካ ከሩሲያ በዋነኝነትም ያስገባችው ማዳበሪያ፣ የኒውክሌር ነዳጅ እና ብረቶችን መሆኑንም ትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ እና የሩሲያ ሚዲያዎች ሪፖርት አድርገዋል።
አንዳንድ የሩሲያ ሚዲያዎች በተለይም በአውሮፓ ላይ የተጣለውን ታሪፍ በምጸትና በመዘባበት ነው የዘገቡት።
ዩክሬን በበኩሏ ወደ አሜሪካ በምትልካቸው ምርቶቿ ላይ 10 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባታል።
የአገሪቱ ተቀዳሚ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዩሊያ ስቪሪደንኮ አዲሱ የአሜሪካ ታሪፍ በአብዛኛው አነስተኛ አምራቾችን ይጎዳል ብለዋል።
በተጨማሪም ዩክሬን የተሻሉ ውሎችን ለማግኘት ጥረት እያደረገች ነው ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2024 ዩክሬን ለአሜሪካ 874 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርቶችን ስትልክ ከአሜሪካ ያስገባችው ደግሞ 3.4 ቢሊዮን ዶላር ምርቶችን እንደሆነ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
“ዩክሬን ለአሜሪካ እንደ ታማኝ አጋር እና ደጋፊ የምትሰጠው ብዙ ነገር አላት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሯ አክለውም ” ፍትሃዊ ታሪፍ ሁለቱንም አገራት ይጠቅማል” ብለዋል።
በአሜሪካ እና ዪክሬን መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ አነስተኛ ቢሆንም አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ለሚደረገው ጦርነት ከፍተኛ የቁሳቁስ ድጋፍ ለዩክሬን አድርጋለች።
ትራምፕ አገራቸው ለዩክሬን ያደረገችው ድጋፍ ከ300-350 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ አገሪቱ በአጠቃላይ በአውሮፓ ለምታደርገው ስልጠና እና የመከላከያ ክምችቷን ለመሙላት የፈጀችው 182.8 ቢሊዮን ዶላር ነው ብሏል። አሜሪካ እስካሁን ላደረገችው ድጋፍ እንዲሁም ጦርነቱ ሰላማዊ እልባት እንዲሰጠው ዩክሬን ማዕድናት እንድትሰጣት እየጠየቀች ትገኛለች።